Saturday, March 31, 2012

ለአንድ ክርስቲያን የሰንበት ትርጉም


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/07/2004
አንድ ቅዱስ ሰንበትን ግርዘት ብሎ ይጠራታል፡፡ አንድ ጊዜ የተገረዘ ሰው ድጋሚ መገረዝ እንደማያስፈልገው እንዲሁ አንድ ጊዜ የተጠመቀም ድጋሚ መጠመቅ አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ ግርዘት የጥምቀትም ጥላ ነው ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስረዳ “የሥጋን ሰውነት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ”(ቆላ.2፡11)ይለናል፡፡
የተጠመቀ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በሞቱ በመተባበር የቀድሞውን አዳም ቀብሮ ዳግማዊውን አዳም ክርስቶስን ለብሶ ይነሣል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ሲጠመቅ “የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይገባዋል” የሚለው የሐዋርያው ቃል በእርሱ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡(1ቆሮ.15፡45፣52) ትንሣኤአችን ግን የሚተገበረው እኛ በዚህ ምድር ሳለን እንደ ክርስቶስ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ ሕያዋን ሆነን የተመላለስን እንደሆነ ብቻ ነው፡፡


ያለበለዚያ ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሲና በረሃ ሲሳይ ሆነው እንደቀሩት እስራኤላውያን መሆናችን አይቀሬ ነው፡፡ እነርሱ ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በውኃ ተጠምቀው ነበር፡፡ ይከተላቸው ከነበረውም ከመንፈሳዊው ዐለት ጠጡ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በብዙዎቹ ደስ አልተሰኘምና ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገቡ በሲና በረሃ ውስጥ አለቁ፡፡ እንዲሁ አንድ ተጠማቂ ምንም ቢጠመቅ በሥራ ክርስቶስን መስሎ ካልተመላለሰ ሊድን ከቶ አይችልም፡፡(1ቆሮ.10፡1-5)  ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ“ብልቶቻችሁን  የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ፡፡ ኃጢአት አይገዛችሁምና ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና” ማለቱ፡፡(ሮሜ.6፡13-14)
ሰንበት ማለት ደግሞ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ አስተምህሮ ከኃጢአት ተከልክሎና ሕይወትን ለእግዚአብሔር ቀድሶ መኖር ማለት ነው፡፡ ይህን በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት አይተነዋል፡፡ እርሱ ቀንን ሳይመርጥ “አባቴም እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” እንዲሁም “በሰንበት በጎ መሥራት ተፈቅዶአል”(ማቴ.12፡12) በማለት የሰንበትን ትርጉም በተግባርም በቃልም አስተምሮናል፡፡እኛም በጥምቀት"እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ተፈጠርን፡፡"(ኤፌ.2፡9)
ስለዚህም አንድ ክርስቲያን ቀኖቹን ሁሉ ሰንበት ያደርጋቸው ዘንድ ከፈቀደ ሥራዎቹን ሁሉ ከእግዚአብሔር ዋጋ የሚያገኝባቸው አድርጎ ሊቃኛቸው ይገባዋል፡፡ ነጋዴው ደንበኛውን ልክ እንደ ክርስቶስ ተመልክቶ ሳያጭበረብር ሚዛን ሳይሰርቅ ንግዱን ሊፈጽም ይገባዋል፡፡ ከንግዱም በሳምንት እንደቀናው መጠን በማስቀመጥ ነዳያን ራሳቸውን ችለው ከምጽዋት ጠባቂነት የሚወጡበትን ሥራን ሊሠራ፤ ከባልንጀሮቹም ጋር ሆኖ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ሊሰማራ ይገባዋል፡፡(ኤፌ.4፡28፤1ቆሮ.16፡2) ሠራተኛም ለክርስቶስ ሥርዐት እንደሚታዘዝ ቆጥሮ ለአለቃው ሊታዘዝ፤ አለቃም በእርሱ ላይ የሚፈርድ ጌታ እንዳለ በመረዳት በበታቹ ያሉትን ሠራተኞች እንደወንድሞቹ በመመልከት በኃይል ሳይሆን በፍቅር ሊመራቸው ይገባዋል፡፡(ሮሜ.13፡1-2፤ 1ቆሮ.6፡5-9) አባወራም በቤቱ እንደ አባትና ጠባቂ በመሆን ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚመራት እርሱም ቤቱን በፍቅር በክርስቶስ ቃል ሊመራ፣ ነፍሱን እስከ መስጠት ደርሶ ሚስቱንና ልጆቹን ሊወድ ይገባዋል፡፡ ሚስትም እንዲሁ ለእርሱዋ አርዓያ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን መስላ በጌታ ለባልዋ ልትታዘዝ፤ ለልጆቹዋም እንደ ክርስቶስ በመሆን ልታሳድጋቸው ይገባታል፡፡(ኤፌ.5፡21-24) በማኅበራዊ ሕይወታችንም ለማኅበረሰቡ እንደ ካህናት በመሆን በቃላችንም ቢሆን በሕይወታችን አብነት ሆነን በመገኘት ወደ መዳን እውቀት ልናደርሳቸውና እንዲድኑ ልንረዳቸው ይገባናል፡፡(1ጴጥ.2፡9-10)

እንዲህ ካደረግን በእርግጥም በመንፈስ ቅዱስ መገረዝ የልቡናችን የኀጢአት ሸለፈት ተገፍፎ ወድቆልናል፡፡ “ወደ ዕረፍቱ የገባ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ (እንዲህ የሚፈጽም ክርስቲያንም)ከሥራው አርፎአል”(ዕብ.5፡9) ስለዚህም በዚህ ዓለምም ሆነን የትንሣኤን አየር ማሻተት እንጀምራለን፡፡ ከእንግዲህ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደለንምና ጊዜአችንን ሁሉ ለወደደን ራሱን እስከ መስጠት ደርሶ ላፈቀረን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እንቀድስ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለዚህ ክብር እንዲያበቃን ትጋትን በነፍሳችን ውስጥ ይጨምር፡፡ ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን አሜን!!!    

1 comment:

  1. አባወራም በቤቱ እንደ አባትና ጠባቂ በመሆን ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚመራት እርሱም ቤቱን በፍቅር በክርስቶስ ቃል ሊመራ፣ ነፍሱን እስከ መስጠት ደርሶ ሚስቱንና ልጆቹን ሊወድ ይገባዋል፡፡ ሚስትም እንዲሁ ለእርሱዋ አርዓያ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን መስላ በጌታ ለባልዋ ልትታዘዝ፤ ለልጆቹዋም እንደ ክርስቶስ በመሆን ልታሳድጋቸው ይገባታል፡፡(ኤፌ.5፡21-24) በማኅበራዊ ሕይወታችንም ለማኅበረሰቡ እንደ ካህናት በመሆን በቃላችንም ቢሆን በሕይወታችን አብነት ሆነን በመገኘት ወደ መዳን እውቀት ልናደርሳቸውና እንዲድኑ ልንረዳቸው ይገባናል፡፡(1ጴጥ.2፡9-10)

    ReplyDelete