Friday, June 1, 2012

"አባታችን ሆይ"በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (ክፍል ሦስት)


‹‹መንግሥትህ ትምጣ››
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
25/09/2009
ይህም በጎ ሕሊና ያለው ሰው ጸሎት ነው፡፡ እንዲህ ዐይነት ሰው በዐይን በሚታዩ ምድራዊ ነገሮች የሚማረክ ሰው አይደለም፡፡ ወይም ይህን የሚታየውን ዓለም እንደ ትልቅ ቁምነገር የሚቆጥረው ሰው አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደ አባታችን በጸሎት ይፋጠናል፡፡ከእግዚአብሔር ዘንድ የምትሰጠውንም መንግሥት ይናፍቃል፡፡ ይህ ፈቃድ ከመልካምና ከምድራዊ አመለካከት የተለየ ሕሊና ካለው ሰው ዘንድ የሚገኝ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሕይወት ዘወትር ይናፍቀው ነበር፡፡ ስለዚህም‹‹… የመንፈሱ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን››(ሮሜ.፰፡፳፫ )ብሏል፡፡ እንዲህ ዐይነት ናፍቆት ያለው ሰው በዚህ ምድር ባገኛቸው መልካም ነገሮች ራሱን አያስታብይም ወይንም በጽኑ መከራ ውስጥ ቢሆንም ከመከራው ጽናት የተነሣ አይመረርም ፡፡ ነገር ግን ወደ ሰማይ ወደ እረፍቱ ቦታ እንደገባ ሰው ምስቅልቅል ከሆነው ከዚህ ዓለም ሕይወት ነፃ የወጣ ሰውን ይመስላል፡፡


Thursday, May 31, 2012

‹‹አባታችን ሆይ››በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ(ክፍል ሁለት)


v በጸሎታችሁ አሕዛብን አትምሰሉአቸው
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/09/2004
በመቀጠል ጸሎታቸንን እንዴት ማቅረብ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ ‹‹አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደነርሱ በከንቱ አትድገሙ›› (ማቴ.፮᎓፯)አለ፡፡...
ጌታችን ከዚህ አስቀድሞ ጸሎትን በተመለከተ ደግሞ ደጋግሞ አስተምሮ ነበር፡፡ በዚህም ቦታ አስቀድሞ ጻፎችና ፈሪሳውያንን እንደወቀሳቸው ሁሉ ‹‹በከንቱ አትድገሙ›› በማለት አሕዛብን ወቀሳቸው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ወገኖችንም አሳፈራቸው፡፡
ጌታችን በትምህርቱ የምንሳብባቸውንና እኛም ልንፈጽማቸው የምንጓጓላቸውን ነገሮች ጎጂነት ነቅሶ በማውጠት አስተማረን፡፡ ምክንያቱም እኛ ሰዎች ስንባል በውጫዊ ገጽታቸው አምረውና አሸብርቀው በሚታዩ ነገሮች በቀላሉ ስለምንሳብ፣ በውጭ ሲታዩ ጻድቃን የሚመስሉትን ግብዞችን  መስለን መመላለስን ስለምንመርጥ ነው፡፡

Wednesday, May 30, 2012

‹‹አባታችን ሆይ››በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ(ክፍል አንድ)


                          
v ግብዞችን አትምሰሉአቸው
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/09/2004
ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባና መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጽ  ይከፍልሃል፡፡››(ማቴ.፮᎓፩−፮)
በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፎችንና ፈሪሳዊያንን ግብዞዎች ማለቱ አግባብነት ነበረው፡፡ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ቤት ለጸሎት በሚመጡበት ጊዜ የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ ከሥርዐት የወጣ አለባበስን ይለብሱ ነበር እንጂ ለጸሎት ተስማሚ የሆነውን የትሕትና አለባበስን አይለብሱም ነበርና ነው፡
ለጸሎት ወደ አምላኩ የሚቀርብ ሰው ሌሎች ጉዳዮቹን ሁሉ ወደ ኋላ ትቶና ከሰው ዘንድም ምስጋናንና ክብርን ሳይሻ ጸሎቱን ተቀብሎ ወደሚፈጽምለት አምላኩ ብቻ ትኩረቱን ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ይህን መፈጸም ትተህ አይኖችህን  የትም የምታንከራትት ከሆነ ከእግዚአብሔር ቤት በባዶ እጅህ ምንም ሳታገኝ እንድትመለስ እወቅ፡፡ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ዋጋ ማግኘትና ማጣት በእጅህ የተሰጠ የአንተ እድል ፈንታህ ነው፡፡ ስለዚህ ከንቱ ውዳሴን የሚሹ ሰዎች ከእኔ ዘንድ አንዳች አያገኙም አላለም ፡፡ነገር ግን‹‹ ዋጋቸውን ተቀብላዋል››አለ፡፡