Monday, March 12, 2012

ምጽዋት በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/07/2004 
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር መብራታቸውን ከዘይታቸው ጋር አስተባብረው ይዘው የተገኙት ደናግላን ወደ ሰርጉ እንዲታደሙ እንዳደረጋቸው ገልጦልናል፡፡ በዘይት የተመሰለው ተግባራዊ ምልልሳችን ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር ስም በእኛ ይበልጥ እንዲከብርና እንዲመሰገን ያደርገዋል፡፡ ይህም የጽድቅ ሕይወታችን ለሌሎች ብርሃን ለመሆን እንድንበቃ ያግዘናል፡፡ ስለዚህም ነው ጠቢቡ ሰሎሞን “የጻድቅ መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው” ማለቱ፡፡ (ምሳ.4፡18) መንገድ የተባለው ለክርስቶስ ፈቃድ መታዘዛችን ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ በማለት ያስተምረናል፤
“በመቅረዛችን ውስጥ ዘይቱን በመጨመር መንፈሳዊውን መብራት ደምቆ እንዲበራ እናድርገው፡፡ መሥዋዕት አድርገን የምናቀርበውን መብራት ሰማያዊውን ሙሽራ ለመቀበል የሚያገለግል መሥዋዕት ነው፡፡ እንዲያም ስለሆነ ከመቅረዙ ውስጥ ተጨማሪ ዘይት ሊጨመርበትና እስከ ላይ ደርሶ ሊበራ ይገባዋል፡፡ እንዲህ ካልሆነ መቅረዝ በመያዛችን ብቻ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ዋጋን የምናገኝ አይደለንም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትን አይደለም” ብሎ አስተማረን ፡፡ (ማቴ.12፡7፤ሆሴ.6፡6)

Saturday, March 10, 2012

ለቤተክርስቲያን መሪዎች የቅዱስ ኤፍሬም መልእክት






ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
02/07/2004
ቅዱስ ኤፍሬም በዚህ ጽሑፉ ላይ ቤተ-ክርስቲያን የሚለው እኛን ክርስቲያኖችን ነው፡፡ በእኛ ግንባር ላይ ስንጠመቅ የሥላሴ ስም ተጽፎአል ስለዚህም የክርስቶስ ቤተሰዎች ተሰኝተናል፡፡ በዚህ ስም ላይ ሌላ ስም መለጠፍ ወይም መጨመር ወይም መቀነስ ፈጽሞ የሚገባ ተግባር አይደለም፡፡ እንዲህ ማለት በክርስቶስ የተፈጸመልንን የማዳን ሥራ ዋጋ ማሳጣት ይሆናል፡፡ ምናልባት በቅዱስ ኤፍሬም ዘመን ቤተ ክርስቲያንን በራስ ስም መጥራት ወይም ሌላ ተጨማሪ ስም መስጠት ወይም መቀነስ ታይቶ ይሆናል፡፡ በዚህም ዘመን በራሳቸው ስም ቤተ ክርስቲያንን ከፍተው  እንደግል ንብረታቸው ቆጥረው የሚኖሩ እንዳሉ ከወደ አሜሪካ ይሰማል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ለጭብጡ መነሻ ነጥብ የሚያደርገው ቅዱስ ጳውሎስ “እያንዳንዳቹ ፡- እኔ የጳውሎስ ነኝ እኔስ የአጵሎስ ነኝ እኔ ግን የኬፋ ነኝ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ፡፡ ክርስቶስ ተከፍሎአልን ጳውሎስስ ስለእናንተ ተሰቀለን ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን” (1ቆሮ.1፡12)ብሎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን የጻፈውን መልእክት መሠረት አድርጎ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አንተ በመንጎቹ ላይ የተሾምህ ካህን ሆይ ለጌታህ ሙሽራ የሆነችው ቤተክርስቲያን እነሆ!! እርሱዋን ከክፉ ሁሉ ጠብቃት፤ እርሱዋን በማባበል የራሳቸውን ስም ለመለጠፍ  ከሚተጉትም ተኩሎች ጠብቃት፡፡ የእርሱዋ የሆነው የሙሽራው ስም በላይዋ ላይ ታትሞአልና ሌላ ስም ለእርሱዋ በመስጠት ከሌሎች ጋር ታመነዝር ዘንድ አትፍቀድ፡፡ እርሱዋ የታተመችበት ስም በሩቁ ብእሲ ስም አይደለምና በግንባሯ ላይ የታተመውን ስም በመጥራት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅድስ ማመኑዋን በይፋ ትገልጥ ዘንድ አስተምራት፡፡ በሥላሴ ስም ትጠራ ዘንድ ያበቃሃት ጌታችን ሆይ! ስምህ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የተመሰገነ ይሁን!!!

“ጌታችን መዝጊያህን ዘግተህ…ጸልይ” የማለቱ ትርጉሙ(በአፍርሃት ሶርያዊ)


                 
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
01/07/2004
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎታችን ምን መምሰል እንዳለበት ሲያስተምር “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ በስውር የሚያይህም አባትህ በግልጽ ይከፍልሃል፡፡”(ማቴ፡፮፥፮)ብሎ አስተምሮአል፡፡ ወዳጄ ሆይ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምንጸልይበት ጊዜ “ወደ እልፈኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላላው አባትህ ጸልይ” ማለቱ የመኖሪያ ቤትህን ደጅ ዘግተህ ጸልይ ማለቱ ነውን ? እንዲህ ነው ብለህስ ስለምን ትረዳለህ ? ጌታችን እንዲህ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እስከቻልኩት ድረስ ላብራራልህ እሞክራለሁ፡፡
እርሱ “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ ጸልይ” ሲልህ የልብህን ደጅ በመዝጋት እንድትጸልይ ሲመክርህ አይደለምን ? እኛ ልንዘጋው የሚገባን ጌታ ያዘዘን  በር የቱ ነው ? ቤቱ ሰውነታችን ፣ በሩ ልባችን ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ? ሐዋርያው እንዳለው ሰውነታችን ክርስቶስ የሚኖርበት ቤተመቅደሱ ነው፡፡ እርሱ“ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንደሆነ አታውቁምን?” አላለንምን?(፩ቆሮ.፮፥፲፱፣፳) ወደ ውስጥ ሰውነትህ ወይም ወደ ገዛ ቤቱ ገብቶ ያደር ዘንድ አፍህ ለጸሎት ሳይከፈት አስቀድመህ ማረፊያ ቤቱን ማጽዳት ማስተካከል ይገባሃል ፡፡ መልእክቱ ይህ ካልሆነ በቀር ኃይለ ቃሉ ምን የተለየ ሌላ ትርጉም አለው ? ወይስ አንተ ቤትና በር በሌለበት በምድረበዳ ብትሆን እንዲህ ስለሆነ ለሰማይ አባትህ በስውር መጸለይ አይቻልህም ማለት ነውን ? ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይ አባታችን የልባችንን መሻትና አሳብ እንደሚያውቅ “አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና”(ማቴ፡፮፥፰ )ብሎ አስተምሮናል፡፡