Friday, March 30, 2012

የመንፈስ ቅዱስ እናትነት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/07/2004
የክርስቶስ ልብ የተባለ፤ የእግዚአብሔር አብ እስትንፋሱ እንዲሁም የፍጥረት ሁሉ አስገኚ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ለተጠማቂያን ክርስቲያኖች እናታችን ነው፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር ብቸኛ ልጁ የሆነውን አፍቃሪያችንን ክርስቶስ ኢየሱስን  ይበልጥ እንድናውቀውና እንድንረዳው እንዲሁም እርሱን አብነት አድርገ እርሱ የሞተለትን የሰውን ልጅ ለእግዚአብሔር አብ እንድንማርክና የእግዚአብሔር አብና የእግዚአብሔር ወልድ ልጆች፣ የክርስቶስ ወንድሞች(በጸጋ) በማድረግ እንድናቀርባቸው፤ በጥምቀት ካህናት፤ የክርስቶስ ወታደሮች፤ የእርሱ አባሳደሮች አድርጎ የሾመን ነው፡፡ ስንጠመቅ ለእያንዳንዳችን ራሱ በሰጠን ጸጋ እንደ እናት ሰብስቦ የጸጋውን ወተት የሚመግበን፣ በእርሱም ባገኘነው ክርስቶስን በሚመስል ተፈጥሮአችን በአእምሮም በአካልም በሞገስም ልክ እንደ እናት እቅፍ ድግፍ አድርጎ በፍቅር የሚያሳድገን እርሱ ነው፡፡


Thursday, March 29, 2012

ቅድስት ድንግል ማርያም ስለልጁዋ ስለወዳጁዋ እንዲህ አለች፡-(በቅዱስ ኤፍሬም)




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/07/2004
“ቅድስት ድንግል ማርያም ስለልጁዋ ስለወዳጁዋ እንዲህ አለች፡-  እኔ የተሸከምኩት ሕፃን እርሱ እኔን የተሸከመኝ ነው ፡፡ እርሱ ክንፎቹን ዝቅ አድርጎ በእቅፎቹ ውስጥ አኖረኝ ፡፡ ከእርሱም ጋር ወደ ሰማየ ሰማያትም ተነጠቅኩ ፡፡ በዚያም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ ለልጄ እንዲሆን ቃል ኪዳን ተገባልኝ ፡፡
ልጄን መልአኩ ገብርኤል ጌታዬ ብሎ ሲጠራው ሰማሁ ፣ ሊቀ ካህኑና አገልጋዩም (ስምዖን አረጋዊ) እርሱን በእቅፉ ይዞ ስለእርሱ ትንቢትን ተናገረ ፡፡ ሰብአ ሰገል በፊቱ ወድቀው ሲሰግዱለት፤ ሄሮድስም ንግሥናዬን የሚቀማ ሌላ ንጉሥ ተነሣብኝ ብሎ ሲርድ ተመለከትኩ ፡፡
ሙሴን አገኘዋለሁ ብሎ የዕብራዊያንን ሕፃናት ያስፈጀ ሰይጣን እርሱን በመስቀሉ ጠርቆ የሚያስወግደውን ሕፃን ለመግደል ሽቶ ሄሮድስን መሳፈሪያው አድርጎ ሕፃናትን ለመግደል ተፋጠነ፡፡ ነገር ግን ጠላቶቹ የሆኑትን ሊያድናቸው የመጣው ጌታ ወደ ግብፅ ተሰደደ ፡፡
ቀዳማይቱ ሔዋን በድንግናዋ የእፍረት ልብስ ለበሰች፡፡ ያንተ እናት ግን በድንግልናዋ ለሁሉ የሚበቃውን የክብርን ልብስ ደረበች ፡፡ እርሱዋ ሁሉን የሚያለብሰውን ጌታ ውሱን የሆነውን ሥጋዋን አለበሰችው ፡፡

Saturday, March 24, 2012

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን በቅዱስ ኤፍሬም የንባብ ስልት እናንብበው



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/07/2004
መጽሐፍ ቅዱስን ቅዱስ ኤፍሬም እንዴት መነበብ እንዳለበት ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡- “ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በሦስት ዐይነት መንገድ ያነብቡታል፡፡ አንደኞቹ በስሜት ሆነው የሚያነቡ(with passion) ሲሆኑ የእነዚህ ወገኖች አነባበብ ፀሐይ በተኮሰች ጊዜ ሥር ስላልነበረው ደርቆና ጠውልጎ ፍሬ ሳያፈራ የቀረውን በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራን ዘር ይመስላሉ፡፡(ማቴ.13፡20) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእነዚህ ወገኖች እንደገለጠው ለጊዜው መጻሕፍትን አንብበው እውቀትን በመጨበጣቸው ደስ የሚሰኙ ሲሆኑ፤  ነገር ግን በውስጡ ተጽፈው ያሉትን በጎ ምግባራት ለመፈጸም ከብዶአቸው ከማንበብ የተመለሱ ወይም ከንባብ ተሰላችተው ያቆሙ ናቸው፡፡
 ሌሎቹ ደግሞ አዋቂዎች ለመባልና ለመራቀቅ ሲሉ የሚያነቡ ናቸው፡፡ ጉድለት ለማግኘትም ብለው የሚያነቡ አሉ (without Passion)፡፡ እነዚህ ወገኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ከሌሎች ጋር ሊሟገቱበት እንጂ በውስጡ የያዘውን በጎ ምግባር ለመተግበር አስበው የሚያነቡ አይደሉም፡፡ ሦስተኞቹ ወገኖች ግን መጽሐፍ ቅዱስን በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ሆነው የሚያነቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች እያንዳንዷን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እግዚአብሔርን በማፍቀር ሆነው የሚያነቡ ናቸው(with Love of God)"ይለናል፡፡