Thursday, January 26, 2012

“ይህ ምሥጢር (በእውነት) ታላቅ ነው ፡፡”



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/05/2004
እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር ሲያበጀው በአርዓያውና በአምሳሉ መፍጠሩ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ውስጥ ያለ ሦስትነትና አንድነት በሰዎችም ዘንድ እንዲታይ በመሻቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን በአካል ሦስት ነው፡፡ በአካል ሦስት ሲሆን በእግዚአብሔርነቱ አንድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መገለጫው ባሕርይ የሕግጋት ሁሉ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር በመሆኑ በባሕርይው መገለጫ ስሙ እግዚአብሔርን ፍቅር እንለዋለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ፍጹም የሆነ አንድነት በአርአያውና አምሳሉ በፈጠረው ሰው እንዲገለጥ በሰው ሰብእና ውስጥ ፍቅርን ተከላት፡፡ በፍቅርም ሰውን ሁሉ ፍጹም ወደ ሆነ አንድነት ያመጣዋል፡፡ ያለፍቅር ሰው እግዚአብሔርን ከቶ ሊመስለው አይችልም፡፡
ይህ እንዲሆን እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ አዳምን ከፍቅር ጋር አዋሕዶ ፈጠረው፤ በመቀጠል ስለፍቅር ከጎኑ  አጥንት ሔዋንን አበጃት፣ የፍቅርን ፍሬ ይመለከቱ ዘንድ ደግሞ በሁለቱ አንድነት እኛን ልጆቹን ሰጣቸው፡፡ እነዚህ በቁጥር ሦስት ቢሆኑም በመገኛቸው አዳም አንድ ናቸው፡፡ እንዲህም ሲባል አባት፤ እናት እና ልጅ ማለታችን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ አንድነት ሲመሰክር “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ባረካቸውም፡፡ እነርሱንም በፈጠረበት ቀን ስሙን አዳም ብሎ ጠራው” ይለናል፡፡(ዘፍ.5፡1-2) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ሦስትነትና አንድነት በሰዎች ውስጥ እንዲታይ መፍቀዱን እናስተውላለን፡፡



Wednesday, January 25, 2012

በእውን እግዚአብሔር በሰዎች ልጆች ላይ ፍትሐዊ ነውን?(ቅዱስ ይስሐቅ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/05/2004
 ስለእግዚአብሔር ብሎ ማጣትን በፍጹም ፈቃደኝነትና ደስታ የተቀበለ ሰው እርሱ በውስጡ ንጹሕ የሆነ ሰው ነው፡፡ የሰውን ስህተት የማይመለከት እርሱ በእውነት አርነት የወጣ ሰው ነው፡፡ ከሰው በሚቀርብለት ክብር ያልተደሰተ እርሱንም በማያከብሩት ያልተከፋ ሰው እርሱ ለዚህ ዓለምና ለምድራዊ አኗኗር የሞተ ሰው ነው ፡፡ ማስተዋል ለሰዎች ከተሠሩላቸው ሕግጋት ሁሉ እጅግ የላቀና በየትኛውም ደረጃ እና መመዘኛ ሥራን በአግባቡ ለማከናወን ዓይነተኛ መሣሪያ ነው ፡፡ ኃጢአተኛውን አትጥላው እኛ ሁላችን የኃጢአትን ሸክም የተሸከምን በደለኞች ነንና ፡፡
 ስለ እግዚአብሔር ብለህ እርሱን ለመቃወም ከተነሣህ ግን ስለ እርሱ አልቅስለት ፡፡ ስለምን እርሱን ትጠላዋለህ? ኃጢአቱን ጥላ  ስለእርሱም መመለስ ጸልይለት ፡፡ እንዲህ በማድረግ በኃጢአተኞች ላይ ያለተቆጣውን ነገር ግን ስለእነርሱ መዳን የጸለየውን ክርስቶስን ምሰለው፡፡ ስለኢየሩሳሌም መጥፋት እንዴት እንዳለቀሰ አትመለከትምን ? በብዙ ድክመቶቻችን የተነሣ ሰይጣን በእኛ ላይ ያፌዝብናል ፡፡ በእኛ ላይ በሚያፌዘው ሰይጣን የሚፌዝበትን ወንድማችንን ስለምን እንጠላዋለን? ሰው ሆይ ስለምን እንዲህ ይሆናል ? ኃጢአተኛን መጥላት ትፈልጋለህ እርሱ እንዳንተ ጻድቅ መሆን ይሣነዋልን ? ፍቅር ሳይኖርህ የአንተ ቅድስና ምን ይጠቅምሃል ? ስለእርሱ ስለምን አታነባም ? ነገር ግን አንተ እርሱን ታሳድደዋለህ ፡፡ አንዳንዶች በኃጥአን ላይ ባለማስተዋል በቁጣ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የኃጢአተኞችንም ሥራ ለይተው የሚያውቁ አድርገው በራሳቸው  ይታመናሉ፡፡

Tuesday, January 24, 2012

“ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ”(ራእ.12፡1)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/05/2004
እነሆ ታላቅ የሆነ ለሰዎች ልጆች መዳን የሚጠቅመውና ትርጉም ያለው በአምላክ የተፈጸመው ታላቁ  ምልክት የታየው በምድር ላይ እንጂ በሰማያት ከመላእክት ጉባኤ አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ በነቢዩ “ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣቸኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለችው ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”(ኢሳ.7፡14) እንዲል ታላቅ የሆነው ምልክት የታየው በምድር ነው፡፡ ሰማያውያን መላእክት ራሳቸው እንኳ ይህ ታላቅ የሆነ ምልክት ለማየት ሲሉ ጌታ ከተወለደበት ግርገግም ተገኙ፤ "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ" እያሉ በምድር ዝማሬን አቀረቡ፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ “ታላቅ ምልክት በሰማያት ታየ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃን ተጫምታ በራሱዋም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች”(ራእ.12፡1)ሲል ስለ ጌታ ልደት ብቻ መናገሩ አልነበረም፡፡ ይህ ምልክት ከልደት እስከ ዕረገት በጌታችን ሥጋዌ የተፈጸሙትን የድኅነት ሥራዎችን ሁሉ የሚጠቀልል ነው፡፡እነዚህ የድኅነት ሥራዎች በምድር ይፈጸሙ እንጂ በሰማያዊው አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና ፍጹም ሰማያዊያን ናቸው፡፡ ያም ማለት በቦታና በጊዜ የሚወሰኑ አይደሉም፤ ዘለዓለማውያንና ዘመን የማይቆጠርላቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዘመን በማይቆጠርለት አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና፡፡ እነዚህን የድኅነት ሥራዎች ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው  ሰውነት የከወናቸው ናቸው፡፡