በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/06/2004
“በጦም ወቅት አንድ ክርስቲያን በፈቃደኝነት አንድ በጎ ሥራን ጎን ለጎን ቢፈጽም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከሰዎች ምስጋናን ወይም አንዳችን
ነገር ሽቶ የሚጦም ከሆነ ግን ጦሙ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይወደድ ጦም ይሆንበታል፡፡ ማንኛውም በጎ ሥራ ስንሠራ ለእግዚአብሔር አምላካችን ካለን ፍቅር የመነጨ ይሁን፡፡
እንዲያ ካልሆነ ግን እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኝ አይቻለንም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ጌታችን በመንጎቹ ላይ ሲሾመው ለእርሱ ያለውን ፍቅር
ተመልከቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን የሚያፈቅር ሰው የሚፈጽማቸው የትኞቹም በጎ ምግባራት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱለት ይሆኑለታል፡፡
ፍጹማንም ናቸው፡፡ ስለዚህም ማንኛውንም በጎ ሥራዎቻችንን ስንሠራ እርሱን በማፍቀር ላይ የተመሠረተ ይሁን፡፡”
“አንድ ሰው ምንም እንኳ መላ የሕይወት ዘመኑን በትህርምት ሕይወት
መምራት ያለበት ቢሆንም በዚህ በዐቢይ ጦም ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃጢአቱን ለካህን ተናዝዞ ለድሆች ምጽዋትን በማድረግ በአግባቡ ሊጦም ይገባዋል፡፡ እነዚህን
ዐርባ የጦም ቀናት በአግባቡ በጎ ሥራዎች አክለንባቸው የጦምናቸው እንደሆነ ቸሩ ፈጣሪያችን ዓመት ሙሉ ባለማወቅ የፈጸምናቸውን ኃጢአቶቻችንን
ይደመስስልናል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ )


