በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/08/2004
ቅዱስ ይስሐቅ ሰው በክፉም ይሁን
በደግ ዐይኖቹ መታወራቸው አይቀርም ይለናል፡፡ በኃጢአት ውስጥ ያለ ሰው ዐይኖች ጽድቅን ማየት ይሳናቸዋል፡፡እንደነዚህ ዐይነት ወገኖች የሰዎች ኃጢአት እንጂ
የጽድቅ ሥራቸው ወይም መልካም የሆነው ተፈጥሮአቸው አይታያቸውም፡፡ ነገር ግን የጻድቅ ሰው ዐይኖች የሰዎችን ድክመትም ሆነ ነውር
ወይም ኃጢአት አይመለከቱም፡፡ሁሉም በእነርሱ ዘንድ ብሩካን ናቸው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ኃጥእ ጽድቅን አያቃትም ማለት ሳይሆን ወደ
ኃጢአት ፈቃድ ያደላል ሲለን ነው፡፡ እንዲሁ ጻድቅ ሰውም የሰዎች ጉድለትና ድክመት ወይም ኃጢአት ሳይሆን አስቀድሞ የሚታየው የእነርሱ
መልካምነት ነው፡፡
ጻድቅ ሰው የሰውን ደካማ ጎን ሳይሆን ጠንካራውን ይመለከታል፤ ስለዚህም
በዐይኑ ውስጥ የገባውን ጉድፍ ለማውጣት በወንድሙ ዘንድ የታመነ ነው፡፡ በጽድቅም ምክንያት ዐይኖቹ ብሩሃን ናቸውና በወንድሙ ዐይን
ውስጥ ያለውን ጉድፍ ዐይኑን ሳይጎዳው ጉድፉን ብቻ ለይቶ ያወጣለታል፡፡ ወንድሙም ከሕመምና ከስቃይ ጤናማ ስለሚሆን እርሱም እንደ ጻድቅ ወንድሙ አጥርቶ
ማየት ይጀምራል፡፡ እንዲህ ነው መልካም ወዳጅ፡፡ ጻድቅ ሰው እንዲህ ነው፡፡ አይነቅፍም፤ አይቆጣም የወንድሙን ነውር ወይም ድክመት
በአደባባይ አያወራም፤ በወንድሙ ላይ አይታበይም፤ ወንድሙ ከእርሱ እንደሚሻል ይቆጥራል፤ ስለወንድሙ መዳን በአምላክ ፊት ያነባል፤
ወንድሙን ከስህተት መንገድ ለመመለስ ነገሮችን ሁሉ በጥንቃቄ ይከውናል፡፡