Tuesday, April 3, 2012

ማርታና ሞቤድ


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/07/2004
ሞቤድ ፋርሶች ሶርያን በተቆጣጠሩበት በ4ተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የዞሮአስትራኒዚም እምነት ተከታይና ፈራጅ ዳኛ ነው፡፡ ማርታ ደግሞ እርሱ በዳኝነት በተሰየመባት ከተማ ትኖር የነበረች በጥንታዊያን የሶርያ ክርስቲያኖች ዘንድ “የቃል ኪዳን ልጆች” ተብለው ከሚጠሩት ወገን ነበረች፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለእርሱዋም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰማዕትነት የምትቀበልበት ጊዜው ደርሶ ኖሮ ይህ የከተማዋ ዳኛ ወደ እርሱ አስጠርቶ እንዲህ ብሎ አስጠቅቆ ተናገራት፡-
 “አንቺ ሴት እኔ የምልሽን ብቻ ልብ ብለሽ አድምጪ፤ ምኞትሽን ተከትለሽ እኔ የምልሽን ከመፈጸም እንዳትዘገዪ ተጠንቀቂ፡፡ በእምነትሽ ትኖሪ ዘንድ አልከለክልሽም፤ እምነትሽን በተመለከተ እንደ ፈቃድሽ ማድረግ ትችያለሽ፡፡  ነገር ግን እኔ የማዝሽን ብቻ ፈጽሚ፤ እኔ የምልሽን የፈጸምሽ እንደሆነ ከሞት ቅጣት ትድኛለሽ፡፡ ማርታ ሆይ ይህ “ቃል ኪዳን” የምትይውን የማይረባ ነገርሽን ትተሽ ገና ወጣትና መልከ መልካም ሴት ነሽና ባል ፈልገሽ አግቢ፤ ሴቶች ልጆችንና ወንዶች ልጆችን ወልደሽ ኑሪ” ብሎ አዘዛት፡፡

Monday, April 2, 2012

ጦምን እንዲህ ብንረዳውስ?


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
25/07/2004
ምግብ ለሰው ልጆች በሕይወት መቆየት መሠረታዊ ነገር ሆኖ መቆጠር የጀመረው ከውድቀት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን እንዲያ  አልነበረም፡፡ የቀደመው የአዳምና የሔዋን ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መረዳት እንችላለን፡፡ እርሱ ምንም እንኳ የእኛን ተፈጥሮ ገንዘቡ ያደረገ ቢሆንም እንዲያ በመሆኑ ምክንያት ልክ እንደ እኛ በሕይወት ለመቆየት ምግብ አላስፈለገውም፡፡ እንዲህ ስል ግን የእርሱን አምላክነት ዘንግቼው ሳይሆን የአዳምና የሔዋን በገነት የነበራቸውን ሕይወት ለማስረዳት ከእርሱ የተሻለ ማሳያ ስለሌለ ነው፡፡
አዳምና ሔዋን ከውድቀት በፊት በገነት ሳሉ በገነት ካሉ ፍራፍሬዎች ይመገቡ ነበር እንጂ በሕይወት መቆየታቸው በእነርሱ ላይ የተመሠረተ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከውድቀት በኋላ ሕይወታችን ከሆነው በአፍንጫችን እፍ ተብሎ ከተሰጠን መንፈስ ቅዱስ ስለተለየን መጽናናታችንና በሕይወት መቆየታችን በምግብ ላይ ተመሠረተ ሆነ፡፡

Saturday, March 31, 2012

ለአንድ ክርስቲያን የሰንበት ትርጉም


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/07/2004
አንድ ቅዱስ ሰንበትን ግርዘት ብሎ ይጠራታል፡፡ አንድ ጊዜ የተገረዘ ሰው ድጋሚ መገረዝ እንደማያስፈልገው እንዲሁ አንድ ጊዜ የተጠመቀም ድጋሚ መጠመቅ አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ ግርዘት የጥምቀትም ጥላ ነው ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስረዳ “የሥጋን ሰውነት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ”(ቆላ.2፡11)ይለናል፡፡
የተጠመቀ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በሞቱ በመተባበር የቀድሞውን አዳም ቀብሮ ዳግማዊውን አዳም ክርስቶስን ለብሶ ይነሣል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ሲጠመቅ “የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይገባዋል” የሚለው የሐዋርያው ቃል በእርሱ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡(1ቆሮ.15፡45፣52) ትንሣኤአችን ግን የሚተገበረው እኛ በዚህ ምድር ሳለን እንደ ክርስቶስ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ ሕያዋን ሆነን የተመላለስን እንደሆነ ብቻ ነው፡፡