Thursday, May 31, 2012

‹‹አባታችን ሆይ››በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ(ክፍል ሁለት)


v በጸሎታችሁ አሕዛብን አትምሰሉአቸው
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/09/2004
በመቀጠል ጸሎታቸንን እንዴት ማቅረብ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ ‹‹አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደነርሱ በከንቱ አትድገሙ›› (ማቴ.፮᎓፯)አለ፡፡...
ጌታችን ከዚህ አስቀድሞ ጸሎትን በተመለከተ ደግሞ ደጋግሞ አስተምሮ ነበር፡፡ በዚህም ቦታ አስቀድሞ ጻፎችና ፈሪሳውያንን እንደወቀሳቸው ሁሉ ‹‹በከንቱ አትድገሙ›› በማለት አሕዛብን ወቀሳቸው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ወገኖችንም አሳፈራቸው፡፡
ጌታችን በትምህርቱ የምንሳብባቸውንና እኛም ልንፈጽማቸው የምንጓጓላቸውን ነገሮች ጎጂነት ነቅሶ በማውጠት አስተማረን፡፡ ምክንያቱም እኛ ሰዎች ስንባል በውጫዊ ገጽታቸው አምረውና አሸብርቀው በሚታዩ ነገሮች በቀላሉ ስለምንሳብ፣ በውጭ ሲታዩ ጻድቃን የሚመስሉትን ግብዞችን  መስለን መመላለስን ስለምንመርጥ ነው፡፡

Wednesday, May 30, 2012

‹‹አባታችን ሆይ››በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ(ክፍል አንድ)


                          
v ግብዞችን አትምሰሉአቸው
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/09/2004
ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባና መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጽ  ይከፍልሃል፡፡››(ማቴ.፮᎓፩−፮)
በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፎችንና ፈሪሳዊያንን ግብዞዎች ማለቱ አግባብነት ነበረው፡፡ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ቤት ለጸሎት በሚመጡበት ጊዜ የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ ከሥርዐት የወጣ አለባበስን ይለብሱ ነበር እንጂ ለጸሎት ተስማሚ የሆነውን የትሕትና አለባበስን አይለብሱም ነበርና ነው፡
ለጸሎት ወደ አምላኩ የሚቀርብ ሰው ሌሎች ጉዳዮቹን ሁሉ ወደ ኋላ ትቶና ከሰው ዘንድም ምስጋናንና ክብርን ሳይሻ ጸሎቱን ተቀብሎ ወደሚፈጽምለት አምላኩ ብቻ ትኩረቱን ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ይህን መፈጸም ትተህ አይኖችህን  የትም የምታንከራትት ከሆነ ከእግዚአብሔር ቤት በባዶ እጅህ ምንም ሳታገኝ እንድትመለስ እወቅ፡፡ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ዋጋ ማግኘትና ማጣት በእጅህ የተሰጠ የአንተ እድል ፈንታህ ነው፡፡ ስለዚህ ከንቱ ውዳሴን የሚሹ ሰዎች ከእኔ ዘንድ አንዳች አያገኙም አላለም ፡፡ነገር ግን‹‹ ዋጋቸውን ተቀብላዋል››አለ፡፡

Thursday, May 24, 2012

ፍቅር (ፆታዊ ፍቅር)



ፍቅር ማለት ምን ማለት ነው?
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/09/2004
ፍቅር ማለት እንዲህና እንዲህ ማለት ነው ብሎ ትርጉም ሰጥቶ መናገር እጅግ የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የሰዎች ቋንቋ ስለ ፍቅር ትርጉም ለመስጠት አቅም የለውምና ነው፡፡ እንዲህ ሲባል የሰዎች አእምሮ አይረዳውም ማለት ግን አይደለም፡፡ ከመገለጫዎቹ ተነሥተን ስለፍቅር ትንታኔ መስጠት ይቻለናል፡፡ ይህ ማለት ግን ስለፍቅር የተሟላ ትርጉም አግኝተንለታል አያሰኘንም፡፡ የፍቅር ትርጉም እንደውቅያኖስ እጅግ ጥልቅና ሰፊ ነው፡፡ ጎርጎርዮስ ዘፓለማስ የሚባሉ አባት የእግዚአብሔር ባሕርያትን አይመረመሬነት ለማስረዳት ሲሉ ባሕርይውን በጨለማ ይመስለዋል፡፡ የእግዚአብሔር ባሕርይን መርምሮ ሊደርስበት የሚችል ከፍጡር ወገን የለም፡፡ ከእግዚአብሔር ባሕርያትም አንዱ ደግሞ ፍቅር ነው፡፡ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” እንዲል፡፡ (1ዮሐ 4.9) ፆታዊውም ፍቅር በእግዚአብሔር ባሕርይ ውስጥ ላለው ፍቅር ምሳሌ ነው፡፡


Tuesday, May 22, 2012

“ዕንቁ ክርስቶስ በቅዱስ ኤፍሬም”



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/09/2004

ከዕለታት በአንዱ ቀን ከወንድሞቼ በስጦታ ዕንቁ ተቀበልኩኝ፤ በዚህ ዕንቁ ውስጥ ታላቅ የመንግሥቱን ምሥጢርንና የገዢው የክርስቶስን ምሳሌ ተመለከትኩ፡፡ ዕንቁ ለእኔ ጥሩ የውኃ ምንጭ ሆነልኝ ፤ከዚህም ምንጭ የእግዚአብሔር ልጅን ምሥጢር ጠጥቼ ረካሁ፡፡
ወንድሞቼ ሆይ የሰጣችሁኝን ዕንቁ እመረምረው ዘንድ በማሃል እጄ ያዝኩት ፡፡ ወደ ዐይኖቼም አቅርቤ ዙሪያውን ተመለከትኩት እናም ይህ ዕንቁ በሁሉም አቅጣጫ ዐይኖች እንዳሉት አስተዋልኩ፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስን ብርሃን ነው ብንልም ፈጽሞ ልንመረምረው እንደማንችል ተረዳሁ፡፡
በዕንቁ ብሩህነት በባሕርይው ምንም ጨለማ የሌለበትን የእግዚአብሔር አብ ብቸኛ ልጁን ተመለከትኩ፡፡ በእርሱም ውስጥ ግሩም የሆነውም ንጽሕናውን አስተዋለኩኝ፤ ከእኛም የነሣውንም ሥጋ ቅድስናውንና ንጽሕናውን ተረዳሁ፡፡ በዚህ ዕንቁ ውስጥ ያየውትን ያለመከፈል አንድ የሆነውን የሥጋንና የመለኮትን ተዋሕዶ ተመለከትኩ፡፡
በዕንቁው ውስጥ እንዲሁ የእርሱን ንጹሕ የሆነውን ፅንሰት አስተዋልኩ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በምትሰኘው ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን የተፈጸመውን የእግዚአብሔር ልጅ ፅንሰትን ተረዳሁ፡፡ እርሱዋ እርሱን የተሸከመችው ደመናው ናት፡፡ የእርሱዋም ምሳሌ ሰማይ ነው፡፡ ከእርሱዋም የጽድቅ ፀሐይ በመውጣት ለዓለም አበራ፡፡


ሠርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እይታ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ 
14/09/2004
ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትምህርትን ሰጥቶአል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችንና ሁካታዎችን አጥብቆ የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል ልንመጣም እንችላልን ፡፡    
"...ትዳር ምንድን ነው? ትዕይንት(ትያትር) ነውን? አይደለም፡፡  ምንም እንኳ እናንተ ለትዳርና ለምሳሌው አክብሮት ባይኖራችሁ እንኳ ትዳር ግሩም ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው” ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና ስለቤተክርስቲያን እላለሁ” ይላል፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተክርስቲያንና የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤ እንዲህ በከበረ ምሥጢር ላይ ዳንኪረኞችን በመጋበዝ ዝሙትን ታስተዋውቃላችሁን ? ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግላን ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነውን ? እንግዲያስ እነርሱ በዚህ ሠርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ፡፡ የእኔ መልስ ማንም አይጨፍር የሚል ነው ፡፡

Monday, May 21, 2012

“መስቀል ለእኔ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/09/2004
መስቀል ስል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ያን መስቀል ማለቴ ነው፡፡ እንዲያም ሲሆን ደግሞ እንደመንፈሳዊ ትርጉሙ እንጂ  እንደ ሥጋዊያን አይደለም አረዳዴ፡፡ እነርሱ በመስቀሉ ክርስቶስን አይመለከቱትም፤ በክርስቶስ ደግሞ የመስቀሉን መንፈሳዊ ትርጉም አይረዱት ቁሳውያን ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር የእውቀቱን ደጅ ይክፈትላቸው፡፡ ታመዋል ወይም እነዚህ ወገኖች ጣዖት አምላኪያን ሆነዋል፡፡ ሰዎችን እንዲህ እንዲስቱ  የሚያደርጋቸው ደግሞ ሰይጣን ነው፡፡ የእርሱ ፈቃድ በምንም ዓይነት መንገድ የክርስቶስ ስም እንዳይጠራ ማድረግ ነው፡፡ አቤቱ አምላኬ ስለምወዳቸው ስለእነዚህ በአመለካከታቸው  ገና ወተት ላይ ላሉት ማስተዋልን ስጣቸው፡፡ ፈቃድህን ተረድተው እንደተርብ ከመናደፍ እንዲመለሱ እርዳቸው፡፡ መስቀል ለእኔ መንግሥተ ሰማያት ማለት ነው ከጌታዬ ከአምላኬ ከአባቴ ከአፍቃሪዬ ከክርስቶስ ጋር የምኖርበት ቤቴ ነው፡፡
በመስቀሉ ለክርስቶስ ኢየሱስ አፍቃሪያን ሁለት ምግቦች ተሰጥተዋል፡፡ አንደኛው ፍቅር ነው፡፡ሁል ጊዜ ወደ መስቀሉ ስመለከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ስለማፍቀሩ የተቀበለውን ጽኑ መከራ አስባለሁ፡፡እኛን ለማዳን ሲል የተቀበለውን መከራ ሳስብ ደግሞ ጥልቅ የሆነውን ፍቅሩን አስተውለዋለሁ፡፡ ስለእኛ መሞቱ ግድ ቢሆንም የተቀበለውን መከራ ሳስታውስ በከባድ ኃዘን ውስጥ እወድቃለሁ፡፡ ኃጢአቴም ትዝ እያለኝ የተዋለልኝን ውለታ ዘንግቼ እርሱን ጌታዬን በማሳዘኔ ቁጭት ሃዘን ይነግሥብኛል፡፡ በዚህም ምክንያት እኔ ከልጆቹ ልቆጠር የማይገባኝ ሲኦል ስለኃጢአቴ የምታንሰኝ እንደሆነች ሆና ትሰማኛለች፡፡ ኦ ፍቅርን እኮ ነው የበለደልኩት!!!


Monday, May 7, 2012

የአዳም እናትነት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/08/2004
አምላኬ ሆይ አንተ ስለኢየሩሳሌም ጥፋት አዝነህ “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶቹዋን ከክንፎቹዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ አልወደዳችሁምም”(ማቴ.23፡37) ብለህ በተናገርከው ኃይለ ቃል   የአዳምን እናትነት ልብ አልኩኝ፡፡
ጌታችን አዳምን ከምድር አፈር አበጅቶ የሕይወት አስትንፋስን እፍ አለበት፤ በዚህም ምክንያት አምላኩን መሰለ፡፡ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ በእርሱ አርአያና አምሳል ሔዋንን በማበጀት በአካል እንድትገለጥ አደረጋት፡፡ ከዚህም በኋላ ከእነርሱ የሚገኙ ሁሉ እነርሱን እንዲመስሉ እነርሱ ያላቸውን ሕይወት ሕይወታቸው አድርገው እንዲኖሩ በእነርሱና በዘሮቻቸው የልጅ ልጆቻቸውን ሁሉ ፈጠረ፡፡ እንዲህ በመሆኑም የአዳም ቅድስና ለእነርሱ ሕያውነት፤ የእርሱ ውድቀት ለእነርሱ ውድቀት ሆነ እንጂ ልክ እንደ መላእክት አንዱ ቢወድቅ ሌላው ጸንቶ በመቆም የሚድን አልሆነም፡፡ ስለዚህም አዳም ወደቀ እኛም የእርሱ የውድቀቱ ተጋሪዎች ሆንን፡፡ እግዚአብሔር በረድኤት ከአዳም ሲለይ ከእኛም በረድኤት ተለየ፡፡ ምንም እንኳ የአዳምና የሔዋን ኃጢአት ተባባሪዎች ባንሆንም የውድቀታቸው ተጋሪዎች ሆንን፡፡ ምክንያቱም በአዳም አንድ ሰው ሆነን ተፈጥረናልና፡፡