Thursday, December 7, 2017

የትርምት ሕይወት በቅዱስ ኤፍሬም (ክፍል ስምንት)


በመ/ር ሽመልስ መርጊያ
29/03/2010

ለቅዱስ ኤፍሬም ድህነት ማለት ሁሉ የሚገኝባት ሰማያዊ ግምዣ ቤት ናት፡

“በዚህች የከበሩ ነገሮች ሁሉ በሚቀመጡባት ግምዣ ቤተ ተደነቅሁ፤ በውስጧ ያሉ የከበሩ ሀብታት ሁሉ ከሁሉ ይልቅ ክቡራን ናቸው፡፡  ከሀብቶቿ ሊያጎልባት የሚችል አንድም ሰው የለም፡፡ ለዚህች ግምዣ ቤት የብዕሏ ምንጭ ድህነት ናት ፡፡ ነገር ግን ሰዎች በዙሪያዋ ከትመውባታል ከዚህች ግምጃ ቤት ሃብትም ይናጠቃሉ፡፡ ንጥቂያ እንደመሆኑ መጠን ብዙዎች ባለጠጎች ሆኑባት፡፡ በዚች ሕይወት ለጸኑትና አጥብቀው ላሿት ሀብቷ በኃይልና በብዛት ይፈሳል” በማለት ድህነትን የሰማያዊ ሀብት ግምዣ ቤት እንደሆነች ሲሰብክ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ከዚህ ሀብት ይናጠቁ ዘንድ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በሁሉ ሊመስሉ ይገባቸዋል፡፡ እርሱ ነውና የጸጋ ሁሉ ግምጃ ቤት ባለቤቱ፡፡ እርሱን ስንመስል ከእርሱ ዘንድ ባለ ሰማያዊ ሀብት ባለጠጎች እንሆናለን፡፡ የዚህንም አላፊ ጠፊ የሆነውን ዓለም ሀብት እንድንንቀው ያደርገናል፡፡ በዚህ ሕይወት ከተገኘንም መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ይመራዋል፡፡ እንዴት መኖር እንዳለብንም እወቀቱ ከእርሱ እናገኛለን፡፡

Friday, December 1, 2017

የቅዱስ ኤፍሬም ልዩ የሆኑ መንፈሳዊ ጠባያት(ካለፈው ይቀጠለ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/03/2010
የቅዱስ ኤፍሬም መንፈሳዊው ሕይወት የሚጀምረው የንጽቢኑ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን ከቃል ኪዳን ልጆች ኅብረት ጋር ካቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ ለቅዱስ ኤፍሬም በቃል ኪዳን ልጆች ይተገበር የነበረው የትርምት ሕይወት እርሱን ከእግዚአብሔር አምላኩ ጋር እንዲጣበቅና ልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት ለማንበብና ለማጥናት ረድቶታል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም እግዚአብሔርን የሚያፈቅር ክርስቲያን ሆነ፡፡ እስቲ ልዩ የሆኑ የቅዱስ ኤፍሬም መንፈሳዊ ጠባያት የተወሰኑትን እንመልከት፡-
ጸሐፊነቱ
ከስበከት ሥራው ጎን ለጎን መንጋውን በመንፈሳዊው እውቀት የበሰሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ቅዱስ ኤፍሬም ስብከቶችን፣ መዝሙራትንና ትርጓሜያትን ለመንጉቹ ይጽፍላቸው ነበር፡፡ ጽሑፎቹ ሁሉ የትርምት ሕይወት ተጽእኖ ስላለባቸው በየጣልቃቸው ጸሎታት አሏቸው፡፡ ወይም ሙሉ ለሙሉ የጸሎት መጽሐፍ ናቸው፡፡ በሚጽፍበትም ጊዜ ራሱን በእግዚአብሔር ፊት እንደቆመ በማሰብ ነው፡፡  መንጎቹን ሳይሰለች የሚጠብቅ ስለሆነ በሕይወቱ ጌታችን ለቅዱስ ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው”(ዮሐ.21፡15) የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ ፍቅር ሆኖ እግዚአብሔርን በመፍራት መንጋውን ይጠበቅ ስለነበረ ነው፡፡ እርሱ መንጋውን ሲጠብቅ ሁሉን ነገሩን ሰጥቶ ነበር፡፡
የሴቶችን እኅቶቻችን መበት ተሟጋች ነበር

የትርምት ሕይወት በሶርያ ቅዱሳን አባቶች (ካለፈው የቀጠለ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን23/03/2010
ከላይ ለማስረዳት እንደተሞከረው የሶርያ ክርስቲያኖች የትርምት ሕይወትን አስመልክቶ የጌታችንን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ ሐዋርያት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው አምላካቸውን በጦም በጸሎት ሆነው ሲያመልኩ በነበሩበት ሥርዓት ይመላለሱ ነበር፡፡ በአንዳንድ ምሁራን ዘንድም የእነርሱን የትርምት ሕይወት ከገዳማዊ ሕይወት በፊት የነበረ የምንኩስና ሕይወት ይሉታል፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንዳንለው ደናግላን ብቻ ሳይሆኑ ያገቡትም ይህን ሕይወት ገንዘባቸው አድርገው ይመላለሱ ነበር፡፡ እነዚህ የቃል ኪዳን ልጆች የተባሉት ጌታችን “ነገር ግን ልባችሁ ... ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”(ሉቃ.21፡34) እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ “ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ”(1ቆሮ.7፡29) እንዲል የጌታን ምጽአት አስበው በፍጹም ተመስጦ ለመንፈሳዊው ሕይወት ቅድሚያ በመስጠት በጦም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በትጋእ ሌሊት፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብ ጽሙድ ሆነው በተግባራዊ ሕይወታቸውም ከኃጢአት ተጠብቀው ነፍሳቸውን በጽድቅ ሕይወት አስጨንቀው ይመላለሱ ነበር፡፡ ይህ ሕይወት ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን ሊኖረው የሚገባው ሕይወት ቢሆንም በዘመኑም ቢሆን በዚህ ሕይወት የሚኖሩት ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ያለ ምርጫ ያገባውም ያላገባውም የሚኖረው ሕይወት ነበር፡፡