Monday, April 2, 2012

ጦምን እንዲህ ብንረዳውስ?


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
25/07/2004
ምግብ ለሰው ልጆች በሕይወት መቆየት መሠረታዊ ነገር ሆኖ መቆጠር የጀመረው ከውድቀት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን እንዲያ  አልነበረም፡፡ የቀደመው የአዳምና የሔዋን ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መረዳት እንችላለን፡፡ እርሱ ምንም እንኳ የእኛን ተፈጥሮ ገንዘቡ ያደረገ ቢሆንም እንዲያ በመሆኑ ምክንያት ልክ እንደ እኛ በሕይወት ለመቆየት ምግብ አላስፈለገውም፡፡ እንዲህ ስል ግን የእርሱን አምላክነት ዘንግቼው ሳይሆን የአዳምና የሔዋን በገነት የነበራቸውን ሕይወት ለማስረዳት ከእርሱ የተሻለ ማሳያ ስለሌለ ነው፡፡
አዳምና ሔዋን ከውድቀት በፊት በገነት ሳሉ በገነት ካሉ ፍራፍሬዎች ይመገቡ ነበር እንጂ በሕይወት መቆየታቸው በእነርሱ ላይ የተመሠረተ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከውድቀት በኋላ ሕይወታችን ከሆነው በአፍንጫችን እፍ ተብሎ ከተሰጠን መንፈስ ቅዱስ ስለተለየን መጽናናታችንና በሕይወት መቆየታችን በምግብ ላይ ተመሠረተ ሆነ፡፡

በእርግጥም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሳቱ ምክንያት ዳግማዊ አዳም ተብሎአል፡፡ ስለዚህም ቀዳማዊው አዳም በገነት ስለነበረው ሕይወት ምስክሩ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እኛም በክርስቶስ ሕያዋን የተባልን ክርስቲያኖች በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቀደመው አዳማዊ ባሕርያችን ተመልሰን በሕይወት ለመቆየት ምግብና መጠጥ መሠረታዊ ነገሮቻችን መሆናቸውን አስቀርተናል፡፡ ስለዚህም ይሆናል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን ምንስ እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና፡፡ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል”(ማቴ.6፡31-33) ብሎ ማስተማሩ፡፡
አሁን እኛ ክርስቲያኖች ሕይወታችን የሆነው መንፈስ ቅዱስ በዚህ ምድር ሳለን ከእኛ እንዳይለይ ምን በጎ ሥራ ብንሠራ ነው ደስ ልናሰኘው የምንችለው? የሚለው ነው እንጂ የሚያስጨንቀን፤ ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ ከሰዎች፤ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች፤ ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው፤ የተረፋቸውን ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ”(መዝ.16፡14) እንደተባለላቸው ኢጥሙቃን ስለምንበላው፣ ስለምንጠጣው፣ ስለምንለብሰው፣ ከዚህም አለፍ ሲል ስለትዳራችንም ቢሆን ምክንያቱም ጌታችን “ነገር ግን ልባቹ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”(ሉቃ.21፡34)ብሎአልና  ከመዳናችን ይልቅ ስለእነርሱ አንጨነቅም፡፡    
በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ምግብን ልንበላ በተቀመጥን ጊዜ ሁሉ በመብል ምክንያት ሕይወታችን ከሆነው መንፈስ ቅዱስ ተለይተን እንደነበርንና በዚህ ምክንያት ሕይወታችን መራራ እንዳትሆን እግዚአብሔር ከምንበላው ምግብ ሕይወታችን ለምልማ እንድትጽናና ማድረጉን እናስባለን፡፡ ወደ ክርስትና እምነት ላልመጡት ግን አሁንም መጽናኛቸው ምግባቸው ነው፡፡
 ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች በሕይወት ለመቆየት መሠረታዊ ነገር ምግብና መጠጥ እንዳልሆነ፣ አዳም በገነት ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ይኖር እንደነበረ እንጂ ምግብና መጠጥ በሕይወት ለመቆየት መሠረታዊ ነገሮች እንዳልነበሩ ለማሰብ፤  እንዲሁም ከውድቀት በፊት የነበረውን የአዳምና የሔዋንን ሕይወት በዚህ ምድር ሆነን ለማጣጣም ስንል ከሌሎች ምክንያቶቹ በተጓዳኝ ጦምን እንጦማለን፡፡ ይህ የጦም ሕይወት እንዴት ድንቅ ነው! ገና ከሥነፍጥረት ምግብ ለመኖር መሠረታዊ ነገር እንዳልነበረ በትንሣኤም መንፈስ ቅዱስ በሚሠጠን ሕይወት እንደምንኖር ጦም ለእኛ አስተማሪያችን ሆነን፡፡ ላልተወን ለወደደን አምላካችን ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!   

2 comments:

  1. It was long ago since I became far from Internet access as you might guess. today I selected this article to read. though it is short it is good article. keep on writing. you will discover a lot and become very near to our Lord then we will benefit such articles in words. But never forget to give attention what our former ethiopian fathers also left for us. we are not only the children of those fathers in blood but also in spirit from them lord.

    ReplyDelete
    Replies
    1. ደቤ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ያልከኝንም ለመፈጸም እሞክራለሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

      Delete