Tuesday, February 14, 2012

እግዚአብሔርን ከማወቅ ጋር ፆታዊ ፍቅር ጣፋጭ!!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/06/2004


ፆታዊ ፍቅር ክርስቶስን በማወቅ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እጅግ ጣፋጭና ማራኪ ይሆንልናል፡፡ እንዲያ ከሆነ ባል በሚስቱ ተፈጥሮ በኩል የጌታውን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ እኛን መንፈሳዊያን ያደረገንን መንፈስ ቅዱስን እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ይመለከትባታል፡፡ ሚስትም በባሎዋ መስታወትነት ለሔዋን እናትም አባትም የሆነውን ቀዳማዊ አዳምንና እርሱዋን ከጎኑ በፈሰሰው መለኮታዊ ውኃ አንጽቶ ከጎኑ በፈሰሰው ክቡር ደሙ ተቤዥቶ የወለዳትን ዳግማዊውን አዳም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትመለከተዋለች፡፡ በሚወልዱአቸው ልጆቻቸው ውስጥም በሥጋ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም እቅፍ የነበረውን፣ እንደ እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅነቱ ግን ከአባቱ እቅፍ የሆነውን ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስን በአንድነት በልጆቻቸው ይመለከቱታል፡፡

Monday, February 13, 2012

ለእኛስ የፍቅረኞች ቀን ይኖረን ይሆንን?(ቀጣይ ጽሑፍ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/06/2004
... ከእዚህ መንደርደሪያ አሳብ ተነሥተን ጾታዊ ፍቅር የተገለጠው መቼ ነው ብለን ብንጠይቅ ሔዋን ከአዳም የግራ ጎን ከተገኘች በኋላ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዚያን ጊዜ አባታችን አዳም እግዚአብሔር ከጎኑ አጥንት የፈጠራትን ሴት በተመለከተ ጊዜ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት” በማለት ለእርሱዋ ያለውን ፍቅር ለአምላኩ ገለጠ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር በገነት በአዳምና በሔዋን መካከል ትዳርን መሠረተ፡፡እግዚአብሔርም "ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል(ይተባበራል)" አለ፡፡ ስለዚህም ለአዳምና ለሔዋን እቺ ዕለት የደስታቸው ቀን ናትና መቼም ቢሆን የሚረሱዋት ቀን አይደለችም፡፡
ይህ በሰማያት የተሠራው ሰማያዊ ሥርዐት ከውድቀትም በኋላም ቀጥሎአል፡፡ ስለዚህም በዚህ ፍቅር እርስ በእርሳችን እንሳሳባለን በትዳርም እንታሰራለን፡፡ ሥርዐቱም ሰማያዊ ነውና ፍቺ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡ ፍቺ ተፈጸመ ማለት ትዳሩ ከሰማያዊው ሥርዐት ወጣ እንስሳዊ ሆነ  ቅድስናውን አጣ ማለት ነው፡፡ ያም ማለት ምን ማለት መሰላችሁ በሥላሴ ውስጥ ያለው አንድነትና ሦስትነት መልኩን አጣ ከተፈጠርንበት ዓላማ ወጣን ማለት ነው፡፡


Sunday, February 12, 2012

ለእኛስ የፍቅረኞች ቀን ይኖረን ይሆንን?



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/06/2004
ዘመኑ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ አንድ ቫላንታይን የሚባል ቅዱስ እንደሆነ የሚነገርለትና በሰማዕትነት ያረፈ ቄስ ነበር፡፡ በእርሱ ስምም በአውሮፓ ፌብሯሪ ዐሥራ ዐራት ቀን በእኛ አቆጣጠር የካቲት ስድስት የፍቅረኞች ቀን ተብሎ ይከበር ነበር፡፡ ነገር ግን የኋላ ኋላ ይህ በዓል በሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አንዳይከበር ታገደ፡፡ ነገር ግን አንደገና ይህ በዓል ሕይወት ዘርቶ በአውሮፓውያን ዘንድ ይከበር ያዘ ፡፡ ቀስ በቀስም በዓሉ የአውሮፓውያን መሆኑ ቀርቶ የመላው ዓለም ሆነ፡፡ በሀገራችንም የፍቅረኞች ቀን መከበር ከጀመረ ሰነባብቶአል፡፡ ይህን እስከዚህ ካልኩ ይበቃኛል፡፡ ምክንያቱም ከእኛ ትውፊት ጋር ፈጽሞ የማይዛመድ ስለሆነ ትቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን አልነቅፍም፤ ዓላማዬም ይህ አይደለም የኔ ትኩረት ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ክቡር ስለሆነው ጾታዊ ፍቅር አንድ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጾታዊ ፍቅር ሰማያዊ፣ ድንቅና ግሩም ነውና፡፡