Monday, December 24, 2012

ወንድሞቼና እኅቶቼ በጋብቻ መነኩሳት ትሆኑ ዘንድ ምኞቴ ነው!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/04/2005
ፍጹም አንድ መሆን፡፡ የራስን አካል የሚያውቁትን ያህል ማወቅ ምንኩስና የሚለውን ቃል ፍቺ ይሰጠናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መንፈሳዊ ጋብቻ የሚለው በመለኮትና በሥጋ መካከል የተፈጸመውንና በልደት የተገለጠውን ተዋሕዶን ነው፡፡ ይህን ጋብቻ ይለዋል፡፡ አንድ ክርስቶስ፣ አንድ ኢየሱስ፣ አንድ የእግዚአብሔር ልጅ፣ እርሱ የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት ነው ይህን ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር የተነሣ በገዛ ሥልጣኑ አደረገው ፡፡ ፍጹም የተዋሐዱ ፈጽሞ የማይለያዩ አንድ አካል ብቻ የሆነ፡፡ መነኮስ ማለትም አንድ ብቻ፤ ብቸኛ ማለት ነው፡፡ሁለቱ አንድ ይሆናሉ” የሚለው ቃል ሲፈጸም አንድብቸኞች ይሆናሉ ግን ሙሉ ናቸው፡

ክርስቶስ በየጥቂቱ አደገ በሠላሳ ዓመቱ ለእርሱ የታጨችውን ሙሽራ ከሚዜው ዮሐንስ መጥመቅ እጅ ተቀበላት፡፡ በመስቀሉም ክርስቶስና ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ጋብቻቸውን ፈጽመው አንድ አካል ሆኑ፡፡ ራስ ክርስቶስ ነው፤ አካሉ ደግሞ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በመስቀሉምሁለቱ አንድ አካል ይሆናሉየሚለው ቃል በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል በጋብቻ ተፈጸመ፡፡
አይሁድ ያላገባ ነገር ግን እድሜው ለጋብቻ የደረሰን ሰው ሙሉ ሰው ብለው አይጠሩትም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲሁ ነው የሚለው፡፡ ሙሉ የሚሆነው ሲያገባ ነው፡፡ ሙሉ ሰው ሲሆን አንድ አዳም ተብሎ ይጠራል፡፡ አዳም የሴትና የወንድ የተዋሕዶ ስም ነው፡፡ ከአዳም ጎን ሔዋን ሳትለይ በፊት አንድ አካል ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ከጎኑ ሔዋንን ፈጥሮ ገለጣት፡፡ መልሶ ግን በጋብቻ አንድ አካል አደረጋቸው ወይም አንድ አዳም ተባሉ፡፡ ስለዚህምእግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ ባረካቸውም ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው፡፡(ዘፍ.51-2) ይህ እንግዲህ ምንኩስና ነው፡፡
በጥልቀት ሲመለከቱትም ሰው የወንዱ ዘርና የሴቲቱ ደም (እንቁላል) ውሕደት ውጤት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ካልሆነ በቀር ፍጥረታዊው ሰው ሰው አልሆነም፡፡ በመንፈሳዊው መልኩ ስንመለከተው ደግሞ መንፈሳዊውን ጋብቻ የመሠረተልን ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ የራሱን መለኮታዊ ባሕርይ ከሥጋ ጋር በማዋሐድ በአዲስ ስምና በአንድ አካል ለእኛ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ፣ አማኑኤል፣ መድኀኒዓለም፣ ዳግማዊው አዳም በመባል ተገለጠልን፡፡ እኛም ክርስቲያኖች ከሁለት አካላት ማለትም ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች ተባልን፡፡ ስለዚህ ፍጥረታዊውም ሰው መንፈሳዊውም ሰው የሁለት አካላት ውሕደት ውጤት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት አካላት ወደ አንድ አካልነት ይመጣሉ፤ ለእኛም ይገለጣሉ እኛም ፍጥረታዊው ሰው እና መንፈሳዊው ሰው እንላቸዋለን፡፡ ከእነዚህ ውጪ ሰው ሰው አይባልም፡፡ ሰው ሲሆን ደግሞ ብቸኛ ይሆናል፡፡ አንድ ነው ከእንግዲህ ሁለት አይደለም፡፡ እድሜው ለጋብቻ ሲደርስ ደግሞ ሙሉ ሰው መሆኑ በሚያገባት ሚስቱ ይወሰናል፡፡ በጋብቻ ከሚስቱ ጋር አንድ ሲሆን ሙሉ ሰው ይባላል ወይም አንድ ሰው ወይም አንድ አዳም ይባላሉ፡፡ በጋብቻ የተገለጠችው ምንኩስና እንግዲህ ይህቺ ናት፡፡

2 comments:

  1. በጣም አሪፍ ጽሁፍ ነው:: ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete