መግቢያ
ኤፍሬም አጭር የሕይወት ታሪክ
ቅዱስ ኤፍሬም በሦስተኛው ክፍለ ዘመን በመጀመሪያዎቹ ሰባት
አሥርተ ዓመታት ውስጥ የኖረ የሥነ መለኮት ሊቅ ፣ የዜማ ደራሲ ፣ ባለቅኔ ፣ ሰባኪ ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ተርጓሚ የሆነ ጻድቅ
አባት ሲሆን ፣ በጊዜው በሮም መንግሥት ሥር በነበረችው በሶርያ ንጽቢን 1 በምትባለው ታላቅ ከተማ ከክርስቲያን ቤተሰብ በ፪፻፺፱
ዓ. ም ተወለደ ፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ከድቁና ተግባሩ በተጨማሪ ለሊቀ ጳጳሱ አማካሪም ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ሲሆን ፤ በንጽቢንም ለሚገኘው
መንፈሳዊ ትምህርት ቤት መሥራችም ነበር ፡፡ ብዙ ጊዜ ጳጳስ እንዲሆን ቢለመንም መሆንን ግን አልፈቀደም ፡፡ ስለቅዱስ ኤፍሬም
በዝርዝር የጻፈውም ፊሊፕ ስካፍ (Philip Schaff) የቅስና ማዕረግን ሳይሾም አይቀርም ይለናል3፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ከሌሎች በዘመኑ ከተነሡት ቅዱሳን አባቶች ይልቅ የተለዩ የቅድስና ጠባያት ይንጸባረቁበት ነበር ፡፡
አንደኛው በዘመኑ በተነሡ ሃይማኖታዊ ውዝግቦች ውስጥ እጁን ከማስገባት ተቆጥቦ ትክክለኛውን ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ፣ ኪናዊ
በሆነ መንገድ ፣ በመጻፍና በማስተማር መትጋቱ ነው ፡፡
እርሱ የሚቃወመው ሰዎችን ሳይሆን ትምህርታቸውን ነው ፤ ስለዚህም ትምህርታቸው በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት ያልጣፈጠ
እንደሆነ ለማስረዳት ሲል በመንፈስ ቅዱስ የተቀመመ እጅግ ማራኪ የሆነ ትምህርትን በማስተማር ይተጋ ነበር ፡፡ በዚህ ጠባዩ
“የመንፈስ ቅዱስ በገና” ለመባል በቅቶአል ፡፡
ሁለተኛው የቅዱስ ኤፍሬም ልዩ
የሆነው የቅድስና ጠባዩ ፣ ለሴቶች እናቶቻችንና እኅቶቻችን የሚሰጠው ልዩ አክብሮትና ቦታ ነው ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም የዜማ
ድርሰቶቹን ደርሶ ካበቃ በኋላ ለሴቶች በማስጠናት በቤተክርስቲያን እንዲያቀርቡት ያደርግ ነበር ፡፡ አብዛኛዎቹም ድርሰቶቹ በሴት
አንቀጽ የተጻፉ ናቸው ፡፡
ለምሳሌ የኒሲቢሳውያን መዝሙር በሚለው ድርሰቱ ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኛለን ፡፡
“ የአንተና ለአንተ ስለሆንኹት ጌታ ሆይ ስለእኔ ቅናትን ቅና ፡፡ እኔ ለአንተ የታጨሁ ነኝ ፡፡ ሐዋርያት እኔን
ለአንተ አጭተውኛል ፡፡ አንተም ቀናተኛ ስለመሆንህ እነርሱ ነግረውኛል ፡፡ ለንጹሐን ሚስቶች የባሎች ቀናተኝነት ልክ እንደ
ግንብ ከርኩሰት ሁሉ ይጠብቃቸዋል ፡፡ … ስለሚስቱ የማይቀና ባል ሚስቱን እንደሚንቃት ያሳየናል ፡፡ ቅናት በልብ ውስጥ ያለን ፍቅር
እንዲገለጥ ያደርገዋል ፡፡ … የፍቺዋን ጽሕፈት ሰጥቶአት ፈትቶአታል እንዳይሉኝ ጌታ ሆይ ቸል አትበለኝ ፡፡ ስለጠላትና
ስለናቃት አውጥቶ ሰደዳት እንዳይሉኝ ጌታ ሆይ ከእኔ አትራቅ ፡፡
ጌታ ሆይ አንተ ቀናተኛ አምላክ ትባላለህና ስለእኔ ያለህን ፍቅር እኔን ከርኩሰት በመጠበቅ አሳየኝ ፡፡ … ጌታ ሆይ የደረሱ ልጃገረዶቼና ሕፃናት ልጆቼ ወደ አንተ ወዮ እያሉ ይጮሃሉ ፡፡
የታጩ ልጃገረዶቼም ወደ አንተ ድምፃቸውን ያሰማሉ ፡፡ በእድሜም
አረጋውያን የሆኑትም የሰቆቃን እንባን ያነባሉ ፡፡ ደናግላኖቼም ጾምን ይዘዋል ፡፡ የበኩር ልጆቼም ጌታ ሆይ ማቅ
ለብሰዋል" 4 በማለት ይጸልያል ፡፡
አብዛኛዎቹ የዜማ ድርሰቶቹም እንዲሁ በሴት አንቀጽ
የተነገሩ ናቸው ፡፡ ለቅዱስ ኤፍሬም ሴቶች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ናቸው ፡፡ ተፈጥሮአቸውን ሁሉ እግዚአብሔራዊ ትምህርትን
ለማስተማር ይጠቀምበታል ፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ሴቶች
እኅቶቻችንን እንዲህ በማለት ይጣራል ፡-
“እናንተ የአሕዛብ ልጃገረዶች ሆይ ! ኑ ወደዚህ ቅረቡ ፣ አዲስ ምስጋናን ተማሩ ፤በእኅታችሁ በቅድስት
ድንግል ማርያም በኩል ፣ ለምስጋና አንደበታችሁን ክፈቱ ፤ከእርሱዋ በመወለድ የመናገር ነጻነታችሁን ላጎናጸፋችሁ ምስጋናን
አቅርቡ ፡፡” 5
በዚህ ምክንያት ቅዱስ ያዕቆብ
ዘስሩግም ቅዱስ ኤፍሬምን“ለሴቶች ሁለተኛው ሙሴ”6 ብሎ ይጠራዋል ፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም አብዛኛውን የጽሑፍ ሥራዎቹን የሠራው በንጽቢን ሲሆን ፤ የሮም መንግሥት በመዳከሙ ምክንያት በጊዜው የሮም
ቄሳር የነበረው ጆቫኒያ ለፋርስ መንግሥት ንጽቢንን መታረቂያ አድርጎ ስለሰጠና ክርስቲያኖችንም ከከተማዋ አውጥቶ
እንዲሰዳቸው ለፋርሱ ንጉሥ በመፍቀዱ በ ፫፻፶፮ ዓ.ም ንጽቢንን ጥሎ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ወደ ኤዲሳ(ዑር)7ተሰደደ ፡፡ በኤዲሳም በቆየባቸው አሥር ዓመታት ውስጥ
በከተማው በነበረው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ ሳለ ፣ በከተማዋ በተቀሰቀሰው ወረርሽኝ ምክንያት ሕመምተኞችን ሲረዳ
ቆይቶ በ፷፯ ዓመቱ ግንቦት 29 /፫፻፷፮ ዓ. ም አረፈ ፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም የደረሳቸው የዜማ ድርሰቶች ከአራት መቶ በላይ ቅኔያዊ ግጥሞችን ያዘሉ ሲሆኑ ፣ ከሦስት ሚሊዮን በላይ
ስንኞች በውስጣቸው አካተው ይዘዋል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ
ዘፍጥረትን ፣ዘጸአትን ፣አራቱ ወንጌላትን8 ፤ የሐዋርያት ሥራን ፣ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታትን ፣ በሙሉ ተርጉሟቸዋል ፡፡ እንዲሁም በቁጥር አይብዙ እንጂ
ስብከቶችንና ፣ መልእክታትን የጻፈ ሲሆን ፤ መርቅያውያንንና በዘመኑ የተነሡ ከሃዲያንን በመቃወም ጽሑፎችን አዘጋጅቶአል ፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ጽሑፎቹ መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ሲጠፉ አብዛኛዎቹ ግን ዘመን ተሻግረው አስከ አሁኑ ዘመን ድረስ በሶሪያ ገዳማት
ተጠብቀው ይገኛሉ ፡፡
የኤፍሬም ሥራዎች በዘመኑ በአርመን ፣ በግሪክ ፣ በግብጽ
፣ በጆርጂያ ቋንቋ እንደተተረጎመ ይታመናል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሶሪያ ቋንቋ ተናገሪ ሀገራትም ዘንድ ሥራዎቹ በጣም የታወቁ
ናቸው ፡፡ ባለንበት ዘመንም ብዙዎቹ የቅዱስ ኤፍሬምን ሥራዎች ከሶሪያ ቋንቋ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ እየተተረጎሙ ይገኛሉ
፡፡
የሚደንቀው ግን ከእነዚህ ሁሉ የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች መካከል ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የሚታወቀውና ወደ ግእዝ በኋላም ወደ አማርኛ ተተርጉሟል ተብሎ የሚገመተው የእርሱ ሥራ ውዳሴ ማርያም ብቻ ነው ፡፡ ይህ ለምን
እንደሆነ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ፣ ግምት ግን ማስቀመጥ ይቻላል ፡፡
እንደሚታወቀው በቤተክርስቲያን ታሪክ ሁለት ታላላቅ ትምህርት ቤቶች ነበሩ ፡፡ አንደኛው የእስክንድሪያው ሲሆን
ሁለተኛው የአንጾኪያው የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት ነው፡፡ የእስክንድርያው ትምህርት ቤት በይበልጥ በዶግማ ትምህርቶች ላይ
ያተኮረ ሲሆን ፤ የአንጾኪያው ትምህርት ቤት ግን ምንም እንኳ
መሠረታዊ የሆኑ የዶግማ ትምህርቶችን ባይስተውም ፣ ይበልጥ ትኩረት ይሰጥ የነበረው በክርስቲያናዊ የሥነምግባር ትምህርቶች ላይ
ነበር ፡፡
በዚህ ምክንያት የእስክንድርያው ትምህርት ቤት በዶግማ ትምህርት ላይ ፣ የአንጾኪያው ትምህርት ቤት ግን
በሥነ ምግባር ትምህርት ላይ የበሰሉ መምህራንን አፍርተዋል ፡፡
ይህን ያመጣው የትምህርት አሰጣጣቸው ዘይቤ ነው ፡፡ የእስክንድርያው ትምህርት ቤት ጌታችንን በተመለከተ
የሚሰጠው ትምህርት ከአምላክነቱ ጀምሮ ሰው ወደ መሆኑ የሚወርድ የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤ ሲሆን ፤ የአንጾኪያው ትምህርት ቤት
ግን ከሰውነቱ ጀምሮ ወደ አምላክነቱ የሚያመራ የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤን ይከተላል ፡፡
እነዚህም የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤዎች የየራሳቸው ውጤቶች ነበሩዋቸው ፡፡ ለምሳሌ የእስክንድርያው ትምህርት ቤት
በመንፈሳዊ እውቀት ለበሰሉ ሰዎች የሚሰጥ ትምህርት ስለሆነ ተደራሽነቱ ለጥቂቶች ነበር ፤ የአንጾኪያው ግን ማንም በቀላሉ
በሚረዳው መልኩ የሚቀርብ ስለሆነ ብዙኃንን ተደራሽ ያደረገ ትምህርት ነበረው ፡፡ ምክንያቱ ስለክርስቶስ ለማስተማር ሲባል ልዩ
ልዩ ምሳሌዎችን እንዲጠቀሙ ይገደዱ ነበርና ፡፡
በዚህም ምክንያት የእስክንድርያው ትምህርት ሰሚውን ወደ ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲመራ ፤ የአንጾኪያው ግን በክርስቶስ
ሰውነት ላይ ያተኮረ ትምህርትን የሚሰጥ በመሆኑ ወደ ፍቅረ እግዚአብሔር የሚመራ ሆኖአል ፡፡
ይህን በአንዴ ለመረዳት የሚያስቸግር ስለሆነ ቤተክርስቲያናችን የምትቀበላቸውን የእስክንድርያ እና የአንጾኪያ
መንፈሳውያን ትምህርት ቤቶች ያፈሩዋቸውን የቅዱሳን አባቶችን መጻሕፍት መመርመር ጠቃሚ ነው ፡፡
ቢሆንም እነዚህ ትምህርት ቤቶች
እነርሱን በሚከተሉት አብያተ ክርስቲያናት ላይ የራሳቸውን ተጽእኖ ማሳረፋቸው አልቀረም ፡፡ የእስክንድርያው
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ፣ የአንጾኪያው ደግሞ በሶሪያና በዙሪያው ባሉት የክርስትና እምነት ተከታዮች
ላይ ተጽእኖአቸውን አሳድረዋል ፡፡
ስለዚህም
የእስክንድርያው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እነ ቅዱስ አትናቴዎስን ፣ እነ ቅዱስ ቄርሎስን ሲያፈራ ፡፡ የአንጾኪያው ደግሞ እነ
ቅዱስ ኤፍሬምን፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን እንዲሁም እነ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግን አፍርቶአል ፡፡
የእስክንድርያውን የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤን የሚከተሉ
አብያተ ክርስቲያናት ይበልጥ ምዕመኑን ወደ ፈሪሐ እግዚአብሔር ሲመሩት ፡፡ የአንጾኪያውን የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤን የሚከተሉ
አብያተ ክርስቲያናት ግን ምዕመኑን ወደ ፍቅረ እግዚአብሔር የሚመሩ ናቸው ፡፡ ይህ የመነጨው ከትምህርት አሰጣጣቸው ይዘት ነው
፡፡
ስለዚም ምዕመኑን ወደ ፍቅረ እግዚአብሔር ለመምራት የሶሪያ ቅዱሳን አባቶችን ሥራ ወደ አማርኛ መልሼ ወደ ምዕመኑ
በማድረስ የበኩሌን አስተዋጽኦ ማበርከ እንዳለብኝ ተሰማኝ ፡፡
በመሆኑም ስሙን በጣም የምናውቀው ነገር ግን ሥራዎቹን በሚገርም ሁኔታ የማናቅለትን ፣ የሴማዊ ትውፊት አባት ከሆነው ከቅዱስ
ኤፍሬም ሥራዎች መካከል ስለጌታችን የሰበከውን ስብከትና ተግሣጽ እንዲሁም በጥምቀት ዙሪያ የእርሱን ምልከታ ወደ አማርኛ ተርጉሜ
ለአንባብያን እነሆ ብያለሁ ፡፡
ማሳሰቢያ
ወደ ዋናው የምንባብ ክፍል አንባቢያን ከመግባታቸው በፊት እንዲያጤኑት የምፈልገው ነጥብ አለኝ ፡፡ እርሱም ፡- ይህ
ወደ አማርኛ የተመለሰው የቅዱስ ኤፍሬም ስብከትና ተግሣጽ አንባቢው በተመስጦ ሆኖ በፍላጎት እንዲያነበው ሲባል በምዕራፍና በንዑሳን ርዕሶች የተከፋፈለ ሲሆን ፣ ከእያንዳንዱ ርዕስ ሥር
ከቅዱስ ኤፍሬም የቅኔ ድርሰቶች መካከል ፣ ርዕሶቹን ይገልጣሉ ያልኩዋቸውን መርጬ አስገብቻለሁ፡፡ ወደ ፊት እግዚአብሔር ቢፈቅድ
የእርሱን የቅኔ ድርሰቶችን ተርጉሜ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ስለዚህ አንባቢው አባባሎቹን ሲያነብ ከምንባቡ የወጡ እንዳይመስሉት እንዲረዳልኝ በመንፈሳዊ ትሕትና እጠይቃለሁ ፡፡
መልካም ንባብ!!
ምዕራፍ 1
የጌታችን ልደት እንዲሁም ስቅለት ፍሬዎች
የአሕዛብ ምሳሌ ለሆነው ለኤፍሬም ዳግም ልደት ፤ ፍጡር የነበረው መስቀል ምክንያት ሆነው ፤ ጌታችን ወደ ኤፍሬም ከተማ ባቀና ጊዜ ፤ አሕዛብ በቅርንጫፎቻቸው ሆነው ምስጋናን ለእርሱ አወጡ ፤ ግሩዛን ግን ለእርሱ ምስጋናን ከማቅረብ ይልቅ ዝምታን መረጡ ፤ እርሱንም ተቃወሙ ፡፡ ምሥጢር ተገለጠ ፤ አሕዛብ ሆሳዕና ያለውን ሕዝብ ቀድመው በጥምቀት የእግዚአብሔር የበኩር ልጆች ተሰኙ”
የእግዚአብሔር ጸጋ አስቀድመው የስድብ ቃል ወደሚያወጡ አንደበቶች ቀረበ ፈወሳቸውም ፤ በዚህም ምክንያት የምስጋናን ቅኔን የሚያወጡ በገናዎች ሆኑ ፡፡ ስለዚህም አንደበቶች ሁሉ እነርሱን ከስድብ ቃል ያወጣቸውን ጌታ ያመስግኑ ፡፡
ጌታ ሆይ ለላከህ ማደሪያዎቹ እንሆን ዘንድ ከላይ ከአርያም ዝቅ ብለህ ማደሪያህን ከእኛ ዘንድ አድርገሃልና ለአንተ ክብርና ውዳሴ ይሁን ፡፡ የእግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁ የሆነ እርሱ ከልዕልናው ዝቅ በማለት ማደሪያውን ከድንግል አደረገ ፡፡ ተፈጥሮአዊ(ያለወንድ ዘር) በሆነው ልደትም በሥጋ ተወልዶ የብዙኀን ወንድም ተባለ ፡፡
በሲኦል ይረገጡ የነበሩ ነፍሳትን ከጥልቁ በማውጣት ወደ መንግሥቱ የሚፈልሱበትን ጎዳና ያበጅ ዘንድ ሲኦልን ድል በመንሣት ወደ መንግሥቱ በክብር ተመለሰ ፡፡ ነፍሳትን ያለ ልዩነት ከምትውጠው ሲኦል አውጥቶ የተጠሩትን በልዩነት ወደምትቀበለው መንግሥቱ ያገባቸው ዘንድ ጌታችን ትንሣኤውን ለሙታን(ለሰው ልጆች) እንደማረጋገጫ ማኅተም አድርጎ ሰጣቸው ፡፡ እንዲህ ማድረጉ በውስጧ የያዘቻቸውን ነፍሳት ሁሉ እኩል ከምታስተካክለው ከሲኦል አውጥቶ ሰዎችን እንደ ሥራቸው ወደምትቀበለው መንግሥቱ ያፈልሳቸው ዘንድ ሥርዐት መሥራቱን ሊያስረዳን ፈልጎ ነው ፡፡
ፈራሽ በስባሽ የሆኑት ከሚጋዙባት ከሲኦል አውጥቶ ጸጋውን እየተመገቡ ወደሚኖሩባት
መንግሥቱ ያገባን ዘንድ ፤ አንዲሁም ባለጸጎች ከሚኖሩባት ፣
የዚህ ዓለም ፍሬዎችና አበቦች ከሆኑት ማደሪያዎች አውጥቶ ወደማታልፈው የእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን ያገባን ዘንድ
ወደ ሲኦል የወረደውና ሲኦልን ድል በመንሣት በክብር ያረገው እርሱ ነው ፡፡
በተፈጥሮአዊ ልደት የተወለድን እኛ ከተፈጥሮአችን ውጪ በሆነ ልደት
እንወለድ ዘንድ እንዲገባን ሊያስገነዝበን በባሕርይው የእግዚአብሔር አብ የበኩር ልጅ የሆነው እርሱ ከባሕርይው ውጪ በሆነ በሌላ
ልደት ተወለደ ፡፡
ሥጋዊ በሆነ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዘፈ አካል አለው እንደማንለው
ሁሉ ፤ እንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም ፡፡ ከአብ ዘንድ የሆነውን ልደቱን
መርምረን የማንደርስበት እርሱ መርምረን በምንደርስበት በሌላ ልደት ተወለደ ፡፡ ይህም ለጌትነቱ ወሰን ለጸጋው ስጦታውም መጠን
የሌለው መሆኑን ያስተምረን ዘንድ ነው ፡፡
ጌትነቱ እጅግ ታላቅ የሆነው እርሱ ቅድመ ዓለም ልደቱ በፍጡራን አእምሮ
ተመርምሮ የማይደርስበት ፣የጸጋ ስጦታውም በስፍር የማይመጠን ፣ ድኅረ ዓለም ልደቱ በፍጡራን አንደበት የተሰበከለት ነው ፡፡
እንደ ተፈጥሮአችን ከሰው ወገን
የተወለድን እኛ ፣ ከተፈጥሮአችን ውጪ በሆነ ልደት ከእግዚአብሔር ተወልደን ከባሕርያችን ውጪ በመንፈስ እንድንጠመቅ ከባሕርይው
ውጪ ከድንግል በመወለድ በውኃ የተጠመቀ እርሱ በባሕርይው የእግዚአብሔር አብ ብቸኛ ልጁ ነው ፡፡
ስለዚህ ቅድመ ዓለም ከአብ
የተወለደ እና ለሁለተኛ ልደቱ ወደዚህ ዓለም የመጣው እርሱ አስቀድሜ ወደ ሰበኩላችሁ ወደ ሁለተኛ ልደት እኛን ያመጣን ዘንድ
የመጣ ነው ብልም ፤ ቅድመ ዓለም ከአብ ዘንድ ያለው ልደቱን በእምነት ከመቀበል ውጪ መርምረን ልንደርስበት የማንችለው ነው ፡፡
እንዲህም ስል ድኅረ ዓለም ከሴት መወለዱን ማሳነሴ አይደለም ፡፡
እጅግ የሚልቅ ነው እንጂ ፡፡
የእርሱ የመስቀል ላይ ሞት
ከሴት ስለመወለዱ ምስክር ነው ፡፡ እርሱ ሊሞት የሚችለው በሥጋ ከሴት የተወለደ አንደሆነ ብቻ ነውና ፡፡ የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል የምሥራች ቃል (“የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል”(ሉቃ. ፩፥፴፭) የሚለው የእርሱን
አምላክነት የሚያውጅ ነው ፡፡ እርሱ ከልዑል ኃይል ከሆነ ከወንድ ዘር ላለመገኘቱ ግልጽ የሆነ መረጃ አገኘን ማለት ነው ፡፡
ስለዚህም የእርሱ ፅንሰት
ከመስቀሉ ሞት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው ፡፡ ቅድመ ዓለም ከአብ ዘንድ ያለውን ልደት የሚክድ በእርሱ ስቅለት ይገሠጻል ፤
እንዲሁም ልደቱ ከድንግል ማርያም የሚጀምር ነው ፤ ስለዚህም
ፍጡር ነው፤ በማለት የሚናገረውን ለማሳፈር ቅድመ ዓለም ልደቱ ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የብሥራት ቃል ጋር በጥብቅ
የተሳሰረ ነው፡፡ ምክንያቱም የእርሱ ቅድምና በመልአኩ ቃል ተብራርቶ ተገልጧልና ፡፡
እግዚአብሔር አብ እርሱን
ወለደው ፤ እርሱም ፍጥረታትን ፈጠረ ፡፡ ሥጋን ለበሰ በእርሱም የሥጋን ፈቃድ ገደለ ፡፡ በእርሱ የሰውነታችንን ዝገት ያስወግድ
ዘንድ ጥምቀትን መሠረተልን( ንባቡ በጥምቀት ተወለደ ነው የሚለው) ፤ ከሲኦልም በኩር በመሆን ሲኦልን ባዶ አደረጋት፡፡
ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ
የነበረው እርሱ በምድራዊ ልደት ሥርዐት ከሴት በመወለድ ወደ እኛ መጣ ፤ በምድራውያን ሰዎች ሥርዐትም በሞት ወደ አባቱ ተመለሰ
፡፡ በዚህም በሥጋዊ ልደት ወደዚህ ዓለም በመምጣቱ የሰው ልጆችን ያድን ዘንድ ይጠበቅ የነበረው ፣ በነቢያትም የተሰበከለት
እርሱ ስለመሆኑ ታወቀ ፡፡ በትንሣኤም ወደ ላይ በማረጉ ሥራውን ፈጽሞ ወደቀድሞው እሪናው መመለሱ ታወቀ ፡፡
ቀሪውን መጽሐፉን ገዝታችሁ ታነቡ ዘንድ ግብዣዬ ነው፡፡
በመጽሐፉ ከታች የተዘረዘሩትን ርዕሶች ይዳስሳል
መግቢያ
...................................................................1
የቅዱስ ኤፍሬም አጭር የሕይወት ታሪክ
..........................................................1
ምዕራፍ አንድ
የጌታችን ልደት፣ጥምቀትና ስቅለት ፍሬዎች
........................................................6
ጌታችን ሥጋ ማርያምን የመልበሱ ምክንያት
......................................................6
ቀዳማዊቱ ሔዋንና ዳግማዊቱ ሔዋን
..............................................................9
አሕዛብ ጌታችንን የማመስገናቸው ምክንያት........................................................11
የመራራው ውሃው ምሥጢር.......................................................................12
የእግዚአብሔር ወገን ስለመሆናችን ምልክቱ ምንድን ነው?........................................14
አምላክ በጣዖታት ላይ ስለስሙ የከፈተው የአግባ መልስ ጦርነት
...............................15
ለሥጋዌው የቀረበ መወድስ ቅኔ
..................................................................16
በድዳና ደንቆሮው ሰው ስለ ሥነ-ተፈጥሮ
.............................................17
ምዕራፍ ሁለት
ፈሪሳዊው ስምዖንና ዘማዊቷ ሴት
.................................................................20
በፈሪሳዊው ማዕድ ላይ የቀረበው የጌታ ማዕድ
...................................................21
የፈሪሳዊው ስምዖን እና የወገኖቹ በደል መመሳሰል
...............................................23
የፈሪሳዊው ስምዖን የልብ አሳብ በክርስቶስ ሲገለጥ
..............................................25
የትሕትና ጉልበት....................................................................................29
የደማስቆው ትዕይንትና የቅዱስ ጳውሎስ መመለስ
................................................32
የተመሰገነችው የሙሴ ትሕትና ....................................................................47
አኮቴት ለሥጋዌው..................................................................................56
ምዕራፍ ሦስት
ከስምዖን(አረጋዊው) እስከ ስምዖን (ጴጥሮስ) ....................................................55
ጌታችን በዮሐንስ መጥምቅ እጅ የመጠመቁ ምሥጢር
..........................................62
ምዕራፍ አራት
ተግሣጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
...............................................................65
ምዕራፍ አምስት
ጥምቀትን አስመልክቶ የቅዱስ ኤፍሬም ጠቅላላ ምልከታዎች ...............................80
ሥነ መለኮታዊ ቃላትና ትርጉማቸው በመጠኑ
ከመጠነኛ ማብራሪያ ጋር ...................................................................85
ትርጉሙ የተወሰደበት መጽሐፍና ዋቢ መጻሕፍት.............................................107
No comments:
Post a Comment