Friday, April 14, 2017

የነፍስ ወግ

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
6/08/2009

ረቂቅ የሆነ እርሱ ፈጣሪዬ በእርሱ ፊት ምንም ግዙፍ ብሆን ሚስቴ ላደረጋት ከምድር አፈር ለፈጠራት ሥጋዬ በእርግጥም ረቂቅ ነኝ፡፡ እርሱ የፈጠረኝ አምላክ በእርሱ አርአያና አምሳል የፈጠረኝ ቢሆንም እንደርሱ ረቂቅ ስለሆንኹ ረቂቃኑ መላእክትም ግዙፋኑ ፍጥረታትም የእርሱን አርአያ በግዘፍ እንዲያዩ አምለክ ሥጋ ሚስቴን ግዙፍ አድርጎ ፈጠራት፡፡
 ከመላእክት እኔ የምለየው ከሥጋ ጋር አንድ አካል መሆን ስለሚቻለኝ ነው፡፡ በሌላ ተፈጥሮዬ ግን ከእነርሱ ጋር አንድ ነኝ፡፡ ቢሆንም ለእኔ ከውድቀት በፊት የነበረው የሥጋ ተፈጥሮ በእጅጉ ይስማማኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም በገነት ለሥጋ የተሰጡ መብላት ሥጋን በሕይወት እንድትቆይ ምንም ዓይነት ሚና የላቸውምና ሥጋን በሕይወት ለማቆየት ስል ምንም ድካም የለብኝም ነበርና፡፡ ከውድቀት በኋላ ግን ከመላእክት ጉባኤ በልዩ ተፈጥሮ ሆኜ የአምላኬን ፍቅር እየተመገብሁ ከምኖርበት መኖሪያዬ ገነት በራሴው ጥፋት የክፋት ምክንያት የሆነውን ሞትን በሥጋዬ ላይ ሹሜ፥ ፍቅርን አጥፍቼ ፥ ፍርሃትን አንግሼ ከመላእክት ጉባኤ ተለየሁ፡፡

Sunday, March 26, 2017

ምጽአቱ ለክርስቶስ


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/07/2009


ወዮ ይህች ከእውነተኛ ጌታ የወጣች ትምህርት እንዴት ታስፈራለች ? እርሱ  ስለትንሣኤ ሕይወታችን በዐሥሩ ደናግላን መስሎ አስተማረን እንዲህም አለን፥-"በዚያን ጊዜ" ያላት ያችን የምታስፈራዋን የምጽአቱን ቀን ነው።  በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች" አለን። በአሥሩ ደናግላን የተመሰልነው እኛ በጥምቀት ለክርስቶስ የታጭነው ክርስቲያኖችን ነን። ስለሆነም ጌታችን ክርስቲያን መሆናችን ብቻ እንደማያድነን እምነትን ከምግባር፥ እምነትን ከፍቅር ጋር፥ እምነትን ከጦም ከጸሎት ከስግደት ከምጽዋት ጋር አብረን አስተባብረን ይዘን የብርሃን መላእክትን መስለን ራሳችንን ከኃጢአት ጠብቀን የጌታን መምጣት በናፍቆት እንጠብቅ ዘንድ እንዲገባን ሊያስተምረን እንዲህ አለን።

Tuesday, March 21, 2017

ሦስት አጫጭር ጹሑፎች

በዙሪያችን ያሉ መምህራን

አንድ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ልማር ካለ በዙሪያው የሚያስተምሩት አሉለት። ከዋኖቹና ከማይሳሳቱ ሊሳሳቱ እስከሚችሉት መምህራን በቅደም ተከተል ልንገራችሁ ፥-
የመጀመሪያው መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ ልጅነትን ከተቀበልንበት ጊዜ አንስቶ መምህራችን ነው። ሁለተኛው ሥጋው ወደሙ ነው። ሥጋው ወደሙን የሚቀብል ሰው ሁሌም ወደላይ ወደ መላእክት ጉባኤ በመነጠቅ ክርስቶስን ወደ ማወቅ ከፍታ እያደገ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ለሰዎች ሊነገር የማይገባውን ሰምቶ ይመለሳል። ያም ማለት ክርስቶስ ባለበት እርሱ በዚያ ይኖራል። ሌላው ከጠባቂ መላእክት ነው። እነርሱ ከእኛ አይለዩም ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ እንድን ዘንድ ያለንን ማስተዋልንንና እውቀትን በመስጠት ይረዱናል። ያዕቆብን በመከራው ጊዜ የተራዳው እርሱ ጠባቂ መልአኩ ነበር። አብርሃምን ያስተማረው ለዳንኤል እውቀትንና ማስተዋልን የሰጠው እርሱ ነው ሌላው  በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው እነዚህ ለአንድ ኦርትዶክስ ክርስቲያን  ከተጠቀመባቸው መምህራኖቹ ናቸው። ከዚያ በኋላ ልንሳሳት የምንችለው እኛ መምህራን እንከተላለን። 
ቢሆንም ግን ክብር ይግባውና የእግዚአብሔርን ድምጽ  እናውቀዋለንና አዲስም ቢሆን ከእግዚአብሔር የሆነውና ያልሆነውን የምንለይበት ሕሊናና መንፈስ ቅዱስ አለን። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኖ ከእውቀት ባዶ ሆኖ መገኘት ይከብዳል።