Friday, September 28, 2012

ስለንስሐ የተላከ መልእክት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/01/2005
ውድ እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን ሕብረት በእጅጉ የምናፍቅልህ ወገኔ ሆይ እንደምን አለህልኝ? ውድ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ ንስሐ ማለት ሕመምን ለዶክተር እንደ መናገር ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ሕመሙን ቢደብቅ ሕመሙ ወደማይደን ደረጃ ይለወጥና ነፍሱንም ሥጋውንም ያጠፋል፡፡ እንዲሁ በንስሐ መድኀኒትነት ከኃጢአት ቁስል ራሱን የማይፈውስ ክርስቲያንም ነፍሱንና ሥጋውን በገሃነም እሳት ያጠፋል፡፡ ውድ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ! በክርስቶስ አምላክነት አምነን በመጠመቃችን ክብር ይግባውና ሁላችንም የክርስቶስ ወታደሮች ሆነናል፡፡ ስለዚህም ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ፍልሚያ ልንቆስል እንችላለን፡፡ አንድ ቁስለኛ ደግሞ የሐኪም እርዳታ በእጅጉ ያስፈልገዋል፤ ያለበለዚያ ሕመሙን ቢደብቅ ቁስሉ ወደ ጋንግሪንነት ተለውጦ የማይድን ይሆንና በሞት ይወሰዳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰው አንዴ ሞቷልና ሊድን አይችልም፡፡ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ! ኃጢአት ለነፍሳችን እንደ በሽታ ነው፡፡በሽታ ጋር ደግሞ እንዲኖር የሚፈቅድ ሰው የለም፡፡ ስለዚህ ወደ ነፍሳችን መድኃኒት ወደ ክርሰቶስ ቅረብ፡፡ እርሱ ሕመምተኞችን እንጂ ጤነኞችን ሊፈውስ አልመጣምና፡፡(ማቴ.912) 
ወገኔ ሆይ ንስሐ ለመግባት አትፍራ፡፡ ወደ ካህን ስትቀርብ ወደ ክርስቶስ እንደቀረብክ ተረዳ፤ በእነርሱ አድሮ ይቅር የሚለን እርሱ ነው፡፡ ይህንን በምን እናረጋግጣለን ካልከኝ? ከታች እንደሚከተለው በጥቅስ አስደግፌ አቅርቤልሃለሁ፡፡

Monday, September 24, 2012

መስቀል ለእኛ ኦርቶዶክሳውያን



በዲ/ን ሽመልስ መርጊ
14/01/2005
ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር የተለቀቀ
መስቀል ለእኛ ኦርቶዶክሳውያን ልዩ የሆነ መንፈሳዊ አንድምታ አለው፡፡ በመስቀሉ እነሆ አሮጌው ሰዋችንን ሰቅለን ከጐኑ በፈሰሰው ውኃ በጥምቀት በመቅበር አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሰን ተነሥተናል(ኤፌ.422-24)፡፡ 
 በመስቀሉ እርግማናችን ተወግዶ የኃጢአት ስርየትን አግኝተናል፡፡ በመስቀሉ ላይ ከተሰዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በመመገብ ከሚያፈቅረን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፍጹም የሆነ ተዋሕዶን መሥርተናል(ማቴ.2626) እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ የሆንበት ሰማያዊ ማዕዳችን በመስቀሉ ላይ የተሠዋው መሥዋዕት ነው፡፡ (ዮሐ.656) 
በመስቀሉ በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት በእኛ ላይ ጸንቶ የነበረው የፍርድ ትእዛዝ ተሽሯል፡፡(ቆላ.214) በብሉይ ለሙሴና ለእስራኤል ዘሥጋ እግዚአብሔር አምላክ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ባለችው የቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ  ሆኖ በደመና አምድ ይገለጥላቸው ነበር፡፡(ዘጸአ.339) ቢሆንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የምታገባዋ ጎዳና ተዘግታ ነበር፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፤ እርሱም ስለ ራሱና ስለሕዝቡ ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳየናል”(ዕብ.96-) ብሎ ተናገረ፡፡


Monday, September 17, 2012

ቅርብኝ ቅርብኝ


ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/01/2005

እናንተዬ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስፈልጋት እንደው አሻጉሊት የሚሆን ራስ ነው እንዴ? ይህ እኔን እጅግ ያንገሸገሸኝ እኔን ብቻ ሳይሆን መላው ምእመናንን ያስመረረ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እኛ የምንፈልገው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና የሰው ኃይል በአግባቡ ተጠቅሞ በመንፈሳዊውም በኢኮኖሚያዊም መስክ ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ የሚያበቃ በሳል ሊቀጳጳስ ነው ነገር ግን አሁንም እንደቀድሞው አሻጉሊት የሆነ ራስ ራስ ሊሆን ከመጣ ራስነቱ ለራሱ ይሁን እኔ ግን ቅርብኝ ብያለሁ፡፡ በቃኝ

ቅርብኝ ቅርብኝ
ራስ እኔነቴን ካዋረደ፤
እፍረትን በእኔ ላይ ካንጓደደ፤
እኔስ እንዴት ላክብረው ራሴን?
ቁልቁል ከጣለው ማንነቴን?
እረ ወዲያ በቃኝ ራስነቱ ይቅርብኝ፤
ጡረተኛን ጣሪ አካል ካደረገኝ፤
ካልጠቀመኝ ራስነቱ፤
ካልረባን አክሊልነቱ፤
እረ ወዲያ ይቅርብኝ፤
ራሱ ገምቶ አካሌን አያግማው፤
ራሱ ያመጣውን ራሱ ይወጣው፤
በሕሊናዬም አይታሰብ ስም አጠራሩም አይታወስ፤
ሰላሜን አይንሳ ብስጭቴን አይቀስቅስ፡፡
ግና እግዚአብሔር በእርሱ ከነገሠ ፤
ነፍሱን ለጌታው ፈቃድ ካፈሰሰ፤
ይምጣ ይግባ ራስም ይሁነኝ፤
በርቶ ያድምቀኝ ሞቆ ያሙቀኝ፤
ሕያው ሆኖ ያኑረኝ ብርሃንን ያልብሰኝ፤
ያለበለዚያ ወዲያ ወዲያ ክላልኝ አትምጣብኝ፡፡
ጫንቃዬ ሰልችቶአል ጡረተኛን ማዘል፤
እሹሩሩ ማለት ጡጦ እየሰጡ ማባበል፡፡

Saturday, September 15, 2012

ክርስትና ማለት እነኋት፡-


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/01/2005
ክርስትና በመንፈስ ቅዱስ እገዛ የሚረዱዋት እምነት ናት፡፡ ብዙዎች ግን በአእምሮ ጠባያቸው ተደግፈው ክርስትናን ከተፈጥሮአዊ ሥርዐት ጋር አቆራኝተው ለመረዳት ሲሞክሩ ከክርስትና ጽንሰ ሐሳብ ሳቱ፡፡ ነገር ግን ክርስትናን ሊረዳት የሚፈለግ ካለ እነኋት፡-  እግዚአብሔር በዘመን ፍጻሜ ያደርግ ዘንድ ያለው አሳቡ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ስለሆነ(ኤፌ.110)ሁሉን ወደ ራሱ ሊያቀርብ ከዚያም ሲያልፍ ሊያዋሕድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት እናታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሳት ሰው ሆነ፡፡ በመስቀሉ በፈጸመው የማዳን ሥራ ሁሉንም ወደ እርሱ አቀረባቸው፡፡(ዮሐ.12፡32)
ስለሆነም በእርሱ ያመንን እኛ ክርስቲያኖች በጥምቀት ከሞቱ ጋር በመተባበር በእምነትም ከትንሣኤው በመካፈል አሮጌውን ሰው ቀብረን አዲሱን ሰው ለብሰን ተነሥተናል፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ጌታችን ለዚህ ዓለም የሞትን ስንሆን በትንሣኤው ደግሞ ሕያዋን ሆነን ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጋር አንድ ቤተሰብ ሆነን እየኖርን እንገኛለን፡፡ ይህን በፍጥረታዊው አእምሮ ጠባይ ለመረዳት እጅግ የሚከብድ ነው፡፡ ይህን እምነት አለኝ የሚልና በጥምቀት ከክርስቶስ ሞት ጋር የተባበረ ክርስቲያን ብቻ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው መረዳት የሚገነዘበው እውነት ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “እኔ ግንድ ነኝ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ” አለን፡፡ በዚህ መልክ ከእርሱ ጋር ካልተባበርን በቀር ስለሰማያዊቱ ዓለም ምንም ዐይነት እውቀት አይኖረንም፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኒቆዲሞስን "ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለድክ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ልታይ አትችልም አለው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ያለእርሱ በጎ መሥራትም መዳንም አይቻለንም፡፡(ዮሐ.155-6)

Thursday, September 13, 2012

ከራኬብ ምን እንማራለን? እስቲ እንወያይ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊ
03/01/2005
ወገኖቼ እስቲ ዛሬ ይክበር ይመስገንና የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅም ቅም አያት ስለሆነችው ስለራኬብ ትንሽ እንወያይ፡፡ ራኬብ ቤቱዋን በኢያሪኮ ቅጥር ላይ ሠርታ በሴተኛ አዳሪነት ብዙዎችን ታወጣና ታገባ የነበረች በዚህም ቤተሰቡዋን የምትመራ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ግብጻውያንን በበረታ ክንዱ እንዳጠፋቸው በተረዳች ጊዜ የእስራኤላውያን አምላክ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ የተገነዘበች ሴት ነበረች፡፡ ይህች ሴት ኢያሱ ኢያሪኮን ይሰልሉ ዘንድ የላካቸውን ሁለት ሰላዮችን በቤቱዋ የተቀበለችና እነርሱን ከሚያሳደዱ ወታደሮች በመሸሸግ ያዳነቻቸው ሴት ነበረች፡፡ እንዲህም ማድረጉዋ በእምነት የእስራኤል አምላክ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ስለተረዳች እርሱዋንና ቤተሰቡዋን ለማትረፍ ስትል የፈጸመችው ነበር፡፡ ኢያሪኮ በእስራኤላውያን ከጠፋች በኋላ ግን ሰልሞን ሚስቱ አድርጎ አገባት፡፡ ከእርሱዋም ቦኤዝን ወለደ ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ እሴም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ፡፡ ከዳዊት ወገን ከሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያምም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ አዳነን፡፡