ቀን23/03/2010
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ምሁራን ቅዱስ ኤፍሬም የተነሣበት ዘመን ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ በስፋት የበለጸገበት ዘመን ነበር ይላሉ፡፡
በቅዱስ ኤፍሬም ሥነ ጽሑፍ ላይ ተጽዕኖአቸውን ያሳደሩ የሥነ ጽሑፍ ስልቶች እነዚህ ናቸው፡፡
ሥዕላዊ የአገላለጽ ስልት የሚባለው የጥንት ሶርያውያን ክርስቲያኖች የአጻጻፍ ስልት(Mesopotamian mystery of Symbolism)
የአይሁድ የሥነ ጽሑፍ ስልት
የግሪክ ፍልስፍና ናቸው፡፡
ስለዚህ አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምሁር ቅዱስ ኤፍሬምን የሜሶፖቶሚያ፣ የአይሁድ እንዲሁም የግሪክ ሥነ ጽሑፍ መገናኛ ይለዋል፡፡ እነዚህ በአንድነት እንደፈለገ የሚጠቀም ቅዱስ አባት ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ለቅዱስ ኤፍሬም ግን ተችሎት ነበር፡፡
የቅዱስ ኤፍሬም ብዙዎቹ ሥራዎች በመዝሙር መልክ የተዘጋጁ ቅኔአዊ ድርሰቶች ሲሆኑ ይህም የሜሶፖቶሚያው ሥዕላዊ የጽሑፍ ስልትን አብዝቶ እንደሚጠቀም ያሳያል፡፡
የቅዱስ ኤፍሬምን ሥራዎችን ለሦስት ልንከፍላቸው እንችላለን፡
የደረሳቸው መዝሙራት
የጌታችን መዋዕለ ሥጋዌ ላይ ያተኮሩ
ስለጥምቀት ክብረ በዓል የሚያወሱ
ስለዕንቍ ሰባት መዝሙራት(በእምነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው)
ስብከቶች
ስለ ሥጋዌ
ተግሣጽና ስለንስሐ
ስለ ኃጢአተኛዋ ሴት
ትርጓሜያት
ዘፍጥረት አንድምታ
ዘጸአት አንድምታ
ወንጌላት አንድምታ(አንድ ወጥ ሆኖ 170 ዓ.ም በታትያን የተዘጋጀ)
አንዳንዶች የሐዋርያት ሥራንና መልእክታትን እንደተረጎመ ይናገራሉ፡፡ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡ አንድ በቅዱስ ኤፍሬም ሥራ ላይ ጥናት ያደረገ ሰባስቲያን ብሮክ የሚባል ጸሐፊ የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች የሚላቸው አሉ፡፡ እነርሱም፡-
ወደ ፖብሊየስ የተላከ ደብዳቤ (ስለመጨረሻው ፍርድ)
ስለኒቆሞዲያ ስለመሬት መንቀጥቀጥ የሚያወሳ ጽሑፉ ይገኙበታል፡፡
ግሪክ ኤፍሬም
ግሪክ ኤፍሬም የሚባሉ የኤፍሬም አሻራዎች ያረፉባቸው ግን በሶርያ ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ጽሑፎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሥራዎች የቅዱስ ኤፍሬም አይደሉም ወይም የእርሱ አሻራዎች የለባቸውም ማለት ግን እጅግ አስቸገሪ ነው፡፡
እነዚህም፡-
በእንተ ብፁዓን(ሃምሳ አምስት ምዕራፎች አሉት)
የብልጽግና ግምጃ ቤት
ስለ ግብጽ መነኩሳት
ስለ ጦም መዝሙር
በአካለ ሥጋ ስለሌሉ ቅዱሳን አባቶች
ስለ ፍቅር
ማኒን ተቃውሞ የጻፈው ጽሑፍ
መርቂያንን ተቃውሞ የደረሰው ድርሰት ይገኙበታል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ኤፍሬም ከዐራት መቶ በላይ መዝሙራትን የደረሰ ሲሆን ጥቂቶቹ ጠፍተዋል፡፡ የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች ለትርጓሜ እጅግ አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ አስቸጋሪ ያደረጋቸው የጽሑፍ አወቃቀሩ የተወሳሰበ በመሆኑና በቃላት ላይ እጅግ ስለሚራቀቅ እንዲሁም ሥዕላዊ ገለጻዎች ስለሚበዙበት ነው፡፡ ስለዚህም የቅዱስ ኤፍሬምን መልእክት ለመረዳት ጥልቅ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀትና ሕይወቱ እንዲሁም ጥናት ይፈልጋል፡፡
ነገር ግን ጽሐፎቹ ወደ አርመን፣ ቅብጥ(ኮፕት)፣ ግሪክ፣ እንዲሁም ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተመልሶአል፡፡
ምዕራፍ ሁለት
የትርምት ሕይወት
የትርምት ሕይወት (Asceticism) ማለት ራስን ማረቅ መግዛት የሚለማመዱበት ሕይወት ማለት ነው፡፡ የትርምት ሕይወት በክርስቲያናዊ ሕይወታችን አንዱ ክፍል ሲሆን ማንኛውም ክርስቲያን ሊያልፍበት የሚገባ ሕይወት ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እርሱን ሊፈትን የሚተጋ ጠላት አለበትና፡፡ ስለዚህ የዲያብሎስን ውጊያ ድል ለመንሣት አንድ ክርስቲያን የጽድቅን ጡሩር ሊለብስ ወይም የጽድቅን ሕይወት ልማድ ሊያደርግ ግድ ነው፡፡
ለዚህ አብነታችን ራሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ በዕደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ቀጥታ መንፈሰ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳም ነበር የወሰደው፡፡ በዚያም ዲያብሎስን እንዴት እንዋጋው ዘንድ እንዲገባን አስተማረን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን የመጽሐፍ ክፍል ሲተረጉም አንድ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ እንደ አዳም እንደ ኢዮብ በዲያብሎስ ይፈተናል፤ ምክንያቱም ሲጠመቅ የእግዚአብሔር ልጅ ሰለሚሆን ነው፡፡ አዳምን ከገነት እንዳስወጣው እንዲሁ እኛንም በክርስቶስ ካገኘነው የልጅነት ሥልጣን ሊያወጣን ዘወትር ይተጋል ብሎ ያስተምራል፡፡ እውነቱም ይህ ነው፡፡ ለክርስቲያን ከነፍስ የሆነ መታዘዝ እንዲኖረው ሰው በመሆን የሰውን ባሕርይ ያከበረውን የጌታችንን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ሊያከብር ግድ አለበት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ቃል በሥጋና በደም በመካፈል የእኛ ዘመድ ሆኖናልና፡፡