ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/04/2005
በመጽሐፍ ብቻ የሚለው አመለካከት
ለእኔ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ከመጽሐፍ ይልቅ በልብ ሰሌዳ በመንፈሱ
የተጻፈ የመንፈስ ቅዱስ መልእክት አለ፡፡ መንፈሱ ያደረበት ሰው የማይመረመረውንና የማያልቀውን የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃድ ወደ
መረዳት ይመጣል ሁሌም መንፈስ ቅዱስ ሰማያዊ የሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያልሰፈሩ ወይም ያልተብራሩ እውነታዎች ይገልጥለታል፡፡
በብሉይም በሐዲስም የእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ በወረቀት ላይ በብዕር ቀለም መጻፍ ያስፈለገበት ምክንያት
ሰዎች አስቀድሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ በልባቸው ጽላት ላይ የጻፈውን ፈቃዱንና ሕጉን በኃጢአት ምክንያት ፈጽመው በመዘንጋታቸው ነው፡፡
ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ፈቃዱን አውቀው በጽድቅ ይመላለሱ ዘንድ የተሰጠ ሁለተኛው እድል ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ከአዳም እስከ
ሙሴ ድረስ ያሉ ቅዱሳንና ሐዋርያት እንዲሁም ሐዲስ ኪዳን ሳይጻፍላቸው በሐዋርያት ትምህርት ይኖሩ የነበሩ ቅዱሳን ክርስቲያኖች ናቸው፡፡
ሐዋርያት በስብከታቸው ማርከው በንስሐ አቅርበው ልቡናቸውን የመንፈሱ
ማደሪያ በማድረግ የእግዚአብሔርን ሃሳብ ሐዋርያት ሲያስተምሩ በሰሚዎቹ ልቡና ያደረው መንፈስ ቅዱስ የትምህርቱን እውነተኝነት በማረጋገጥና
እነርሱም በጽሙና ሆነው ለእግዚአብሔር መንፈስ የጠየቁትን ጥያቄ ግልጽ እያደረገላቸው ሰውነታቸውን ከኃጢአት ጠብቀው በቅድስና እንዲመላለሱ
ረድቶአቸዋል እንጂ የጽሑፍ መረጃ አልስፈለጋቸውም ነበር፡፡ ከዚህ ተነሥተን የእግዚአብሔር ፈቃድ ልክ እንደ ቅዱሳን መላእክት እንደ
እግዚአብሔር መንፈስ ፈቃድ እንዲመሩ እንጂ በወረቀት ላይ በተጻፈ መመሪያ እንዲመላለሱ አይደለም፡፡
መጽሐፍ
ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተጻፈ ነው፡፡ መንፈሱ የሌለበት ምንም መጽሐፍ ቅዱስን ቢያነብ አይረዳውም፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው
መንፈሱ ሳይኖረው መጽሐፍ ቅዱስን ሸምድዶ በማወቁ የሚታበይ ከሆነ ጸሐፍት ፈሪሳዊያንን ቢመስል እንጂ ዳን አንለውም፡፡ ጻሕፍት ፈሪሳዊያን
በመጽሐፍ ሕይወት የሚገኝ ይመስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሕይወት
የሆነውን ክርስቶስ በመንፈሱ ሳያቁ ተሰነካክለው ወድቀዋል፡፡ እንዲያ ከሆነ ከመጽሐፍ ይልቅ በመንፈሱ መመራት የላቀ መሆኑ የሚያጠያይቅ
አይደለም፡፡ ቢሆንም አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ለመመራትና ለማደግ እንደ አንድ እርከን ሆኖ ያገለግላል እንጂ ፍጻሜ
አይደለም፡፡ ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው የሚዳነው የሚለውን አመለካከትን አልቀበለውም፡፡
ይህ
በኦሪት ሥርዐት አንደመላለስ ይቆጠራል፡፡ እነርሱ በወረቀት ላይ በሰፈረ ቃል ብቻ የሚመሩ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለው
አመለካከትን የምንከተል ከሆነ ከኦሪታዊያን በምን ተለየን ታዲያ? ይህ ብዙዎችን የራሳቸውን ትርጉም እንዲሰጡ በማድረግ እንደ ራሳቸው
ፈቃድ እንዲመላለሱ በር ከፍቶአል፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ግን አንድ ነው፡፡ በእርሱ የተሰጠው ትምህርት ሁሉ መንፈሱ ያደረባቸውን
ሁሉ እንደ አንድ አካል ግን እንደተለያዩ ብልቶች ሆነው የአንዱን አካል የክርስቶስን ፈቃድ እንዲተገብሩ ያበቃቸዋል፡፡ ስለዚህ በእርግጠኝነት
ከመጽሐፍ ይልቅ በመንፈሱ መመራት ይበልጣል፡፡ በመንፈሱ ከተመራን ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስም በላይ ነን፡፡ ነገር ግን ለሕጻናት ከእግዚአብሔር
መንፈስ ፈቃድና ሃሳብ ጋር እንዲተዋወቁ መጽሐፍ ቅዱስን ሊማሩ ሊያነቡ ይገባቸዋል፡፡
ወንድሜ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አሳብ ነው:: ያለዚያ ወደ እነንቶኔ ጎራ ያቀላቅላል:: ጃንደረባው ያስተማረንና የሐዋርያት ስብከት ካንተ አሳብ ተለይቶ ይታየኛል:: የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? ፤ ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? የሚሉትን አሳቦች እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
ReplyDeleteትሑቱ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በጥምቀት መንፈስ ቅዱስ ሳያድርበት በፊት ያለ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ስለማይቻል ፊልጶስን ጠይቆታል፡፡ ያለሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ ማለቱም ወደ እምነት ለሚመጡት የተነገረ ነው፡፡ እኔ ላስተላልፈው የፈለገኹት የተረዳኸው አልመሰለኝም፡፡ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበቡ ብቻ ወደ እምነት ይደረሳል ይድናል መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የእምነታችን ምንጭ ነው የሚለውን ሃሳብ አለመደገፌን ነው ያሰፈርኩት፡፡ አሁንም ያለ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ መረዳት ሰዎች ሊደርሱ አይችሉም፡፡ ልክ እንደ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ አያስፈልገውም፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው መንፈስ ቅዱስ እርሱ እውነቱን ይገልጥለታልና፡፡ እኛም የክርስቶስ ልብ የተባለው መንፈስ ቅዱስን በጥምቀት ተቀብለናልና እንደ ሐዋርያትና ቅዱሳን መላእክት ሊመራን የተጠራን ነን፡፡ ይህ ግን መጽሐፍ ቅዱስን ከሀ-ፐ ማንበብን የሚጠይቅ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ ምን እንደሆነ እንለያለን፡፡ ከዚያም በውስጣችን ያደረው መንፈስ ቅዱስ ሲናገረን ማዳመጥ ይቻለናል፡፡ በመቀጠልም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መመላለስ እንጀምራለን፡፡ ይህን ይበልጥ ለመረዳት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስን ወንጌል የተረጎመበትን መግቢያውን ያንብቡ አመሰግናለሁ፡፡
ReplyDeleteወንድማችን ከላይ የቀረበውን የስጋት አስተያየት እጋራለሁና ተጨማሪ ብታክልበት?
Delete"መንፈሱ ያለበት" ማለት በልጅነት ክብር የከበረ ጥሙቅ/ምዕመን/ ማለት ከሆነ በትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርት መድከም አያስፈልግም ማለት አይሆንምን? በጥሙቃን ላይ መንፈስ ቅዱስ የሚያድር መሆኑ የታመነ ነው:: ነገር ግን ከወንጌል ትምህርት አይቦዝንም:: በዚያውስ ላይ ዘወትር የመሰበካችን ዓላማ ምንድን ነው? ሊቃውንቱ የጻፉት የተረጎሙትና ያስተማሩት ላላመኑ ብቻ አልነበረም:: ለምእመናንም ጭምር እንጂ:: ጻድቁ ባኮስ ከጥምቀት በኋላ ሰባኪ አላስፈለገውም ማለት ይቻላል? ይህም ይሁንና ይህ ለሁሉ ጥሙቃን ያገለግላልን ወይስ?
አንተ የጠቀስኽው የቅዱስ ዮሐንስን የማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ መግቢያን እንዳየሁት ከሆነ ካንተ ሀሳብ ርቆ እንደውም የሚያስረዳው ሌላ ነው:: በትንታኔው እጅግ ተደንቂያለሁ:: አንተ "አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበቡ ብቻ ወደ እምነት ይደረሳል ይድናል መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የእምነታችን ምንጭ ነው የሚለውን ሃሳብ አለመደገፌን ነው ያሰፈርኩት፡፡" ብለሀል:: ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ የመርጃ መሣሪያና የበደል ውጤት እንጂ ለመንፈሳዊ ሰው መጽሐፉም ጭምር ግድ አስፈላጊ ነገር አለመሆኑን በረቀቀ መንገድ ያስረዳል:: የአንተን አገላለጽ ብታብራራው እወዳለሁ::ታዲያ ወደ እምነት መድረስ መዳንና ሌላ ምንጭ ከየት ይገኛሉ? ያላመነስ እንዴት ይጠመቃል? አመሰግናለሁ::