Monday, March 5, 2012

ተወዳጆች ሆይ እናንተ……ናችሁ!!(በአፍርሃት ሶርያዊ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/06/2004
"ተወዳጆችና የሰላም ልጆች እንዲሁም የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ሆይ! እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ እናንተ የምድር ጨውና የሰውነት(የዓለም) ዓይኖች ናችሁ፡፡ እናንተ የሙሽራውና የመልካሙ ዘር እንዲሁም የሕይወት ውኃ ለሚፈልቅበትና የማዕዘን ራስ ለሆነው ሕያው ዓለት ክርስቶስ ሚዜዎች ናችሁ፤ እናንተ አጥልቃችሁ በመቆፈር ቤታችሁን በዓለት ላይ የምትሠሩ ብልህ አናጺዎች ናቸሁ፡፡
እናንተ የብዙ ብዙ የሆነ እህልን በጎተራችሁ የምታከማቹ ታታሪ የጽድቅ ገበሬዎች ናችሁ፡፡ እናንተ የተሰጣችሁን ጥሪት ብዙ እጥፍ አትርፋችሁ የተገኛችሁ ትጉሃን ነጋዴዎች ናቸሁ፡፡ እናንተ ዋጋችሁን ተቀብላችው ሌላ ይጨመርላችሁ ዘንድ ያልጠየቃችሁ ቅን ሠራተኞች ናችሁ፡፡


Saturday, March 3, 2012

ሴቶች ሊያውቁዋት የምትገባ እውነት!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
24/06/2004
ዛሬ ባነሣሁት ጭብጥ ላይ:- ደግሞ ምን አመጣህ? ትሉኝ ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ፍጥጥ ያለ እውነትና እውቀት ነው፡፡ ይህቺ እውነት እናቶቻችን፡- "ድሮ አግኝተናት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይህች ዓለም የአውሬዎች መፈንጫ ባልሆነች ነበር" ብለው የሚቆጩባት እውነት ናት፡፡ ይህቺ እውቀትና እውነት ፡-  ዓለምን ሴቶች ይገዙአትና ይመሩዋት ዘንድ ተፈጠረች የምትል ናት፡፡ መቼም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብላችሁ በመገረም ትጠይቁኝ ይሆናል፡፡ እውነቱና ሐቁ ግን ይህ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሴት ልጅ ገነትን እንደራሱዋ ሃሳብና ጥቅም ትመራትና ትጠቀምባት ዘንድ በዚህም እርፍ ብላ ትኖርባት ዘንድ አዳምን ጨምሮ ሁሉን አደላድሎ ከፈጠረ በኋላ የፍጥረት ሁሉ ዘውድ አድርጎ ከአዳም አስገኛት፡፡ አዳም አስቀድሞ በሥጋ መገለጡ ለእርሱዋ በእግዚአብሔር ፈንታ ሆኖ ገነትን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንደምትችል ያስተምራት ዘንድ ነበር፡፡ በእርግጥም አዳም ይህን ፈጽሞላታል፡፡ ስለዚህም ነው ሰይጣን እርሱዋን በተንኮል “በእውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ በጠየቃት ጊዜ “በገነት ካለው ዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ፡-እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም”ብላ መመለሱዋ፡፡(ዘፍ.3፡2-3)

Thursday, March 1, 2012

ገነት በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/06/2004
በዚህ መዝሙር ቅዱስ ኤፍሬም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን ዓለት በማንሣት እግዚአብሔር ፍጥረታትን እንዴት እንደፈጠራቸውና ስለገነት ያለውን አስተምህሮ እንመለከታለን፡፡

እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን አለትን አስታውሼ ዓለማትን የፈጠረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልብ አልኩ፡፡ እንደ ታላቅ ወንዝ ለእነርሱ ከአለቱ ውስጥ የፈለቀው ውኃ በውስጡ ካለው የውኃ ቋት የተገኘ አልነበረም ፡፡ በአለቱ ውስጥ አንድም ጠብታ ውኃ የለም፤ ነገር ግን ልክ የእግዚአብሔር ቃል ፍጥረትን ከምንም እንዳስገኛቸው፤እንዲሁ ታላቅ የውኃ ጅረት ከደረቅ ድንጋይ ውስጥ ፈልቆ የተጠሙትን አረካቸው፡፡
ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ተፈጥሮ ገልጦ ጽፎልናል  ስለዚህም ተፈጥሮና መጽሐፍ ቅዱስ ስለፈጣሪ ምስክሮች ሆኑ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለራሱ ጥቅም ሲገለገልባት እንደሚያውቃት እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ በውስጡ የያዘውን መረዳት ይቻለናል እነዚህን ሁለቱን ምስክሮች በሁሉ ስፍራ እናገኛቸዋለን፡፡