Thursday, July 26, 2012

ቅዱስ ገብርኤል ሆይ እስቲ ልጠይቅህ!


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/11/2004
ዛሬ የጌታችንንና የአፍቃሪያችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክና ግርማ ለብሶ በብሉይ ኪዳን ለቅዱሳን መጽናናትን ይሰጥ የነበረውና(ዳን.10፡5-5 ከ ራእይ.1፡14-16 ካለው ጋር ያነጻጽሩ፤ እንዲሁም ሕዝ. 1፡26 ከ ዳን.8፡15፤9፡21፤10፡18 እንዲሁም 3፡25 ያነጻጽሩ)በሐዲስ ኪዳንም የድኅነት ብሥራትን ይዞ ወንድሞቻችንን መላእክትን ወክሎ እንዲሁም ነፍስን በደስታ በምታስጨንቅ ፍስሐ ተሞልቶ፣(ሉቃ፡15፡10) ወደ ድንግል በመምጣት ሕዝቡን ከኃጢአት የሚያድናቸው የስሙ ትርጓሜ መድኀኒት የሆነውን "ኢየሱስን በድንግልና ጸንሰሽ በድንግልና ትወልጃለሽ"(ሉቃ፡1፡31) ብሎ ያበሠረ የተወዳጁ መልአክ የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ነው፡፡
 ሰውና አምላክ ፍጹም እርቅን የፈጸሙባትን ያቺን ዕለት ሳስባት ነፍሴ በሐሴት ትሰክራለች፡፡ ልጅ ከእናትና ከአባት ጥምረት ይወለዳል ፡፡ ስለዚህ ልጅ የእናትና የአባት ውሕደት አማናዊ መገለጫ ነው፡፡ እንዲሁ እግዚአብሔር አብ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ሊገልጥልን ስለወደደ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን ከድንግል በሥጋ ይወለድ ዘንድ ላከው፡፡  ልጁም ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ ነስቶ በመወለድ ፍጹም እርቅ በሰውና በእግዚአብሔር  መካከል መፈጸሙን በልደቱ አበሠረን፡፡ 
ከአባት አብራክና ከእናት መኀፀን የተወለደን ልጅ አካፍሎ ወደፊት ለአባትና ለእናት መስጠት እንዳይሞከር እንዲሁ እግዚአብሔር ወልድ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከተወለደ በኋላ አምላክ ወሰብእ ተብሎ ይኖራል እንጂ ወደፊት ተከፍሎ የለበትም፡፡

Sunday, July 22, 2012

ሰው ማለት ምን ማለት ነው?


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/11/2004
(ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር የተለቀቀ)
ሰው ማለት ነፋሳዊነት፣ እሳታዊነት፣ ውኃዊነት፣ መሬታዊነት ባሕርያት ያሉት በነፍስ ተፈጥሮውም ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት የሆነች ነፍስ ያለችው ፍጥረት ነው፡፡ እንዲህ ብለን ግን የሰውን ተፈጥሮ ጠቅልለን መናገር አይቻለንም፡፡ ምክንያቱም ሰውን ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ እጅግ ልዩ በሆነ መልኩ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮአልና፡፡ ስለዚህም ቅዱሳን አባቶች ከዚህ በላይ ከሰጠነው ትንታኔ በመውጣት እንዲህ ብለው ሰው ለሚለው ስያሜ ትርጓሜ ይሰጡታል፡፡

Saturday, July 21, 2012

ለፍቅር መምህር የሆነ ፍቅር እና ወዳጄ ሆይ .....


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/11/2004
ጾታዊ ፍቅር በራሱዋ ንጽሕትና ቡርክት እንዲሁም ቅድስት ናት፡፡ በዚህ ፍቅር የወደድካትን ካገኘሃት፤ ይህች ፍቅር በልብህ ውስጥ ርኅራኄን፣ አክብሮትን፣ትዕግሥትን፣ አርቆ አሳቢነትን ስትዘራብህ ታገኛታለህ፡፡ ከአጣሃት ግን ከልብህ ስለማትወጣ እስከ ነፍስህ ህቅታ ድረስ በልብህ ሃዘንን ተክላ ትኖራለች እንጂ ፈጽማ አትጠፋም፡፡ወላጆች ሆይ ልጆቻችሁ ባለገንዘብ እንዲሆኑ ከመድከም ይልቅ ወደ እግዚአብሔር ባሕርይ የምታቀርባቸውን ይህችን ፍቅር በሕይወታቸው አግኝተዋት አእምሮአቸው ብሩህ ሆኖ ፍቅር የሆነውን አምላካቸውን እንዲያውቁትና እንዲያፈቅሩት ለዚህ ሕይወታቸው ትጉላቸው!!! እናንተ በእውነተኛይቱ ፍቅር ተጣብቃችሁ አንድ አካል ወደ መሆን የመጣችሁ ጥንዶች ሆይ! ንጽሕት፣ ቡርክት፣ ቅድስትና የእግዚአብሔር ፍቅር ፍጣሬ ብርሃን በሆነችው በዚህች ፍቅር ታግዛችሁ “ራስን ለሚወዱት አሳልፎ እስከመስጠት ወደሚያደርሰው” የክርስቶስ ፍቅር ታድጉ ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ ለዚህች ፍቅር እንደ መጥምቁ ዮሐንስ አዋጅ ነጋሪዎች ትሆኑም ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ አቤቱ አንተነትህን በዚህች በማንነታችን ውስጥ በጥልቀት በተከልካት ፍቅር እንድናውቅና በእንባ ሆነን በፍቅር እንድናመልክህ ይህችን ፍቅር በተፈጥሮአችን የሠራሃት አንተ ለዘለዓለም የተመሰገንክ ሁን፡፡ በዚህች ፍቅር ጠብን እንድናጠፋትና ፍቅርህን ለብሰን እንድንገኝ ጌታ ሆይ እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡