Saturday, March 3, 2012

ሴቶች ሊያውቁዋት የምትገባ እውነት!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
24/06/2004
ዛሬ ባነሣሁት ጭብጥ ላይ:- ደግሞ ምን አመጣህ? ትሉኝ ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ፍጥጥ ያለ እውነትና እውቀት ነው፡፡ ይህቺ እውነት እናቶቻችን፡- "ድሮ አግኝተናት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይህች ዓለም የአውሬዎች መፈንጫ ባልሆነች ነበር" ብለው የሚቆጩባት እውነት ናት፡፡ ይህቺ እውቀትና እውነት ፡-  ዓለምን ሴቶች ይገዙአትና ይመሩዋት ዘንድ ተፈጠረች የምትል ናት፡፡ መቼም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብላችሁ በመገረም ትጠይቁኝ ይሆናል፡፡ እውነቱና ሐቁ ግን ይህ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሴት ልጅ ገነትን እንደራሱዋ ሃሳብና ጥቅም ትመራትና ትጠቀምባት ዘንድ በዚህም እርፍ ብላ ትኖርባት ዘንድ አዳምን ጨምሮ ሁሉን አደላድሎ ከፈጠረ በኋላ የፍጥረት ሁሉ ዘውድ አድርጎ ከአዳም አስገኛት፡፡ አዳም አስቀድሞ በሥጋ መገለጡ ለእርሱዋ በእግዚአብሔር ፈንታ ሆኖ ገነትን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንደምትችል ያስተምራት ዘንድ ነበር፡፡ በእርግጥም አዳም ይህን ፈጽሞላታል፡፡ ስለዚህም ነው ሰይጣን እርሱዋን በተንኮል “በእውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ በጠየቃት ጊዜ “በገነት ካለው ዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ፡-እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም”ብላ መመለሱዋ፡፡(ዘፍ.3፡2-3)

Thursday, March 1, 2012

ገነት በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/06/2004
በዚህ መዝሙር ቅዱስ ኤፍሬም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን ዓለት በማንሣት እግዚአብሔር ፍጥረታትን እንዴት እንደፈጠራቸውና ስለገነት ያለውን አስተምህሮ እንመለከታለን፡፡

እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን አለትን አስታውሼ ዓለማትን የፈጠረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልብ አልኩ፡፡ እንደ ታላቅ ወንዝ ለእነርሱ ከአለቱ ውስጥ የፈለቀው ውኃ በውስጡ ካለው የውኃ ቋት የተገኘ አልነበረም ፡፡ በአለቱ ውስጥ አንድም ጠብታ ውኃ የለም፤ ነገር ግን ልክ የእግዚአብሔር ቃል ፍጥረትን ከምንም እንዳስገኛቸው፤እንዲሁ ታላቅ የውኃ ጅረት ከደረቅ ድንጋይ ውስጥ ፈልቆ የተጠሙትን አረካቸው፡፡
ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ተፈጥሮ ገልጦ ጽፎልናል  ስለዚህም ተፈጥሮና መጽሐፍ ቅዱስ ስለፈጣሪ ምስክሮች ሆኑ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለራሱ ጥቅም ሲገለገልባት እንደሚያውቃት እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ በውስጡ የያዘውን መረዳት ይቻለናል እነዚህን ሁለቱን ምስክሮች በሁሉ ስፍራ እናገኛቸዋለን፡፡





Monday, February 27, 2012

ዕንቁ፣ ክርስቶስና ኢትዮጵያ በቅዱስ ኤፍሬም




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
20/06/2004
መግቢያ
ለቅዱስ ኤፍሬም አንድ ወቅት ደቀመዛሙርቱ ዕንቁ ያመጡለታል፡፡ እርሱም ዕንቁውን በተመለከተ ጊዜ ሰማያዊ ምስጢር ተገለጠለት፡፡ ስለዚህም በዕንቁ ነገረ ሥጋዌውንና በጥምቀት ያገኘነውን ክብር ሰበከ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ዕንቁን መሠረት አድርጎ ሰባት መዝሙራትን የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ድርሰቶቹ ውስጥ ለአሁኑ ስለኢትዮጵያና ስለንግሥት ሳባ እንዲሁም ስለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሚያወሳውን ሦስተኛውን መዝሙር ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ፡፡

አንተ ዕንቁ ሆይ! ሰውነትህ ከልብስ የተራቆተ ነውና ራስህን መሰወር እንዴት ይቻልሃል? ነጋዴዎች አንተን ከማፍቀራቸው የተነሣ ከልብስ ተራቆቱ፤ ነገር ግን እነርሱ ከልብስ መራቆታቸው የአንተን ራቁትነት በልብሳቸው ለመክደን ሲሉ አልነበረም፡፡ አንተ ምንም እንኳ ከልብስ የተራቆትክ ብትሆን ከውስጥህ የሚፈልቀው ብርሃን ልብስህ ነው፤ መጎናጸፊያህም የብርሃኑ ነጸብራቅ ነው፡፡ ኦ አንተ ዕንቁ ሆይ! ግሩም የሆነው ባሕርይ እንዴት ድንቅ ነው!!
ከስህተት በፊት ሔዋን በገነት ሳለች ምንም እንኳ ከልበስ የተራቆተች ብትሆንም ልክ እንዳንተው ብርሃንን የተጎናጸፈች ውብ ነበረች፡፡ ከዚህ ልብሱዋ ያራቆትካት አንተ ሰይጣን ሆይ ርጉም ሁን፡፡ ጌታ ሆይ! ዕንቁው ያንተ ምሳሌ ነው ፤ አንተን ግን ይህ ሰይጣን ከዚህ ልብስህ ሊያራቁጥህ አይቻለውም፡፡ አሁን በገነት ሴቶች እንደዚህ ዕንቁ ብርሃንን ተጎናጽፈው የቀድሞዋን ሔዋንን መስለዋታል፡፡