Monday, August 31, 2015

የተመሰገነችው ድህነት በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
25/12/2007

ቅዱስ ጳውሎስ "ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።"(1ጢሞ.6:6-8) እንዳለው ክርስቶስን በመሰለና ለራስ በቂ በሆነ ሕይወት ውስጥ በመገኘት ናት በቅዱስ ኤፍሬም የተወደደችው ድህነት።
 ይህቺ ድህነት ሙሉ ትኩረትን እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚረዱ ተግባራት መኖርን ትጠይቃለች።ይህ ነው ለቅዱስ ኤፍሬም ድህነት የሚለው ቃል ትርጉሙ።  ድህነት የሥጋ ድህነት ማለት አይደለም ለቅዱስ ኤፍሬም ይህ እንዳልሆነ እርሱ ራሱ በቃሉ  "ለሥራ ከመትጋት አትለግም ምንም እንኳ ባለጠጋ ብትሆን፥ ሰነፍ ሰው በሥራ ፈትነቱ  የተነሣ ቁጥሩ የበዛ ኃጢአትን ይፈጽማታልና" ብሎ ይመክራል። ስለዚህ ድህነት ማለት ለቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ከሆነ ድህነት ሳይሆን ድኅነት ነው።

Tuesday, July 14, 2015

እድሜ ይስጥልኝ ብያለሁ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

07/11/2007

እንደ መንፈሳዊ መረዳት ድንቅ የሚለኝና የሥነ ተፈጥሮአችን አንዱና መሠረታዊ ክፍል  ስለሆነው ነገር ልንግራችሁ። ከእናት ማኅጸን ሥጋችን ከነፍሳችን ጋር ተዋሕዳ ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ ወደ እርጅናና ሞት ስታዘግም ነፍሳችን ግን እለት እለት እየታደስችና በእውቀት ሙሉ እየሆነች በመምጣት ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው እርሷ በእግዚአብር ዘንድ  እንደታወቀች እስክታውቅ ድረስ ደርሳ ፍጹም ወደ መሆን ታድጋለች። የዛኔ እግዚአብሔር አምላኩዋን አባ አባ ስትለው በፍጹም ልጅነት መንፈስ ሆና ነው። እንዲህ በመሰለ መንፈሳዊ ከፍታ እያደገ የሚመጣው ግን ሰሎሞን "ጥበብ" ያለው  ሲወድቅም ሲነሣ ያልራቀው  የእግዚአብሔር መንፈስ ከእርሱም ጋር የሆነለት ሰው ብቻ  ነው። 

Friday, July 10, 2015

ክርስቶስ የማይታየው አምላክ ምሳሌ የመባሉ ምክንያት



በዲ/ን   ሽመልስ መርጊያ
3/10/2007
ሕዝቅኤል እግዚአብሔር ለእርሱ እንዴት እንደተገለጠለት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር "በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።  በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።"(ሕዝ.1:26-28)