በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/06/2004
ጌታችን ሆይ! ዛሬ ወደ ኋላ ተመልሼ የአዳምና የሔዋን ቅድስናና ንጽሕና
ምን ይመስል እንደነበረ ለማስተዋል ሞከርኩ፡፡ ጌታ ሆይ! የኃጢአታችንን ታላቅነት እኛ በአንተ ላይ ባደረስነው መከራ ስንመለከተው፣ የጥንት ቅድስናችንንና ንጽሕናችንን በአንተ ሰው መሆን ውስጥ ተመለከትነው፡፡ አዎ ጌታችን ሆይ! በአንተ የቀደመው የቅድስና ሕይወታችን ምን ያህል ማራኪ እንደነበረ አስተዋልነው፡፡ አንተ በልብህ
ትሑትና የዋህ እንደሆንክ ነገር ግን የዋህነትህ ከእውቀት ጉድለት እንዳልሆነ እንዲሁ ከውድቀት በፊት የአዳም አባታችንና የሔዋን
እናታችን ትሕትናና የዋህነት በእውቀት የተሞላ ነበር፡፡
አንተ ፍጥረትህን ነፍስህን እስከ መስጠት ደርሰህ እንድትወድ እንዲሁ
አዳምና ሔዋንም ራሳቸውን እስከመስጠት ድረስ ደርሰው አንተንና ከሥራቸው ያስገዛህላቸውን ፍጥረታት ይወዱ እንደ ነበር አሳየኸን፡፡
ጌታ ሆይ! አዳምና ሔዋን እርስ እርሳቸውም ያላቸው ፍቅር በአንተና በአባትህ መካከል እንዳለው ዓይነት ፍቅር ይመስል ነበር፡፡ ቅድስናቸውም
አንተ “የሰማዩ አባቴ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብለህ እንዳስተማረከን ዓይነት ሥላሴን አብነት ያደረገ ቅድስና ነበር፡፡
ይህ እንደ ሕፃን ቅዱስና ንጹሕ የሆነ የአዳምና የሔዋን ተፈጥሮ በአንተ ዘንድ እጅግ ተፈቃሪ ነበር፡፡ ስለዚህም አባታችን ያዕቆብ
ከልጆቹ ይልቅ የክርስቶስ ኢየሱስ አርአያ ያለውን ዮሴፍን እንዲወደው፣ አንተም ጌታ ሆይ! እኛን የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጥረታት
ሁሉ ይልቅ የአንተ አርአያ ይታይብናልና ትወደን ነበር፡፡


