Wednesday, December 20, 2017

ሕግ ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ምንድን ነው?

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/04/2010
ሕግ የእግዚአብሔር ባሕርይንና ፈቃድ የምንለይበት መሣሪያ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል የተፈጠረ ፍጥረት ስለሆነ በባሕርይው የእግዚአብሔርን ባሕርይና ፈቃድ ያውቃል፡፡ ሰው ለባሕርይው አልታዘዝ ሲል የገዛ ተፈጥሮውን ወደ ማጥፋት ይመጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰው በልቡናው ወይም በተፈጥሮ ውስጥ ያኖረውን ሕግ በማጥፋቱ ፈጽሞ ጠፍቶ እንዳይቀር በጽሑፍ ሕግን ሠራለት፡፡ ይህ በጽሑፍ የተዘጋጀው ሕግ የሚያስፈልገው ሕግን ላፈረሱ ኃጥአን እንጂ ለጻድቃን አልነበረም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “ሰው እንደሚገባ ቢሠራበት ሕግ መልካም  እንደሆነ እናውቃለን ይኸውም ለበደለኞች ቅድስና ለሌላቸውና ለርኩሳን ….ሁሉ እንደ ተሠራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሠራ ሲያውቅ ነው ፡፡”(1ጢሞ.1፡8-11) ይላል፡፡ ስለዚህ የጽሑፉ ሕግ የተሰጠን ለእርሱም የአፈጻጸም ሥርዓታት የተሠሩት እኛ ከልቡና ሕግ በመውጣታች ነው፡፡ ጻድቃን ግን ሕግን ሳይጠብቁ ሕግን ይፈጽማሉ፡፡ ይህም እግዚአብሔርንና ባልጀሮቻቸውን ከማፍቀራቸው የተነሣ ነው፡፡ እነርሱ የሚተጉት በትሩፋት ሥራዎች ላይ ነው ፡፡ የትሩፋት ሥራዎች የሚባሉት በምጽዋት፣ ነፍስን በማዳን፣ በንጽሕና በመመላለስ፣ እና በመሳሰሉ ተግባራት ላይ ነው፡፡ ይህንን ከፍቅር ስለሆነ የሚተገብሩት ሕግን እየፈጸሙ እንደሆነ አያስተውሉትም ፡፡ ስለዚህም ጌታችን ቅዱሳንን በምጽአት ስራብ አብልታችሁኛል ስታሰር ጠይቃችሁኛል ብሎ ሲያመሰግናቸው ጌታ ሆይ መች ተርበህ አይተንህ አበላንህ  መች ተጠምተህ አይተንህ አጠጣንህይሉታል ፡፡(ማቴ.25፡35-40) ስለዚህ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ግቡ እግዚአብሔር አምላኩን መምሰል ነው ለዚህም ይተጋል እንደ ትጥቅም የሚታጠቀው ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ነው፡፡ ሰው ለፍቅር ሲገዛ ሕግጋትን አሟልቶ መፈጸም  ይችለዋል፡፡ ሕግ ወደ ፍቅር የሚያደርስ መሠላል እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም ፍጻሜው ክብር ይግባውና በእርሱ አማልክት መሰኘት ነው፡፡

Monday, December 18, 2017

"እንኋት ክርስትና" መጽሐፌ ለኦን ላይን ግዢ በአምዞን ላይ ቀረበች


እነሆ የማኅበረ ቅዱሳን ኤዲቶሪያል ቦርድ በመጽሐፏ ላይ የሰጠውን አስተያየት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ታርማና ተስተካክላ የተዘጋጀች እንኋት ክርስትና መጽሐፌ በአማዞን እንዲህ ሆና ቀርባለች። በተለይ በብሎጌ ላይ ጽሑፎቼን የምትከታተሉ በአሜሪካ፥  በአውሮፓ   ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ፥ በሩቅ ምሥራቅ ያላችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ ይህችን መጽሐፌን አሁን ገዝታችሁ በእጃችሁ ማስገባት እንደምትችሉ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። በዚህ ሥራ የተራዳኝን በተለይ መራዊ በጽሐን እንዲሁም የመጽሐፉን ሽፋን እንደገና አርሞ በመሥራት የረዳኝ ወንድሜ አንዷለምን በድንግል ስም ሳላመሰግን አላልፍም።

ከምዕራፍ አንድ ላይ የተቀነጨቡ

 ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባንን አስመልክቶ በሶርያ ቅዱሳን አባቶች በጥቂቱ


እነዚህ የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ይህን ፅንሰ አሳብ በማዳበር ብዙ የጻፉ ሲሆኑ ባለራዕይው ዮሴፍ የተባለው ቅዱስ አንድ ክርስቲያን በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሲታዘዝ በሰውነቱ የሚከሰቱ ለውጦችን ደረጃ በደረጃ ጽፎልን እናገኛለን ፡፡

……..“አንድ ክርስቲያን በሰውነቱ ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ ሥራ መጀመሩን የሚረዳው  በልቡ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንደ እሳት መቀጣጠል ሲጀምር ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሣ ዓለማትን እንደ ፈጠረ ወደ ማስተዋል ይመጣል፡፡ ከዚህም ስለእግዚአብሔር ፍቅር ሲባል ለእግዚአብሔር መለየትና የትህርምት ሕይወትን ወደ መምረጥ ይመጣል፡፡ እነዚህ ሁለቱ የመልካም ሥነምግባራት እናቶች ናቸው፡፡ ወንድሜ ሆይ ሁለተኛው መንፈስ ቅዱስ በአንተ ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምትገነዘበው እውነተኛ የሆነው ትሕትና በአንተ ሲወለድ ነው፡፡ እንዲህ ስልህ ለታይታይ በሥጋ የሚገለጠውን ትሕትና ማለቴ ግን አይደለም ፡፡ በእኛ ባደረው መንፈስ ቅዱስ ድንቅ የሆነ ሥራ እየተፈጸመ ነገር ግን ራሳችንን እንደትቢያና አመድ የተናቅን አድርገን የምንቆጥርና ከሰው ተርታ የማንመደብ አድርገን  የምንመለከት ከሆነ በእርግጥ እውነተኛይቱትሕትና በእኛ ውስጥ ተወልዳለች ፡፡ (መዝ.፳፩፥፮) ይህ ትሕትና ራስን በእግዚአብሔር ፊት በመመልከት የሚወለድ ትሕትና ነው፡፡

Wednesday, December 13, 2017

የትርምት ሕይወት በቅዱስ ኤፍሬም(ክፍል ዘጠኝ) ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
04/04/2010
ወደ ቅድስና ሕይወት የሚመሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን አድኖ ማንበብ አንዱ በትርምት ሕይወት ውስጥ የሚኖር ክርስቲያን ጠባይ ነው፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች ክርስትናን በሕይወት ስለኖሩባት በጽሑፎቻቸው ሁሉ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል ከዲያብሎስ ጋር በምናደርገው ፍልሚያ ምን ማድረግ እንዳለብን በስፋት ጽፈውልን እናገኛለን፡፡
ቅዱስ ኤፍሬምም ከዲያብሎስ ወጥመድ ለማምለጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጸሎትና ራስን ሰብስቦ በጥንቃቄ ማንበብ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡ ቅዱስ አፍሬም እንደህ ማለቱ ዲያብሎስ አንባብያን የሚጠቅማቸውን ሰማያዊ ዕውቀት ከሚያነቡት መንፈሳዊ መጽሐፍ እንዳያገኙ ተግቶ ስለሚሠራና መልእክቱን አዛብተን በመረዳት ወደ ምንፍቅና እንዲንደረደሩ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡ ስለዚህ የንባብ ሕይወታችን እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግና በማስተዋል መፈጸም እንዳለበት ያሳስባል፡፡ እርሱም ሰይጣን እንዲህ አለ ብሎ በጻፈልን ጽሑፍ ላይ ይህንን እናስተውላለን፡፡
“እኔ ሰይጣን ስንፍናቸውን እንደሰንሰለት ተጠቅሜ ሰዎችን አ