Monday, December 24, 2012

ወንድሞቼና እኅቶቼ በጋብቻ መነኩሳት ትሆኑ ዘንድ ምኞቴ ነው!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/04/2005
ፍጹም አንድ መሆን፡፡ የራስን አካል የሚያውቁትን ያህል ማወቅ ምንኩስና የሚለውን ቃል ፍቺ ይሰጠናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መንፈሳዊ ጋብቻ የሚለው በመለኮትና በሥጋ መካከል የተፈጸመውንና በልደት የተገለጠውን ተዋሕዶን ነው፡፡ ይህን ጋብቻ ይለዋል፡፡ አንድ ክርስቶስ፣ አንድ ኢየሱስ፣ አንድ የእግዚአብሔር ልጅ፣ እርሱ የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት ነው ይህን ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር የተነሣ በገዛ ሥልጣኑ አደረገው ፡፡ ፍጹም የተዋሐዱ ፈጽሞ የማይለያዩ አንድ አካል ብቻ የሆነ፡፡ መነኮስ ማለትም አንድ ብቻ፤ ብቸኛ ማለት ነው፡፡ “ሁለቱ አንድ ይሆናሉ” የሚለው ቃል ሲፈጸም አንድና ብቸኞች ይሆናሉ ግን ሙሉ ናቸው፡፡

Friday, December 21, 2012

አርምሞ (ለአንድ ወንድሜ የጻፈኩት)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/04/2005
አርምሞ ከራስ ጋር ለመሆን ጊዜን ከመስጠት የሚጀምር ነው፡፡ እንዲያው በባዶ ግን አይደለም፤ አስቀድሞ የግል ጊዜ ሊኖረን  ግድ ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ዐይን ውስጥ ትንሽ ብናኝ ብትገባ እንደምትረበሽና እንደምትታወክ ከዚያም በላይ አንደምታለቅስ እንዲሁ ሕሊናም ጥቃቅን በምንላቸው ኃጢአቶች መረበሹና መታወኩ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሕሊናችን በኃጢአት ከተያዘ መረጋጋትን ገንዘባችን ማድረግ አይቻለንም፡፡
ነገር ግን ሕሊናችን ከኃጢአት ነጽቶ እርጋታን ገንዘቡ ሲያደርግ በጥሙና ሆነን ያለ አንዳች መደነቃቀፍ መንፈሳዊውን ዓለምና ምሥጢር ወደ መረዳት እንመጣለን፡፡ ስለዚህ ወደ ጥሙና ሕይወት ከመግባታችን በፊት አስቀድመን ለንስሐ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን በኋላም ንስሐ መግባት፡፡ በንስሐ የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን ይቀጣጠላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለእግዚአብሔር በጥልቀት ለማወቅ እጅግ እንጓጓለን፡፡ በዚህ ሰዓት ነው እንግዲህ የምናነባቸውን ምንባባትና የምንጸልያቸውን ጸሎታት መምረጥ ያለብን፡፡ ያለበለዚያ ፈጽሞ አርምሞን ገንዘባችን ማድረግ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ ሌላውን የሚነቅፉና ለጠላት ጥፋትን የሚለምኑ ምንባባትንና ጸሎታትን ከማንበብ መከልከል ተገቢ ነው፡፡

Saturday, December 15, 2012

የሞቴ ማስታወሻ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/04/2005
ሰው ማለት እንደ እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ከንቱ የሆነች አንዲትም ሰከንድ የለችም፡፡ ሰውም እንዲሁ ዘመኑን ሁሉ በጥንቃቄና ያለዝንጋዔ እግዚአብሔርን መስሎ ሊኖር ተፈጠረ፡፡ የሰው ደስታው እውነት፣ ጽድቅ፣ ቅን ፈራጅነት፣ ከእውቀት ያልተለየ ፍቅር ናቸው፡፡ እነዚህን በተመለከተ አዳም አባታችን፣ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና እርሱን በቅርበት ያወቁት ሐዋርያት ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ከጌታችንና ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትም የምናስተውለው ሰው ሊጸድቅ የሚችለው ልቡን በቃሉ ሞልቶ የሥነ ምግባራችን ቁልፍ በሆነው ማስተዋል የተመላለሰ  እንደሆነ ነው፡፡ ይህን ግን ምናልባት በቀን ውስጥ ሁለት ደቂቃ ግፋ ቢል አምስት ደቂቃ ሰጥተን ብናስበው ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ስለእግዚአብሔር እውቀቱ ካለው ነው፡፡ የሌለው ግን ዘመኑን ሁሉ እንደ ነዌ ያሳልፈዋል፤ አንድም ሰከንድ እንኳ እግዚአብሔርን የሚያስብበት ጊዜ የለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ በዝንጋዔ ሆኖ በስሜቶቹ ፈቃድ እየተነዳ በኃጢአት ሲንቧቸር ይኖራል፡፡ ይህ የአብዛኞቻችን ሕይወት ነው፡፡