Sunday, April 27, 2014

ዘኬዎስ


ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/08/2006

ቅዱስ ኤፍሬም ዘኬዎስ ጌታን ሲቀበል የነበረውን ምናባዊ በሆነ መንገድ እንዲህ ብሎ ጽፎልናል፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት ስዕላዊ አጻጻፍ ስልት የሴማዊያን የአጻጻፍ ስልት ነው፡፡
ዘኬዎስ በልቡ“ ይህን ጻድቅ ሰው በእንግድነት በቤቱ የተቀበለ ሰው ብፁዕ ነው” ብሎ በልቡ ጸለየ፡፡ ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ ጌታ ደግሞ የልቡን ጸሎት ሰምቶ “ዘኬዎስ ሆይ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ” አለው፡፡ ዘኬዎስም በልቡ ሲያመላልስ የነበረውን ጌታ እንዳወቀበት ተረድቶ “ይህ ያሰብሁትን ያወቀ የሠራሁትንስ ሁሉ እንዴት አያውቅ? በማለት ለጌታችን መልሶ “ጌታ ሆይ ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ ማንንም በሃሰት ከስሼ ብሆን ዐራት እጥፍ እመልሳለሁ” አለ፡፡ ጌታውም “ፈጥነህ ውረድ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ብሎ መለሰለት፡፡” በኋለኛው የበለስ ተክል ምክንያት በአዳም በለስ ምክንያት የሚታወሰው በለስ ተረሣ፡፡ ዘኬዎስ በበደሉ ምክንያት “ጌታ ሆይ ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድሆች አሰጣለሁ ማንንም በሃሰት ከስሼ ብሆን ዐራት እጥፍ እመልሳለሁ” በማለቱ ለዚህ ቤት መዳን ሆነለት፡፡
ተቃዋሚዎች በዚህ ሰው እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት  ይደነቁ፡፡ አስቀድሞ ሌባ የነበረ አሁን ግን መጽዋቾች ሆነ አስቀድሞ ቀራጭ የነበረ ዛሬ ግን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ ዘኬዎስ ቅን የሆነውን ሕግ ወደ ኋላ ትቶ ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ላለመስማቱ ምልክት ወደሆነችው ወደማትሰማውና ወደማትለማው ዛፍ ተወጣጣ፡፡

Wednesday, December 11, 2013

በአታ ለማርያም


03/04/2006
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
(በዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተለቀቀ ጽሑፍ)
ሰይጣን በእባብ አካል ተሰውሮ ሔዋንን፤ በእርሱዋም አዳምን በማሳት በእነርሱ ላይ ሞት እንዲሠለጥንባቸው ስላደረገ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደረጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትነድፋለህ”በማለት የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ፈረደበት፡፡ “በአንተ” የተባለው ሰይጣን ሲሆን ፣ “በሴቲቱ” የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት (ገላ.4፡4) ፣ “በዘርህ” ሲል የዲያብሎስ የግብር ልጆችን ሲሆን(ዮሐ.8፡49)፣ “በዘርዋ” የተባለው ክርስቶስ ነው(ገላ.3፡16)፡፡ ትርጉሙ እንዲህ አንደሆነም ወንጌላዊው ዮሐንስ “ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ”አለን፡፡(ራእ.12፡17) እባብ የተባለው ሰይጣን ስለመሆኑም “ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ”(ራእ.12፡9) ብሎ ጻፈልን፡፡

Monday, October 21, 2013

ጌታችን የእግዚአብሔር ምሥጢር የመባሉ ምክንያት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

ቀን 11/02/2006
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለልደቱ ጥንት ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ በሥጋ ከመገለጡ በፊት ቅዱስ ዮሐንስ “በዓለምም ነበር ዓለሙ አላወቀውም ነበር” እንዲል በዓለሙ ሙሉ ሆኖ የሚኖር እግዚአብሔር ነው፡፡ አንዳንዶች በዓለም ነበር ሲባሉ ለምድር መነሻ እንዳላት ለእርሱም መነሻ አለው እንዳይሉ  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው “ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ብሎ አስቀድሞ ጻፈልን፡፡
 በዓለም ነበር ሲልም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛት እርሱ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን በሥጋ ማርያም አስኪገለጥ ድረስ ዓለም አላወቀችውም ነበር፡፡ አይደለንም እኛ መላእክት እንኳ አላዩትም፤ ነገር ግን ለእነርሱ በሰው አምሳያ ይታያቸው ነበረ፡፡ እነርሱም ለእርሱ አምልኮትን በአምሳያው ፊት ይፈጽሙ ነበር፡፡ እርሱ በሰው አምሳል ለመላእክት ተገልጦ ይታያቸው ነበር እንጂ በፍጹም እርሱነቱ ያልተገለጠ ማንም በማይቀርበው መለኮታዊ ብርሃን ውስጥ የሚኖረው ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱ ስሙ እውነተኛ ብርሃን የሆነ እኛን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ፡፡ ያም ማለት ሰው ሆነ፤ ለእርሱ አንድ ነገርን ለማድረግ መውጣት መውረድ የሚገባው አይደለም፤ ነገር ግን ሰው መሆኑን እንድንረዳ “ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ተብሎ ተጻፈልን፡፡