ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ
20/04/2005
ቅዱስ ኤፍሬም “እንዳይፈረድባቸሁ አትፍረዱ” የሚለውን ኃይለ ቃል እንዲህ
ይተረጉመዋል፡፡(ማቴ.7፡1-2) “ጌታችን አትፍረድ ሲል ኢፍትሐዊ ፍርድን ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህም ኢፍሕታዊ ፍርድን ብትፈርድ ባንተ
ላይ ይፈረድብሃል፡፡ በመሆኑም ፍርድን የሚለይ መንፈሱ ሳይኖርህ አትፍረድ፡፡ ፍትሐዊ መስሎህ ፍትሐዊ ያልሆነ ፍርድን ልትፈርድ ትችላለህና፡፡ እንዲህም በማድረግህ ከፍርድ አታመልጥም፡፡
በመሆኑም ይህ ቃል “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይላችኋልና”(ማቴ.6፡4) ከሚለው ኃይለ ቃል ጋር
መጣመር አለበት፡፡ ይህ ኃይለ ቃል አትፍረድ ከሚለው ሕግ ጋር እንዴት ይጣመራል? ፍትሐዊ የሆነ ፍርድን በአንድ ሰው ላይ ስትፈርድ
በጸጋው ሕግ ደግሞ ይቅር ልትለው ይገባሃል፡፡ ቅን የሆነ ፍርድን ፈርዶ በጸጋ ግን ይቅር ላለ ሰው እግዚአብሔር አምላክም ይቅር
ይለዋል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ቅን ፍርድን ምክንያት አድርገው ለበቀል ለሚነሳሱ ሰዎች “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ” ብሎ አስተማረን፡፡ ይህም ማለት “ራሳችሁ አትበቀሉ”
ማለቱ ነው፡፡ “በቀል የኔ ነው እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ” እንዲል ጌታችን፡፡(ሮሜ.12፡19) ሌላው ደግሞ በመልክ ወይም ስለወደዳችሁ
እንዳው በከንቱ አትፍረዱ ነገር ግን ከጥፋታቸው ይማሩ ዘንድ ምከሩዋቸው ገሥጾአቸው ሲለን ነው፡፡
ከላይ
በተሰጣቸው ትርጉም ተነስተን ሦስት ነገሮችን እናስተውላለን፡፡ አንደኛው ፍርዳችን ቅን ፍርድ ሊሆን ይገባል ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ
ይቅር ባዮችም ልንሆን ይገባናል፡፡ ሁለተኛው እኛም እናጠፋለንና በቅን ፍርድ ተነሳስተን ለበቀል መዘጋጀት የለብንም ሲለን ነው፡፡
ስለዚህም እርሱ አምላካችን ይቅር እንዲለን ይቅር ባዮች ልንሆን ይገባናል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የመፍረድ ሥልጣኑ ሳይኖረንና መንፈሱም
ሳይሰጠን በመልክ ወይም ስለወደድን መፍረድ የለብንም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከጥፋቱ ይመለስ ዘንድ ልንገሥጸውና ልንመክረው ይገባናል ሲለን
“እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ” አለን፡፡ ይህ ብናጤነው ፍትሕን አስጠብቀን
መመላለስ ይቻለናል፡፡
No comments:
Post a Comment