Friday, August 16, 2013

የሙታን ትንሣኤና የጥምቀት ፍሬ እንዲህ ነው (1ቆሮ.15፡45-50)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/12/2005 ዓ.ም
ቅዱስ ጳውሎስ “የሙታን ትንሣኤ እንዲህ ነው፡-” በማለት  ትንሣኤችንን ከለበስነው ሰማያዊ አካል ማለትም በጥምቀት ከለበስነው አዲስ ተፈጥሮ ጋር አዛምዶ ሂደቱን እንዲህ ይገልጥልናል፡፡ “በመበስበስ ይዘራል” ይህ አስቀድመን ስለለበስነው በዘር በሩካቤ ስላገኘነው ሰውነት ሲናገር ነው፡፡ ይህ አካል ሟችና በስባሽ አካል ነው፡፡ ስለዚህም “በመበስበስ ይዘራል” ያም ማለት ይሞታል፡፡ ይህም ስለትንሣኤችን ሊናገር እንደ መንደርደሪያ ያነሣው ነጥብ ነው፡፡ ሲቀጥል “ባለመበስበስ ይነሣል” ይላል፡፡ ይህ ቃል የሰውን ሁሉ ትንሣኤ ይናገራል እንጂ የክርስቲያኖችን ትንሣኤ ብቻ የሚናገር አይደለም፡፡ በትንሣኤ የሰው ዘር ሁሉ ለፍርድ ይነሣል፤ ዘለዓለማዊ ደስታን ወይም ዘለዓለማዊ ኩነኔን በኃጥአንና በጻድቃን ላይ በሚፈርደው በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ቆሞ ይቀበላል፡፡(2ቆሮ.5፡10) ይህም አንዱ ለጽድቅ አንዱ ለኩነኔ መነሳቱን የሚገልጥ ነው፡፡
ቀጥሎ ግን በእውነት ክርስቲያን ለሆኑት ወገኖች የተሰጠው ትንሣኤ ምን እንደሚመስል ያስረዳል፡፡ ምክንያቱም በጥምቀት አዲሱን ሰው ብንለብሰውም ተመልሰን ለኃጢአት ባሮች ከሆንን በጥምቀት አዲሱን ሰው በመልበሳችን አንዳች ዋጋ እንደሌለን አስቀድሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናልና “ወንድሞች ሆይ” ይለናል “ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ” አለን፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያላቸው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እንደሆነ አንባቢው ልብ ሊል ይገባዋል፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከጣዖት አምልኮ ወደ እግዚአብሔር አምልኮ የመጡ ናቸው ወይም አሕዛብ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ለእነርሱ “አባቶቻችሁ ናቸው” ያላቸው እስራኤላዊያንን እንደሆነ አስተውሉ፡፡

 ይህ እንዴት ሆነ ? ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ይመልስለታል፡፡ “እነዚህ ከእስራኤል የተወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉምና የአብርሃምም ዘር ስለ ሆኑ ሁላቸው ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን በይስሐቅ ዘርህ ይጠራልሃል ተባለ፡፡ ይህም የተስፋ ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ እነዚህ የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው፡፡” ይህ እንግዲህ የሚያሳየን እስራኤላዊና የአብርሃም ልጆች ወይም የእግዚአብሔር ልጆች ለመባል የግድ በሥጋ እስራኤላዊ ወይም ከአብርሃም ዘር መወለድን የማይጠይቅ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን በእምነት አብርሃምን የመሰሉ እስራኤላዊያን ናቸው ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለዋል፡፡ በመሆኑም “እነዚህ በሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው ብሎ” ጻፈልን፡፡ አሕዛብም በእምነት አብርሃምን ቢመስሉ እስራኤላዊና የአብርሃም ልጆች በመባል የእግዚአብሔር ልጆች እንዲባሉ ቅዱስ ጳውሎስ አስከትሎ “…. ነገር ግን ከአሕዛብ የጠራን እኛ ነን፡፡ እንዲሁ ደግሞ በሆሴዕ፡- ሕዝቤ ያልሆነውን ሕዝቤ ብዬ ያልተወደደችውን የተወደደች ብዬ እጠራለሁ፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ”(ሮሜ.9፡6-8፣25) ብሎ አብራርቶ ጻፈልን፡፡
 ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን “ወንድሞች ሆይ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ አባቶቻችን ከደመና በታች ነበሩ” ብሎ በእምነት ሙሴን የተከተሉትን እስራኤላዊያን ለእነርሱ አባቶች እንደሆኑ ገለጠላቸው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ አባቶች ጉደለት ነበር፡፡ ምንም ሙሴን በእምነት ቢተባበሩትና ለጊዜው ለቃሉ ታዘው ከግብጽ ባርነት ቢወጡም እስከ መጨረሻው በጽድቅ ሕይወት አልጸኑም ነበር፡፡
 ስለዚሀም “ሁሉም በባሕሩ መካከል ተሻገሩ” አለን፡፡ እስራኤላዊያን የኤርትራን ባሕር ሳይሻገሩ ወደ ምድረ ርስት እንዳልገቡ እንዲሁ እኛም ካልተጠመቅን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አንገባም፡፡ እንደውም ጌታችን ኒቆዲሞስን “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም”(ዮሐ.3፡5) ማለቱን እናስታውሳለን፡፡ አስቀድሞም ቢሆን “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ብሎ ተናሮታል፡፡(ዮሐ.3፡3) ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ” አለን፡፡ ባሕሩ የጥምቀቱ ውኃ ደመናው ደግሞ የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው፡፡
“ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ”(ዘጸአ.40፡34) ወይም “ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው፡፡ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም”(1ነገሥ.8፡10-11) እንዲል ደመናው በእግዚአብሔር ይመሰላል፡፡ ምክንያቱም በደመናው እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ይገለጥ ነበርና፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር በደመና ዓምድ ተመስሎ ነበር ሕዝቡን ይመራ የነበረው፡፡(ዘጸአ.13፡22፤14፡24) አስከትሎም “ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ፡፡ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፡፡ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና” እነዚህም የአማናዊው ሥጋውና ደሙ ምሳሌ ናቸው፡፡ ስለዚህ አክሎ “ያም መንፈሳዊ ዓለት ክርስቶስ ነው” ብሎ ተርጉሞ ጻፈልን፡፡
 ይህን አስመልክቶ ጌታችን አስቀድሞ“…. አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል ፤ እኔም ስለ ዓለም የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡…. እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፡፡እኔም በመጨረሻ ቀን አስነሣዋለሁ፡፡ ሥጋዬን እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡ ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን እንዲሁ የሚበላኝ በእኔ ሕያው ይሆናል ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፡፡”(ዮሐ.6፡49-59)ብሎ አስተምሮናል፡፡
ቢሆንም ግን ተጠምቀን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን ከቅዱስ ሥጋው ከክቡር ደሙ መቀበላችን ላይ በቅድስና መመላለስ ካላከልንበት አደጋ ስላለው ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚብሔር ግን ከአነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም በምድረ በዳ ወድቀዋልና፡፡” ብሎ ጻፈልን፡፡ ለምን ቢባል ወደ ቀደመው የኃጢአት ሕይወታቸው ተመልሰዋልና፡፡ ይህ እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጥ “እነርሱ ክፉ ነገር እንደተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን” አለን፡፡ ምክንያቱም ወደ ጣዖት አምልኮ፣ ወደ መጠጥና ጥጋብ ወደ ዘፈን ወደ ሴሰኝነት ገብተው ነበርና፡፡ በመሆኑም ምድረ ርስትን ሳይወርሱ በረሃው ውጧቸው ቀሩ፡፡ ስለዚህም ተጠምቄ ቆርቢያለሁና እድናለሁ ብሎ ወደ ኃጢአት የተመለሰ ሰው እርሱ እግዚአብሔር ከግንዱ ቆርጦ እንደሚጥለው ሊያሳስበን ቅዱስ ጳውሎስ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ብሎ አሳሰበን (1ቆሮ.10፡1-12)
እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ተጠምቆ ክርስቲያን ስለሆነ ከቅዱስ ሥጋው ከክቡር ደሙ እየተቀበለ በንጽሕናና በቅድስና ስለሚኖረው ክርስቲያን ትንሣኤ ምን እንደሚመስል ሲገለጥልን “በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል” አለን፡፡ የቀድሞው አዳማዊ ሰውነት ተልቶና ሸቶ እንዲሁም በስብሶ አፈር ስለሚሆን “በውርደት ይዘራል” አለ፡፡ “በክብር ይነሣል” ሲልም ይህ እንዲያ ተዋርዶ የሞተው ሰውነት በጥምቀት አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሶት ከሆነ “ክብር ይነሣል” ማለቱ ነው፡፡ ይህ ክብር ጌታችን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ለሦስቱ ደቀ መዛሙርቱ የገለጠውን ክብርን ይመስላል፡፡(ማቴ.17፡2) ወይም “እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንንም ይለውጣል፡፡”(ፊልጵ.3፡21) ካለው ጋር አንድ ነው፡፡ ወይም “ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን”(ሮሜ.6፡4-5) ከሚለው ጋር አንድ ነው፡፡ የውርደት ትንሣኤ ስላለ ከእርሱ ለመለየት ቅዱስ ጳውሎስ የእውነተኛው ክርስቲያን ትንሣኤ “የክብር ትንሣኤ” ማለቱን እናስተውላለን፡፡
አስከትሎም “በድካም ይዘራል በኃይል ይነሣል፡፡” አለን፡፡ “በድካም” ያለው በጽድቅ ሕይወት ለመኖር የምንተጋውን ትጋትን ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንቃትታለን ለበሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡ በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆን በድንኳን ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን፡፡ ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱ የመንፈሱን መያዣ ሰጠን”(2ቆሮ.5፡1-5)ይለናል፡፡ ይህ ደካማ በሆነው በድንኳን በተመሰለው ሰውነታችን ስለምንፈጽመው ክርስቲያናዊ ሕይወት የመናገር ሲሆን ይህን ፈጽመን በሞት ካንቀላፋን በኋላ በትንሣኤ በኃይል እንነሣለን፡፡ ያም ማለት ነግሠን፣ ከብረን እንነሣለን ማለት ነው፡፡
“ፍጥረታዊ አካል ይዘራል መንፈሳዊ አካል ይነሣል” በዚህ ኃይለ ቃል ፍጥረታዊና መንፈሳዊ አካል የተባሉ ሁሉት አካላት አሉን እያለን እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ መንፈሳዊ አካል የሚሆነው ወይም የሆነው ይኸው ተፈጥሮአዊው አካል ነው፡፡ መንፈሳዊ አካልን የምንለብሰው በጥምቀት ነው፡፡ ነገር ግን እውን ሆኖ የሚገለጠው በትንሣኤ ነው፡፡ ይህ ከትንሣኤ በፊት አንለብሰውም የሚል ግን አይደለም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ  ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም” በማለት ሥጋችንን የክርስቶስ አካል ብሎ ባልጻፈልን ነበር፡፡(1ቆሮ.6፡15) በመሆኑም ይህ ፍጥረታዊ አካል መንፈሳዊውን አካል ለብሶት ስላለ በትንሣኤ የማይፈርስ የማይበሰብስ ሆኖ በሥልጣን ይነሣል ስለዚህ “መንፈሳዊ አካል ይነሣል” አለን፡፡  
እስከትሎም “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ ተብሎ ተጽፎልአል” አለን፡፡ እንዲህ ያለው ከምድር አፈር የተበጀውን የአዳም ተፈጥሮ ነው፡፡ አዳም ከአፈጣጠሩ ሥጋና ነፍስ እንዲሁም የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነበር፡፡ ነገር ግን ለነፍሱ ሕያውነት የሚሰጠውና አባ አባ የሚልበት መንፈስ ቅዱስ በመተላለፍ ምክንያት ከእርሱ ስለራቀ ሟች የሆነን ባሕርይን ተላብሶ ወደ ምድር ወረደ፡፡ እኛም የእርሱን ሟች የሆነውን ተፈጥሮ ገንባችን እያደርግን ተፈጠርን፡፡ ይህ ቃል ጠቅለል ስናደርገው የሚናገረው የቀደመው አባታችን ከመሬት መሬታዊ የሆነ ፍጡር መሆኑን ሲሆን፡፡ ሕያውነቱም ለሌላው የሚተርፍ ሳይሆን በራሱ ኖሮ የሚያገልግል መሆኑን ነው፡፡
ሲቀጥል ቅዱስ ጳውሎስ ስለክርስቶስ ይነግረናል፡፡ “ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” አለን፡፡ ይህን የመሰለ ቃል በቀጣይ መልእክቱ ላይም “ጌታ መንፈስ ነው የጌታ መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ”(2ቆሮ.3፡17) በማለት ጽፎልን እናገኛለን፡፡
 ይህ ኃይለ ቃል ቀጥታ ለሥጋው ሰውነቱ የተነገረ ቃል ነው፡፡ በቅድምና ላለው ማንነቱ ይህ ቃል የሚያገለግል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞም ቢሆን መንፈስ ነበርና፡፡ ሥጋን ከለበሰ በኋላ ግን አዳም የሚለውን መጠሪያን አገኘ፡፡ ይህ አዳም የሚለው ስያሜ ለሰውነቱ የተሰጠ ስያሜ እደሆነ ግልጥ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህ አካል መንፈስ ያለው፡፡ ምክንያቱም መንፈስ የነበረው ቃል ሥጋ በመሆኑ ሥጋን መንፈስ አድርጎታልና፡፡ ይህም ማለት አምላክ አድርጎታልና፡፡ ከአብ ዘንድ በቅድምና የነበረ ቃል እግዚአብሔር ነው፡፡እግዚአብሔር ደግሞ መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህም ሥጋ በቃል ምክንያት አምላክ ስለተባለ መንፈስ ተባለ፡፡ ይህም ሥጋ አምላክ ሆነ ለማለት እንጂ ሥጋ ተለውጦ መንፈስ ሆነ ማለት አይደለም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ አዳም የሚለው መጠሪያ ባላስፈለገው ነበር፡፡ ስለዚህም ቃል የተዋደው ሥጋ እንደ ፍጡር መንፈስ ቅዱስ አድሮበት ሕያው ሆኖ የሚኖር ሳይሆን ራሱ ሕይወትን የሚሠጥ መንፈስ ነው ወይም አምላክ ሆነ፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ “ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” አለን፡፡
 ጌታችን ከድንግል ማርያም የነሣውን ሥጋ አምላክ በማድረጉ ረቂቅ ባሕርይም ሥጋ ይታይበት ነበር፡፡ ለምሳሌ በድንግልና ተወለደ፣ ከሕዝብ መካከል ሆኖ ድንገት ይሰወር ነበር፣ በትንሣኤው  መቃብር ክፈቱልኝ መግነዜን ፍቱልኝ ሳይል ተነስቶአል፡፡ ከትንሣኤም በኋላ በዝግ ቤት ገብቶአል፡፡ መንፈስ ብቻ ነው እንዳይሉት መንፈስ ብቻ ከሆንኩ መንፈስ ሥጋና አጥንት የሉትም ሲላቸው ዳሰው በማረጋገጥ እርሱ “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ የተባለው ኋለኛው አዳም” እንደሆነ አስረዳቸው፡፡ ከድንግል የነሣው ሰውነቱ አምላክ ስለሆነ ከሥጋው የበላ ከደሙም የጠጣ ሁሉ ሕይወትን ያገኛል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ጌታችን “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” ብሎናል፡፡(ዮሐ.6፡54) ይህ ሲጠቃለል ቅዱስ ጳውሎስ “ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” ሲል ሥጋ አምላክ ሆነ ረቂቅ የነበረው ባሕርይውን ሳይቀይር አዳም በማባል ግዙፍ ግዙፍ የሆነው ባሕርይውን ሳይቀይር ረቂቅ በመሆን መንፈስ  እንደተባለ መረዳት እንችላለን፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ አስከትሎ “ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም፡፡” አለን፡፡ ትንሣኤ ያስፈለገው ለፍጥረታዊው አካል እንጂ ለመንፈሳዊው አካል አይደለም፡፡ ስለዚህ ፍጥረታዊው አካል ሳይኖር መንፈሳዊው አካል አያስፈልግም ፤መንፈሳዊው አካል ማስፈለጉ ፍጥረታዊው አካል ስላለ ነው፡፡ ስለዚህ ፍጥረታዊው አካል ይቀድማል መንፈሳዊው አካል ይከተላል፡፡
በመቀጠል ስለፍጥረታዊው አካል ባሕርይ ያስረዳል፡- “የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፡፡” አለ፡፡ ይህም አዳም አባታችን ከምድር አፈር መፈጠሩን የሚያስረዳ ነው፡፡” አስከትሎም  “ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው፡፡” አለን ይህም ክርሰቶስ ፈጣሪ መሆኑን ለማስረዳት ነው እንጂ ሥጋውን ከሰማይ ይዞት መጣ ማለቱ አይደለም፡፡ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ሥጋና ደም ከፍሎ ሰው ሆኖ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡ ነገር ግን ሥጋ በተዋሐደው ቃል የተነሣ ቅድምናን እንዳገኘ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ “ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው” ተባለ፡፡
 ለምሳሌ የሚሆኑንን ጥቅሶች እንመልከት “ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው”(ዮሐ.3፡31) እንዲሁም “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” የሚሉትን ጥቅሶች እንመልከታቸው፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች “ከሰማይ የሚመጣው” ወይም “ከሰማይ ከወረደው” በሚለው ቃል ቅድምና ያልነበረው ሥጋ ቅድምና እንዳገኘ እናገኛለን፡፡
 እንደነዚህ ጥቅሶች በጣም ግልጥ በሆነው መልኩ የተቀመጡ አይሁኑ እንጂ ሌሎችም እነዚህን የመሰሉ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት እንችላለን ፡፡ ለምሳሌ ዮሐንስ መጥምቅ “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበረ”(ዮሐ.1፡29)ብሎ የተናገረውን ቃል እንመልከት፡፡ እንደምናውቀው ጌታችን የተጸነሰው ዮሐንስ መጥምቅ ከተጸነሰ 6 ወር በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን ዮሐንስ “አንድ ሰው …ከእኔ ፊት ነበረ” ብሎ ጽፎልናል፡፡ “አንድ ሰው … ከእኔም በፊት ነበረ” ሲል ፈጣሪ ነው ማለቱ ግልጥ ነው፡፡  ኅዳጉን ስንመለከትም የሚመራን “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር” ወደሚለው ቃል ነው፡፡ ነገር ግን ዮሐንስ “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበረ” በሚለው ቃሉ ከድንግል ማርያም የነሣውን ሰውነት ቅድምና ሰጥቶት እንደጻፈልን መገንዘብ ይገባናል፡፡ ይህም ሥጋ አምላክ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ነው፡፡  “እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ”(ዮሐ.8፡58)በሚለውም ቃል ይህን የሚያጠናክርልን ነው፡፡
ሲቀጥል ቅዱስ ጳውሎስ “መሬታዊው እንደሆነ መሬታዊያን እንዲሁ ናቸው፤ ሰማያዊው እንደሆነ ሰማያዊያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው” ብሎ ጻፈልን፡፡ በእርግጥ ይህ እውነት ነው፡፡ በጥምቀት ክርስቶስን ያልለበሰ ሰውነት መሬታዊ ነው፡፡ ይህ መሬታዊ አካል በመንፈስ ቅዱስ ታድሶ መንፈሳዊ አካል ሊሆን ይገባለዋል፡፡ ያለበለዚያ ፍጥረታዊ ሰው እንጂ መንፈሳዊ ሰው አይባልም፡፡ (1ቆሮ.2፡14-16)
በመሆኑም “የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን”አለን፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ አንድ ነገርን እናስተውላለን እናስተውላለን፡፡ “የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን” ሲል እንደልብስ ደርበነዋል ማለት ሳይሆን ተፈጥሮአችን አድርገነዋል ማለቱ እንደሆነ ሁሉ “ሰማያዊውን መልክ እንለብሳለን” ሲልም ሥጋችን የክርሰቶስ የአካሉ ሕዋስ ይሆናል ማለቱ እንደሆነ ልንረዳለን፡፡ ይህ የሚፈጸመው በጥምቀት ነው፡፡ በጥምቀት ሰማያዊ የሆነውን ክርስቶስን እንለብሳለን፡፡ ክርስቶስን ካለበስነው መሬታዊውን መልክ እንደለበስን ነንና  “ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን አይወርስም፡፡” ብሎ እንደ ገለጠልን ፈጽሞ መዳን አንችልም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ያልታደሰውን የቀድሞውን አዳማዊ ባሕርይ ገንዘባችን አድርገን በክብርና በኃይል ክርስቶስን ለብሰን አንነሣም፡፡ ተጠምቀን ክርስቶስን ካለበስነውና በተፈጠርነበት ዓላማ በአግባቡ ካልተመላለስን የእኛ ትንሣኤ የሚሆነው የውርደት ትንሣኤ ነው፡፡ ስለዚህም ወገኖች በእጅጉ ልናስተውለው የሚገባ ነገር እንዳለ ልንረዳ ይገባናል፡፡ ክርስቶስን መስለን በክብር ለመነሣት በጥምቀት ከእግዚአብሔር መወለድና ክርስቶስን ለብሰን ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ ልንቀበል ከዚህ ጨምረንም በክርስቲያናዊ ሥነምግባር በአግባቡ ልንመላለስ ይገባናል፡፡ አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን መስለን እንደሚገባን ሆነን በጽድቅ እንመላለስና በትንሣኤ እርሱን ለብስንና መስለን ለመነሣት ያብቃን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡        

1 comment:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን:: የክብር ትንሳኤ ባለቤት ያድርገን

    ReplyDelete