Thursday, August 16, 2012

አሁን ደግሞ ሹመቱ የካህናት ተራ ቢሆን!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
09/12/2004
ጭንቅ የሆነው የቤተ ክርስቲያን የስደት ዘመን በንጉሥ ቆስጠንጥኖስ እስካበቃበት እስከ3ኛው ክ/ዘመን ድረስ ክርስቲያኖች ፍጹም በሆነ የቅድስና ሕይወት ውስጥ ይመላለሱ ነበር፡፡ በውጭ በአላውያን ነገሥታትና በጣዖት አምልኮ በታወሩ ሕዝቦች እንዲሁም በአይሁድ የሚቀበሉት መከራ እርስ በእርስ ያላቸው ፍቅር እንዲጠብቅና እንዲተዛዘኑ እንጂ ከቅድስና ሕይወታቸው እንዲወጡ አላደረጋቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ከ3ኛ ክ/ ዘመን ጀምሮ በንጉሥ ቆስጠንጥኖስ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት ስትሆንና ነገሥታት በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ሲገቡ ፍጹም የተባለው ክርስቲያናዊ ሥነምግባር እየጎደፈ ሕዝቡም መረን እየለቀቀ ውሻ ወደ ትፋቱ እንዲመለስ ብዙዎች ወደ ቀድሞ ግብራቸው ተመለሱ፡፡

Tuesday, August 14, 2012

እናንተስ ምን ትላላችሁ?

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

08/12/2004

አንባቢው እዚህ ላይ እንዲያስተዋልልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር በሐዲስ ኪዳን ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዴ በመስቀሉ በፈጸመው የድኅነት ሥራ እኛ በጥምቀት ስንተባበርና የተሰጠንን የልጅነት ጸጋችንን ጠብቀን ስንገኝ የምንድን መሆናችንን ነው፡፡ ድኅነቱ አሁን ተሰጥቶናል፡፡ የመዳንና ያለመዳን ምርጫው የተያዘው በእኛው እጅ ነው፡፡  ስለዚህም አንዴ በተቋጨና በተደመደመ ጉዳይ ዙሪያ ነው የምንነጋገረው፡፡ በመሆኑም ይህን ጽሑፍ ሳቀርብም ለእውቀት ያህል ብቻ እንደሆነ አንባቢው እንዲረዳኝ በትሕትና እጠይቃለሁ፡፡    


ነቢዩ ዳዊት ኃጢአት ከእናት ማኅፀን እንደሚጀመር ሲጽፍልን “ኃጥአን ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ፤ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፤ ሐሰትንም ተናገሩ፡፡”ሲለን(መዝ.57፡3-4) ኢዮብ ደግሞ ሕፃናት ገና ከማኅፀን ሳሉ ጽድቅን እንደሚጀምሩ ሲናገር “ደሃውን ከልመና ከልክዬ፣ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደሆነ፤ እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፣ ደሃ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤ እርሱን ግን ከታናሽነቱ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፡፡ እርሱዋንም ከእናቴ መኅፀን ጀምሮ መራኋት”አለን፡፡(ኢዮ.31፡16-18)


Monday, August 13, 2012

የፍቅሩ ድልድይ (በቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/12/2004
መግቢያ
በዚህ ርእስ ግሩም የሆነውን የቅዱስ ኤፍሬም መጽሐፍ ቅዱስን የመረዳት ጸጋውን እንመለከታለን ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ሲናገር  የሰውን ተፈጥሮአዊ ጠባይ በመጠቀም ነበር ፡፡ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ቅዱስ ኤፍሬም ታላቅ ገደል ወይም ጥልቁ ጸጥታ ብሎ ይጠራዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ በሰው ላይ የሚታዩ ተፈጥሮአዊ ጠባዮችን ለራሱ በመስጠት በእርሱና በሰው መካከል ያለውን ሰፊ የሆነ ልዩነት ያጠበበው እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ እንዲህ ማድረጉ ክብር ይግባውና ለሰው ልጆች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሰው የሚሰጠውን መጠሪያና ጠባይ ለራሱ ተጠቅሞባቸው እናገኛቸዋለን፤ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የአጻጻፍ ዘይቤ ደግሞ እንደ ልብስ ለብሶአቸው እናገኛቸዋለን፡፡
በብሉይ ኪዳን በእኛ ምሳሌ በመገኘት ራሱን የገለጠልን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚሰማን ሊያሳውቀን ስለጆሮዎቹ ነገረን፤ እኛን እንደሚመለከተን ሊያስረዳንም ስለዐይኖቹ ጻፈልን፡፡ በዚህ መልክ በምሳሌአችን ተገልጦ እግዚአብሔር እኛን ይመክረናል ይገሥጸናል፡፡ እርሱ በባሕርይው ቁጣና ጸጸት የሌለበት አምላክ ሲሆን ስለእኛ ጥቅም እነዚህንም ግብሮች ለራሱ ሰጥቶ ተናገረን፡፡