በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን 11/02/2006
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለልደቱ ጥንት
ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ በሥጋ ከመገለጡ በፊት ቅዱስ ዮሐንስ “በዓለምም ነበር ዓለሙ አላወቀውም ነበር” እንዲል በዓለሙ ሙሉ ሆኖ የሚኖር እግዚአብሔር ነው፡፡ አንዳንዶች በዓለም ነበር ሲባሉ ለምድር መነሻ እንዳላት ለእርሱም መነሻ አለው እንዳይሉ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው “ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ብሎ አስቀድሞ ጻፈልን፡፡
በዓለም ነበር ሲልም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛት እርሱ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን በሥጋ ማርያም አስኪገለጥ ድረስ ዓለም አላወቀችውም ነበር፡፡ አይደለንም እኛ መላእክት እንኳ አላዩትም፤ ነገር ግን ለእነርሱ በሰው አምሳያ ይታያቸው ነበረ፡፡ እነርሱም ለእርሱ አምልኮትን
በአምሳያው ፊት ይፈጽሙ ነበር፡፡ እርሱ በሰው አምሳል ለመላእክት ተገልጦ ይታያቸው ነበር እንጂ በፍጹም እርሱነቱ ያልተገለጠ ማንም በማይቀርበው መለኮታዊ ብርሃን ውስጥ የሚኖረው ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱ ስሙ እውነተኛ ብርሃን የሆነ እኛን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ፡፡ ያም ማለት ሰው ሆነ፤ ለእርሱ አንድ ነገርን ለማድረግ መውጣት መውረድ የሚገባው አይደለም፤
ነገር ግን ሰው መሆኑን እንድንረዳ “ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ተብሎ ተጻፈልን፡፡