Saturday, January 21, 2012

ስለሦስተኛው ልደት(ጥምቀት) ምን ያህል ያውቃሉ?



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/05/2004
እነኋት ክርስትና ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ
እንደ ሶርያ ቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ ሦስት ዓይነት ልደታት አሉ፡፡ እነርሱም ከሥጋ እናታችን የምንወለደው ልደት፣ ከውኃና ከመንፈስ የምንወለደው ልደት(ይህ በእግዚአብሔር በሆነው ሁሉ ላይ መብትን የሚሰጠን ነው) ሦስተኛውና መሠረታዊው ልደት የፈቃድ ልደት ነው፡፡ ይህ ልደት ሦስተኛው ልደት በመባል ይታወቃል ወይም ሦስተኛው ጥምቀት ይባላል፡፡ ለዚህ ልደት የሚበቃው ሰውነቱን በጥምቀት የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ያደረገ ክርስቲያን ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሲታዘዝ ክርስቶስን ወደ መምሰል ይመጣል፡፡ አንድ ክርስቲያን ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስን ወደ መምሰል ማዕረግ ሲያድግ ሦስተኛውን ልደት ተወለደ ይባላል፡፡ እኛ ክርስቲያኖችም ለዚህ ተጠርተናል፡፡ ለመሆኑ በዚህ በፈቃድ ልደት ውስጥ ያለ ክርስቲያን ላይ የሚንጸባረቁ ጠባያት ምን ምን እንደሆኑ ሶርያዊው ባለራእይው ዮሴፍ የዘረዘራቸውን እንመልከት፡፡


አንድ ክርስቲያን በሰውነቱ ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ ሥራ መጀመሩን የሚረዳው  በልቡ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንደእሳት ሲቀጣጠልበት ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሣ ዓለማትን እንደፈጠረ ወደማስተዋል ይመጣል፡፡ ከዚህም ስ ለእግዚአብሔር ፍቅር ሲባል ለእግዚአብሔር መለየትንና የትርምት ሕይወትን ወደ መምረጥ ይመጣል ፡፡ እነዚህ የመልካም ሥነምግባር እናቶች ናቸው ፡፡ ወንድሜ ሆይ ሁለተኛው መንፈስ ቅዱስ በንተ ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምትገነዘበው እውነተኛ የሆነው ትሕትና በአንተ ሲወለድ ነው ፡፡ እንዲህ ስልህ ለታይታይ በሥጋ የሚገለጠውን ትሕትና ማለቴ ግን አይደለም ፡፡ በእኛ ባደረው መንፈስ ቅዱስ ድንቅ የሆነ ሥራ እየተፈጸመ ነገር ግን ራሳችንን እንደትቢያና አመድ የተናቅን አድርገን የምንቆጥር ፣ ከሰው ተርታ የማንመደብ አድርገን  እንመለከታለን ፡፡ ይህ የነፍስ ትሕትና ነው ፡፡ (መዝ.፳፩፥፮)  በዚህ ዐይነት ትሕትና ውስጥ የሚገኝ ሰው ሰዎች ሁሉ ቅዱሳንና ከእርሱ ይልቅ የከበሩ አድርጎ ያስባል ፡፡ በእርሱ አእምሮ ውስጥ እገሌ መጥፎ ነው እገሌ ደግሞ ደግ ነው የሚል አስተሳሰብ የለም ፡፡ ይህ ፍትሐዊ ነው ያ ግን አይደለም ብሎ በማንም ላይ አይፈርድም ፡፡ ይህን ከመሰለ ትሕትናም ሰላማዊነት፣ የዋሃነት፣ትዕግሥትም ይወለዳሉ ፡፡ ሦስተኛው መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሥራ የመሥራቱ ምልክቱ የእግዚአብሔር አርዓያ ላለው ለሰው ልጅ ሁሉ እጅግ አዛኝ ስንሆን ነው ፡፡ ስለዚህም ለእነርሱ ካለን ፍቅርና አዘኔታ የተነሣ እንባች ጉንጫችንን ሞልቶ ይፈሳል፡፡ የሰው ፍቅር በውስጣችን በመቀጣጠሉ ምክንያት ሰውን ሁሉ እቅፍ አድርገን ጉንን መሳም እንወዳለን ፤ ለሁሉም ሰው ያለንን በልግሥና እንሰጣለን ፡፡ እነርሱን ባስታወስናቸው ቁጥር በመንፈስ ቅዱስ ለእነርሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ ተቀጣጥሎ ይንቀለላል፡፡ ከዚህም ለሰዎች በጎ ማሰብንና ተቆርቋሪት ይወለዳል ፡፡ ስለዚህም ሰውን በንግግር ላለማሳዘን ቃልን መርጦ መጠቀምን እንጀምራለን ፡፡ በልባችን እንኳ ስለሰው ልጆች ክፉ ማሰብን አንፈቅድም ፡፡ ነገር ግን ለሰው ሁሉ በልባችንም በተግባራችንም መልካምን ለማድረግ እንተጋለን፡መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምናረጋግጥበት አራተኛው ምልክት እውነተኛው እግዚአብሔርን መውደድ በሕሊናችን ያደረ ጊዜ ነው ፡፡ በዚህ ወቅት እግዚአብሔርን ከማሰብ አንዲት ቅጽበት አንኳ ማቋረጥ አይቻለንም ፡፡ ይህ የውስጠኛውን የልባችንን በር የሚከፍተው ቁልፍ ነው ፡፡ በዚያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ እልፍኙም ግሩም በሆነው መለኮታዊ ብርሃን ተሞልቶ ከገጽታውም የክብሩ ብርሃን ሲፈልቅ ንመለከታለን
እግዚአብሔርንም በክርስቶስ ከመውደዳችን  የማይታየውን አምላክ የምናይበት እምነት ይወለዳል ፡፡ ይህ እምነት ከአእምሮአችን በላይ የሆነ መረዳትን ስለሚሰጠን በወረቀት ላይ ማስፈር እንቸገራለን ፡፡ እንዲህ ዐይነት እምነትን ቅዱስ ጳውሎስ “ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ብሎ የተናገረለት እምነት ነው ፡፡ ይህ እምነት በሥጋ ዐይናችን የማንረዳው ነገር ግን ለነፍሳችን ዐይኖች በግልጽ የሚታወቅና የሚረዳ ነው፡፡
አምስተኛው መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሰውነት ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምንረዳው አእምሮአችን ፍጽም ብሩህ በሆነ የማስተዋል ብርሃን ሲሞላ ነው ፡፡ በልባችን ጠፈር ላይ የሰንጴር ድንጋይን የመሰለ ሰማይ ተዘርግቶ ከልባችን ጠፈር ልዩ ልዩ ሕብረ ቀለማት ያሉዋቸው ብርሃንት ሲፍለቀለቁ ይታናል ፡፡ እንዲህ ዐይነት ማራኪ የሆኑ ብርሃናት በልቡናችን የሚፍለቀለቁት ሥላሴ በልቡናችን የባሕርይ የሆነውን ብርሃን ሲያበራበት ነው (እውቀቱን ሲገልጥልን ነው)፡፡ በሥላሴ ብርሃን እገዛ የሚኖረን ማስተዋል ፍጥረታዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀውና እንድንረዳው የሚያደርገን ሲሆን ከዚህ አልፈን መንፈሳዊውን ዓለም በጥልቀት እንድንፈትሸው ያደርገናል፡፡ በመቀጠልም ስለእግዚአብሔር ቅን ፍርድና መግቦት ወደማወቅ እንመጣለን ፡፡  ይህ በሂደት ከፍ ከፍ እንድንል በማድርግ ከክርስቶስ የክብሩ ብርሃን ተካፋዮች እንድንሆን ያበቃናል ፡፡ ከዚህ ቅዱስና ግሩም ከሆነው ማዕረግ ስትደርስ እጅግ ውብ አድርጎ በፈጠራቸው ዓለማት በእጅጉ ትደነቃለህ ፡፡ ከእነርሱ የምታገኘው ማስተዋል እጅግ ታላቅ ይሆንልሃል፡፡ በዚህ ድንቅ ከሆነው ከፍታ ላይ ስለሁለቱም ዓለማት መንፈሳዊው እውቀት እንደ ውኃ ሞልቶ ከአንደበት ይፈሳል ፤ የሚመጣውን ዓለም በዚህ ዓለም ሳለን ማጣጣም እንጀምራለን ፡፡ እጅግ ውብ የሆነውን የመላአክትን ማስተዋል ገንዘባችን እናደርጋለን፡፡ ደስታቸውን ፣ ምስጋናቸውን ፣ ክብራቸውን ፣ ዝማሬአቸውን ቅኔአቸውን እንሰማለን፡፡ መላእክትን ከእነማዕረጋቸው ያቸውን ኅብረት እናስተውላለን ፣ ቅዱሳን ነፍሳትን ለመመልከት እንበቃለን ፣ ገነትን ማየትን፣ ከሕይወት ዛፍ መመገብን ፣ ከቅዱሳን ነፍሳትና መላእክት ጋር መነጋገርና ከዚህም ባለፈ ልዩ ልዩ በረከቶችን ለመቀበል የበቃህ እንሆናለን፡፡” ከላይ የጠቀስናቸው ምልክቶች በሰውነታችን መታየት ሲጀምሩ በጥምቀት ያደረው መንፈስ ቅዱስ እኛን ክርስቶስን እንድንመስል እየሠራን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ አምላክ ሆይ ይህ እንዴት ግሩምና ድንቅ የሆነ ልደት ነው!!! አቤቱ አምላካችን ሆይ ለፈቃድህ ታዘን  እኛም በዚህ ልደት ውስጥ እንድንገኝ የበቃን አድርገን ለዘለዓለሙ አሜን!!




2 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ሽሜ። ማንገሰት ሰማያት ያውርሰልን።
    ሙሉጌታ ክቫንኩቨር ደሴት

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይውት ያሰማልን ጸጋውን ያብዛልህ መምህር

    ReplyDelete