Tuesday, April 3, 2012

ማርታና ሞቤድ


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/07/2004
ሞቤድ ፋርሶች ሶርያን በተቆጣጠሩበት በ4ተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የዞሮአስትራኒዚም እምነት ተከታይና ፈራጅ ዳኛ ነው፡፡ ማርታ ደግሞ እርሱ በዳኝነት በተሰየመባት ከተማ ትኖር የነበረች በጥንታዊያን የሶርያ ክርስቲያኖች ዘንድ “የቃል ኪዳን ልጆች” ተብለው ከሚጠሩት ወገን ነበረች፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለእርሱዋም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰማዕትነት የምትቀበልበት ጊዜው ደርሶ ኖሮ ይህ የከተማዋ ዳኛ ወደ እርሱ አስጠርቶ እንዲህ ብሎ አስጠቅቆ ተናገራት፡-
 “አንቺ ሴት እኔ የምልሽን ብቻ ልብ ብለሽ አድምጪ፤ ምኞትሽን ተከትለሽ እኔ የምልሽን ከመፈጸም እንዳትዘገዪ ተጠንቀቂ፡፡ በእምነትሽ ትኖሪ ዘንድ አልከለክልሽም፤ እምነትሽን በተመለከተ እንደ ፈቃድሽ ማድረግ ትችያለሽ፡፡  ነገር ግን እኔ የማዝሽን ብቻ ፈጽሚ፤ እኔ የምልሽን የፈጸምሽ እንደሆነ ከሞት ቅጣት ትድኛለሽ፡፡ ማርታ ሆይ ይህ “ቃል ኪዳን” የምትይውን የማይረባ ነገርሽን ትተሽ ገና ወጣትና መልከ መልካም ሴት ነሽና ባል ፈልገሽ አግቢ፤ ሴቶች ልጆችንና ወንዶች ልጆችን ወልደሽ ኑሪ” ብሎ አዘዛት፡፡
ጥበብን የተሞላች ማርታም እንዲህ ብላ መለሰችለት “አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ከታጨች በኋላ አንድ ሰው መጥቶ እጮኛዋን ገድሎ የታጨችይቱን ድንግል ሊነጥቅ ወይም ከእጮኛዋ ውጪ ይህቺ ሴት ሌላ ወንድ ልታገባ ሕጉ ይፈቅዳልን? ብላ ጠየቀችው፡፡ ሞቤድም  “አ…ይ በፍጹም!” ብሎ ይመልሳል፡፡ ራሱዋን ለክርስቶስ ያጨች ማርታም “እንዴት ታዲያ አንተ እጮኛዬ ያልሆነውን እንዳገባ ታዘኛለህ፤ እኔ ለአንድ ሰው የታጨው ድንግል ነኝና” አለችው፡፡ ሞቤድም በመገረም “በእርግጥ አንቺ እጮኛ አለሽን? ብሎ ይጠይቃታል፡፡ ክብርት ማርታም “እኔ ለእውነት የታጨው ድንግል ነኝ” ብላ ትመልስለታለች፡፡ እርሱም መልሶ “ለማን?” ብሎ  ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም “እርሱን ታውቀው ዘንድ አንተ የሚገባህ አይደለህም” ብላ ትመልስለታለች፤ “እሺ የት ነው ያለው?” ብሎ መልሶ ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም “ለንግድ እሩቅ ሀገር ሄዷል፤ ነገር ግን የመመለሳሻው ቀን ስለተቃረበ በቅርቡ ይመጣል፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡ ሞቤድም በመልሱዋ በመደነቅ “ስሙ ማን ይባላል? አላት፡፡ እርሱዋም “ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ” ይባላል ብላ መለሰችለት፡፡
ይህን ሁሉ ስትናገር ግን ሞቤድ ስለክርስቶስ እየነገረችው እንደሆነ አላስተዋለም ነበር፡፡ “የት ሀገር ነው ለንግድ የሄደው የሀገሪቱ ከተማስ ማን ትባላለች? ብሎ መጠየቁን ቀጠለ፡፡ እርሷም “ሀገሩ በሰማያት ነው፤ እርሱ ያለባትም ከተማ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ትባላለች” አለችው፡፡ በዚህን ጊዜ ዞሮአስትራናዊው ሞቤድ ስለጌታችን ስለመድኃኒታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ እየነገረችው እንደሆነ ተረድቶ ልቡ በቁጣ ነደደ፡፡ በቁጣም ገንፍሎ በዙሪያው ላሉት መሰሎቹ “አስቀድሜም እነዚህ ሰዎች ግትሮች ናቸው ብያችሁ ነበር ለእነዚህ ተለሳልሶ መናገር ስንፍና ነው፡፡”ብሎ ከደነፋ በኋላ ወደ እርሱዋ ተመልሶ “አንቺን ከራስሽ እስከ እግር ጥፍርሽ ድረስ በሰይፍ ቆራርጬ ከገደልኩሽ በኋላ ያኔ እጮኛሽ መጥቶ ከትቢያና ከቆሻሻ ውስጥ ፈልጎሽ በማግኘት ያገባሽ እንደሆነ እናያለን” ብሎ ዝቶ ተናገራት፡፡ ማርታም በድፍረት “በእርግጥም እርሱ በታላቅ ክብር ይመጣል፡፡ ለእርሱ የታጩትን ከትቢያ ለይቶ ያስነሣቸዋል፡፡ በሰማያዊ ጠልም ንጹሐን ያደርጋቸዋል፤ የደስታንም ዘይት ይቀባቸዋል፤ የሰርግ ቤቱ ወደሆነችው በሰው እጅ ወዳልተሠራች ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም አስገባቸዋል”ብላ መለሰችለት፡፡ እርሱም አሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ሰውነቱዋን ሁሉ በሰይፍ ቆራርጠው እንዲገድሉዋት ጭፍሮቹን አዘዛቸው፡፡ እነርሱም እንደታዘዙት ፈጸሙባት፡፡ እርሱዋም ሰማዕትነት በዚህ ጨካኝ ዳኛ ተቀብላ በሰማያት ወደ ተሰበሰቡት በኩራት ማኅበር ገባች፡፡ እነሆ አሁን በነፍሱዋ የሚወዳትን አምላኩዋን እያመለከች ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከአእላፋት መላእክት፤ ከቅዱሳን ነፍሳት ሁሉ ጋር በፍጹም ደስታና ደኅንነት ትኖራለች፡፡”
ጥያቄው ግን እኛስ ለክርስቶስ የታጨን ደናግላን አይደለንምን? የሚለው ነው፡፡ ጥንቱን መጠመቃችን እንደ አምስቱ ደናግላን መብራታችንን ከዘይታችን ጋር ይዘን ማለትም መልካም ሥራን ከፍቅር ጋር፣ ንጽሕናን ከምጽዋት ጋር አስተባብረን በመያዝ የጌታችንን መምጣት በትጋት እንጠባበቅ ዘንድ አይደለምን?
ቅዱስ ጳውሎስ በትዳር የተሳሰሩ ባልና ሚስት በራሳቸው አካል ላይ ሥልጣን እንደሌላቸው ገልጦ ጽፎልናል፡፡(1ቆሮ.7፡4) በዚህ ምሳሌ እኛም ለክርስቶስ ታጭተናል፡፡(2ቆሮ.11፡2) ስለዚህም ይህ ሐዋርያ “ሥጋ ግን ለጌታ ነው …. ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? ብሎ ተናገረ፡፡ በመሆኑም የኃጢአት ፈቃድ ከውስጣችን መንጭቶ ሊያሳድፈን ሲነሣ ይህ አካል እኮ የኔ አይደለም፤ የብርቱው ንጉሥ የክርስቶስን አካል ነው ብለን የኀጢአትን ፈቃድ ልንቃወም ይገባናል፡፡ በዝሙት ሊያረክሰን የመጣውን ሰውንም ልክ እንደ ማርታ አካላችን የክርስቶስ እንጂ የእኛ እንዳልሆነ ገልጠን እንነገረውና እንደአመጠጡ እንመልሰው፡፡ በእግጥም በዋጋ ተገዝተናልና የእኛ አይደለንም፤ ስለዚህ በሥጋችን እግዚአብሔርን እናክብረው፡፡ (1ቆሮ.6፡13-20)ሁል ጊዜም ለአእምሮአችን ሰውነታችን የእኛ እንዳልሆነ የንጉሥ እልፍኝና የመንፈሱ ቤተ መቅደስ እንደሆነ እንገረው፡፡ ለልጆቻችንም ሰውነታችውን ከኃጢአት እንዲጠብቁ “ሰውነታችሁ የእናንተ እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ ተጠምቃችሁ በሁሉ ሥፍራ ለሚገኘው ለክርስቶስ ሆናችኋልና ጌታ በእናንተ ላይ እንዳይቆጣ ራሳችሁን ከነውር ሁሉ ንጹሐን አድርጉ” ብለን እንምከራቸው፡፡ ሰውነትን የሚያረክሱ ኃጢአቶች ምን ምን እንደሆኑ ገልጠን እናስረዳቸው፡፡
ጌታ ሆይ! ይህን ልዩ የሆነ ክብር ያጎናጸፍከን ላንተ ክብር ይሁን፤ ነገር ግን እኛ በደምህ ዋጅተህ፣ ከጎንህ በፈሰሰው ውኃ አንጽተህ የራስህ ያደረግኸውን ይህን ሥጋችንን በመተላለፋችን አሳደፍነው፡፡ ጌታ ሆይ! ለዚህ መተላለፋችን ይቅር በለን፤ በንስሐ አንጻን፣ ቀድሰንም፤ ዳግም ወደዚህ ታላቅ በደል እንዳንገባ ማስተዋልን አድለን፤ እኛም ስላንተ ያለን መረዳት ታላቅ እንዲሆንልን እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን!!!   
   
  

2 comments:

  1. በመሆኑም የኃጢአት ፈቃድ ከውስጣችን መንጭቶ ሊያሳድፈን ሲነሣ ይህ አካል እኮ የኔ አይደለም፤ የብርቱ ንጉሥ የክርስቶስን አካል ነው ብለን የኀጢአት ፈቃዳችንን ልንቃወመው ይገባናል፡፡ በዝሙት ሊያረክሰን የመጣውን ሰውንም ልክ እንደ ማርታ አካላችን የክርስቶስ እንጂ የእኛ እንዳልሆነ ገልጠን እንንገረውና እንዳመጠጡ እንመልሰው፡፡ በእግጥም በዋጋ ተገዝተናልና የእኛ አይደለንም ስለዚህ በሥጋችን እግዚአብሔርን እናክብረው፡፡ (1ቆሮ.6፡13-20)ሁል ጊዜም ለአእምሮአችን ሰውነታችን የእኛ እንዳልሆነ የንጉሥ እልፍኝ እንደሆነ፣ የመንፈሱ ቤተመቅደስ እንደሆነ እንገረው፡፡ ልጆቻችንንም ሰውነታችውን ከኃጢአት እንዲጠብቁት “ሰውነታችሁ የእናንተ እንዳልሆነ ልብ በሉ

    ReplyDelete
  2. kale hiwot yasemaln !!!YE martan yemesele be krstos fker yetemolach hiwot yadlen. manachinm yersachn endalhonn enreda bewaga tegeztenal ena !!!

    ReplyDelete