Monday, January 30, 2012

“ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጁዋ ከወዳጇ ጋር ያወጋችው ወግ” (ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/05/2004
ልጄ ሆይ አንተ የእኔ ስትሆን ሌሎች የእኛም ነው በማለታቸው እኔ እናትህ ቅናት አይሰማኝም ፡፡ ለአንተ ኃጢአቱን ለሚናዘዝ ሰው ሁሉ አምላኩ ሁነው ፤ አንተንም ለማገልገል ለሚተጋውም ጌታ ሁነው፤  ሁሉ የሚሹህ ልጄ ሆይ አንተን ያፈቀሩህ ሁሉ ወንድሞችህ ይሁኑ ፡፡
ልጄ ሆይ አንተ ከእኔ ማኅፀን ውስጥ በነበርክበት ወቅት እንዲሁ በውጪም በዓለም ነበርኽ፡፡ አንተ ከእኔ በሥጋ በመወለድ ከእኔ ሆድ ብትወጣም በሕቡዕ ግን ከእኔ ውስጥ ነበርህ ፡፡ኦ ! እኔን እናትህን በእጅጉ ያስገረምኽ ልጅ ሆይ አንተ ከእኔም ጋር ነህ በዓለምም ሙሉ ነህ፡፡
 ቅዱስ የሆንኽ ልጄ ሆይ በአካል የተገለጠውን አንተነትህን በሥጋዊ ዐይኖቼ  ስመለከት በነፍስ ዐይኖቼ ደግሞ  በሕቡዕ በውስጤ ያለውን ማንነትህን እስተውላለሁ፡፡ በአካል በተገለጠው ማንነትህ በኩል አዳምን ስመለከት ሕቡዕ በሆነው ማንነትህ በኩል ደግሞ ከአንተ ጋር አንድ ባሕርይ የሆነውን አባትህን እመለከታለሁ፡፡
ልጄ ሆይ! እንዲህ እጹብና ድንቅ የሆነውን ሁለት ዓይነት ገጽታዎች ያለውን ማንነትህን እኔ ብቻ ተመለከትኩትን? ልጄ ሆይ ይህን ሕቡዕ የሆነ ማንነትህን በሕብስቱ ውስጥ እንዲያዩት ፍቀድ፡፡ ሥጋህን በሚመገበው ሰው ሕሊና ውስጥ አንተነትህ ግለጥ፡፡ ልጄ ሆይ በግልጽም  ይሁን በሕቡዕ አንተነትህን  ያንተ ለሆነችው ቤተክርስቲያንህ እና ለእኔ ለእናትህ ዘወትር ግለጥልን፡፡

የአዳም ብሩካን ዐይኖች



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/05/2004

ዘፍ. ም.2፡18-25 ያለው ለእኔ ልዩ አንድምታ አለው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ “ሰውን በአርያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” አለና አዳምን ፈጠረው፡፡ በእርሱዋ ደስ ይለውም ዘንድ እጹብ ድንቅ አድርጎ ገነትን ፈጥሮ ሰጠው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲያ እጅግ ውብና ረቂቅ አድርጎ የፈጠራት ገነት አዳምን ደስ አላሰኘችውም ነበር፡፡ ለምን ቢባል አዳም በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል በመፈጠሩ የተነሣ እርሱን የሚመስል አቻ አስፈልጎት ነበርና ነው፡፡ የእርሱ አርዓያና አምሳል ያለው ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር እንደ አቻ ሊነጋገር አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አዳም ፍጡር እግዚአብሔር ደግሞ ፈጣሪ ነው፤ አዳም ግዙፍ እግዚአብሔር ረቂቅ ነው፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ እግዚአብሔር በገጽታው አዳምን ቢመስለውም ለአዳም እንደ አቻ ወዳጅ ሊሆነው አልቻለም፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር አርዓያ ያላት ፍጥረት አስፈለገችው፡፡
 ይህ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ እውቀት ቢሆንም ሰው ቀስ በቀስ ይህንን ተረድቶ የአምላክን ሥራ እንዲያደንቅ “እግዚአብሔር ሰውን በአርዓያውና በአምሳሉ ፈጠረ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ብሎ ወዲያው አዳምን እንደፈጠረው ሔዋንን በአካል እንድትገለጥ አላደረጋትም፡፡ ይህ ለአዳም አንዳች ትርጉም ሰጠው፡፡

Saturday, January 28, 2012

ስምንተኛዋ ቀን



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
20/05/2004
ለስሙ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ስቅለቱ ተፈጥሮአዊ ሥርዐታትን ሁሉ በመሻር እኛም እንደርሱ ከፍጥረታዊ ሕግ በላይ እንድንሆን አበቃን፡፡ አስቀድሞ ከተፈጥሮአዊ ሕግ ውጪ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለወንድ ዘር ተፀነሰ፤ በኅቱም ድንግልናም ተወለደ፤ እንደንግሥናው ማረፊያውን ከንጉሥ እልፍኝ ያደርግ ዘንድ የሚገባው ጌታ ከከብቶች በረት እንስሳት እስትንፋሳቸውን እያሟሟቁት ተገኘ፡፡ ድንግል ከሆነችም ክብርት ብላቴና ጡት ጠብቶም እንደ ሕፃናት አደገ፡፡ በአይሁድ ሥርዐት ሙሉ ሰው እስከሚባልበት እስከ ሠላሳ እድሜው ድረስ ሁሉን በቃሉ የፈጠረ አምላክ ዝምታን መረጠ፡፡
 እርሱ ሁሉን ማድረግ ሲቻለው በቅናት ተነሣስተው በእርሱ ላይ የስድብን ቃል በተናገሩት ላይ ስለክፋታቸው በብድራት ክፋትን አልመለሰላቸውም፡፡ ይልቁኑ “…አባቴን አከብረዋለሁ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ” ብሎ በትሕትና ቃል መለሰላቸው፡፡(ዮሐ.8፡49) ከፍጥረታዊው ሕግ ውጪ በጭቃ የዕውሩን ዐይኖች አበራ፡፡ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ሆኖ እግዚአብሔርን ይሳደባል ብለው ከሰሱት፡፡ ወንጀለኞችን በሲኦል የሚቀጣ እንደ ወንጀለኛ ተቆጠረ፡፡ አሕዛብ ለእግዚአብሔር የቀኑ መስሎአቸው ሊቀኑለት በሚገባው አምላካቸው ላይ ተዘባበቱበት፡፡ በጥፊ መቱት የረከሰ ምራቃቸውንም ተፉበት እርሱ ግን በምራቁ እርሱን ሰምተው መንጎቹ ይሆኑ ዘንድ ጆሮአቸውን ኤፍታህ ብሎ ከፈተላቸው፤(ማር.7፡35) አርዓያቸውንም ይለዩበት ዘንድ ዐይኖቻቸውን በምራቁ አበራላቸው፡፡(ዮሐ.9፡8) አይሁድ በወንጀለኛው ምትክ ቅዱስ የሆነውን ክርስቶስን ይሰቅሉት ዘንድ ተማከሩበት፡፡

የእውነተኛ ጸሎት ባሕርያትና ውጤቱ (ከስምዖን ሶርያዊ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/05/2004
መግቢያ
ይክበር ይመስገንና የጥንት ክርስቲያኖች ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ሕይወት ይኖራቸው ዘንድ ራሳቸውን የሚያስተካክሉበት የጽሙና ጊዜና ቦታ ነበራቸው፡፡ ቤታችውንም ሲያንጹ የጸሎት ቤትንም ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ይህች የጸሎት ቤት ጸሎት የሚያደርሱባት ብቻ ሳትሆን ቤተመጻሕታቸውም ናት፡፡ ለእነርሱ ሰገነታቸው እርሱዋ ናት እግዚአብሔር በዚያ ያስተማራቸውን ለማኅበራዊ ሕይወታቸው ማጣፈጫ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ ይህ ሕይወት የትህርምት ሕይወት ተብሎ ይታወቃል፡፡
 ይህ ሕይወት ከምንኩስና ሕይወት ፈጽሞ የተለየና ማንም ክርስቲያን ሊተገብረው የሚችል ምናልባትም ከምንኩስና ሕይወት የሚልቅ ሕይወት ነው፡፡ ክርስቶስ ቀን ቀን ሕዝቡን ካስተማረ በኋላ ማታ ማታ ወደ ደብረዘይት ተራራ በመሄድ በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ ይህ ግን እርሱ ተገብቶት ሳይሆን ለእኛ አብነት ሊሆነን በመሻት ነው፡፡ በትህርምት ሕይወትም ጸሎትን የምንጸልይበትና መንፈሳዊ መጻሕፍትን የምንመረምርበት ጊዜና ቦታ ሊኖረን ግድ ነው፡፡ በጨለማ ከአምላክ የተማርነው በተግባራዊ ሕይወታችን ለዓለሙ ሰባኬያነ ወንጌል በመሆን ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር እናቀርባለን፡፡ በዚህ ሕይወታችን በጥምቀት ያገኘነው የክህነት ሥልጣን ተግባራዊ ይሆናል(royal priesthood ይህን ለመረዳት “እናንተ የመንግሥቱ ካህናት ናችሁ የሚለውን ጽሑፌን ይመልከቱ) በዚህ ሕይወቱ እጅግ የሚታወቀው ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ እርሱ ጌታውን በመሰለ ሕይወት ይኖር ነበር፡፡ ማታ ማታ በጸሎትና መንፈሳዊ መጻሕፍት በመመርመር ሲተጋ ቀን ቀን ደግሞ ሕዝቡን በማስተማር ይተጋ ነበር፡፡ ወደፊት ይህን አስመልክቶ መጽሐፍ ይኖረኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ የትህርምት ሕይወት ሲባል ይህን ሕይወት እንደሆነ አንባብያን እንዲያስተውሉልን በትሕትና እጠይቃለሁ፡፡   

ሥራ ፈትነት ለብዙ ኃጢአቶች መወለድ በር ይከፍታል” ተብሎ ተጽፎአል፡፡ በትህርምት ሕይወት የሚኖር ክርስቲያን ጸሎት የማያደርስ ከሆነ እርሱ ሥራ ፈት ነው ፡፡ ቅዱሳን አባቶች ከሌሎች አግኝተው ለእኛ እንዳስተማሩን በእግዚአብሔር አገልግሎት የተጠመደ ሰው እርሱ በጸሎት እየተጋ  ነው ፡፡እኔ እንደማምነው “ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል”(መዝ.፩፥፪) እንዲል ነቢዩ ዳዊት በመልካም ሥራ በመትጋት ሕጉን ለመፈጸም የሚታትር ከሆነ እርሱ በእውነት ያለማቋረጥ እየጸለየ ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን ወደ ተሟላ መንፈሳዊ ከፍታ ሲደረስ፣ አመለካከቱም በመንፈስ ቅዱስ ሲታደስና ፍጹም ሰላምን ሲያገኝ፣ አንዲሁም አእምሮው በእግዚአብሔር ፍቅር ሲያዝ  እግዚአብሔር የዚህን ታራሚ ልቡና መገለጫው አድርጎታል ማለት ነው፡፡

Thursday, January 26, 2012

“ይህ ምሥጢር (በእውነት) ታላቅ ነው ፡፡”



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/05/2004
እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር ሲያበጀው በአርዓያውና በአምሳሉ መፍጠሩ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ውስጥ ያለ ሦስትነትና አንድነት በሰዎችም ዘንድ እንዲታይ በመሻቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን በአካል ሦስት ነው፡፡ በአካል ሦስት ሲሆን በእግዚአብሔርነቱ አንድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መገለጫው ባሕርይ የሕግጋት ሁሉ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር በመሆኑ በባሕርይው መገለጫ ስሙ እግዚአብሔርን ፍቅር እንለዋለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ፍጹም የሆነ አንድነት በአርአያውና አምሳሉ በፈጠረው ሰው እንዲገለጥ በሰው ሰብእና ውስጥ ፍቅርን ተከላት፡፡ በፍቅርም ሰውን ሁሉ ፍጹም ወደ ሆነ አንድነት ያመጣዋል፡፡ ያለፍቅር ሰው እግዚአብሔርን ከቶ ሊመስለው አይችልም፡፡
ይህ እንዲሆን እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ አዳምን ከፍቅር ጋር አዋሕዶ ፈጠረው፤ በመቀጠል ስለፍቅር ከጎኑ  አጥንት ሔዋንን አበጃት፣ የፍቅርን ፍሬ ይመለከቱ ዘንድ ደግሞ በሁለቱ አንድነት እኛን ልጆቹን ሰጣቸው፡፡ እነዚህ በቁጥር ሦስት ቢሆኑም በመገኛቸው አዳም አንድ ናቸው፡፡ እንዲህም ሲባል አባት፤ እናት እና ልጅ ማለታችን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ አንድነት ሲመሰክር “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ባረካቸውም፡፡ እነርሱንም በፈጠረበት ቀን ስሙን አዳም ብሎ ጠራው” ይለናል፡፡(ዘፍ.5፡1-2) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ሦስትነትና አንድነት በሰዎች ውስጥ እንዲታይ መፍቀዱን እናስተውላለን፡፡



Wednesday, January 25, 2012

በእውን እግዚአብሔር በሰዎች ልጆች ላይ ፍትሐዊ ነውን?(ቅዱስ ይስሐቅ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/05/2004
 ስለእግዚአብሔር ብሎ ማጣትን በፍጹም ፈቃደኝነትና ደስታ የተቀበለ ሰው እርሱ በውስጡ ንጹሕ የሆነ ሰው ነው፡፡ የሰውን ስህተት የማይመለከት እርሱ በእውነት አርነት የወጣ ሰው ነው፡፡ ከሰው በሚቀርብለት ክብር ያልተደሰተ እርሱንም በማያከብሩት ያልተከፋ ሰው እርሱ ለዚህ ዓለምና ለምድራዊ አኗኗር የሞተ ሰው ነው ፡፡ ማስተዋል ለሰዎች ከተሠሩላቸው ሕግጋት ሁሉ እጅግ የላቀና በየትኛውም ደረጃ እና መመዘኛ ሥራን በአግባቡ ለማከናወን ዓይነተኛ መሣሪያ ነው ፡፡ ኃጢአተኛውን አትጥላው እኛ ሁላችን የኃጢአትን ሸክም የተሸከምን በደለኞች ነንና ፡፡
 ስለ እግዚአብሔር ብለህ እርሱን ለመቃወም ከተነሣህ ግን ስለ እርሱ አልቅስለት ፡፡ ስለምን እርሱን ትጠላዋለህ? ኃጢአቱን ጥላ  ስለእርሱም መመለስ ጸልይለት ፡፡ እንዲህ በማድረግ በኃጢአተኞች ላይ ያለተቆጣውን ነገር ግን ስለእነርሱ መዳን የጸለየውን ክርስቶስን ምሰለው፡፡ ስለኢየሩሳሌም መጥፋት እንዴት እንዳለቀሰ አትመለከትምን ? በብዙ ድክመቶቻችን የተነሣ ሰይጣን በእኛ ላይ ያፌዝብናል ፡፡ በእኛ ላይ በሚያፌዘው ሰይጣን የሚፌዝበትን ወንድማችንን ስለምን እንጠላዋለን? ሰው ሆይ ስለምን እንዲህ ይሆናል ? ኃጢአተኛን መጥላት ትፈልጋለህ እርሱ እንዳንተ ጻድቅ መሆን ይሣነዋልን ? ፍቅር ሳይኖርህ የአንተ ቅድስና ምን ይጠቅምሃል ? ስለእርሱ ስለምን አታነባም ? ነገር ግን አንተ እርሱን ታሳድደዋለህ ፡፡ አንዳንዶች በኃጥአን ላይ ባለማስተዋል በቁጣ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የኃጢአተኞችንም ሥራ ለይተው የሚያውቁ አድርገው በራሳቸው  ይታመናሉ፡፡

Tuesday, January 24, 2012

“ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ”(ራእ.12፡1)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/05/2004
እነሆ ታላቅ የሆነ ለሰዎች ልጆች መዳን የሚጠቅመውና ትርጉም ያለው በአምላክ የተፈጸመው ታላቁ  ምልክት የታየው በምድር ላይ እንጂ በሰማያት ከመላእክት ጉባኤ አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ በነቢዩ “ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣቸኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለችው ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”(ኢሳ.7፡14) እንዲል ታላቅ የሆነው ምልክት የታየው በምድር ነው፡፡ ሰማያውያን መላእክት ራሳቸው እንኳ ይህ ታላቅ የሆነ ምልክት ለማየት ሲሉ ጌታ ከተወለደበት ግርገግም ተገኙ፤ "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ" እያሉ በምድር ዝማሬን አቀረቡ፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ “ታላቅ ምልክት በሰማያት ታየ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃን ተጫምታ በራሱዋም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች”(ራእ.12፡1)ሲል ስለ ጌታ ልደት ብቻ መናገሩ አልነበረም፡፡ ይህ ምልክት ከልደት እስከ ዕረገት በጌታችን ሥጋዌ የተፈጸሙትን የድኅነት ሥራዎችን ሁሉ የሚጠቀልል ነው፡፡እነዚህ የድኅነት ሥራዎች በምድር ይፈጸሙ እንጂ በሰማያዊው አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና ፍጹም ሰማያዊያን ናቸው፡፡ ያም ማለት በቦታና በጊዜ የሚወሰኑ አይደሉም፤ ዘለዓለማውያንና ዘመን የማይቆጠርላቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዘመን በማይቆጠርለት አምላክ የተፈጸሙ ናቸውና፡፡ እነዚህን የድኅነት ሥራዎች ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው  ሰውነት የከወናቸው ናቸው፡፡

Monday, January 23, 2012

ከሕግ በላይ የሆነው የደስታና የነጻነት ሥፍራ (ጋብቻ)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/05/2004
  ድሮ ድሮ ያኔ በገነት አንድ ሔዋን የምትባል ሴት ነበረች፤ እርሱዋም ዓለሙዋ በሆነ በአዳም ሰውነት ውስጥ ትኖር ነበር፡፡  አንድ ወቅት ባልዋ አዳም በውስጡ እየተመላለሰች ደስ ታሰኘው የነበረችውን ይህቺን ሴት በአካል ተገለጣ ሊያያት ፈለገ፡፡ ነገር ግን በውስጡ ተሰውራለችና ሊያያት አልተቻለውም፡፡ ስለዚህም የደስታ መፍሰሻ በሆነችው ገነት እጅግ ታላቅ በሆነ ትካዜ ተዋጠ ተከዘ አዘነ፡፡ ገነትም ገነት አልመሰለችውም፡፡ ነገር ግን ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ እግዚአብሔር የአዳምን ጽኑ ኀዘን ተመለከተ፡፡ ስለዚህም ጽኑ እንቅልፍ በእርሱ ላይ ጣለበት፡፡ ይህንን ቅዱሳን አባቶች በተለይ አምብሮስ ተመስጦ ይለዋል፡፡ በዚያ ጊዜ ነፍስ በሥጋ ሰውነቱዋ ላይ እግዚአብሔር የሚያከናውነውን ትመለከት ዘንድ ወደ አምላኩዋ ተነጠቀች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከሥጋዋ ከግራ ጎኑ፣ ከልቧ አጠገብ ሔዋንን  ለይቶ ገለጣት፡፡




Sunday, January 22, 2012

“የከበረው መሥዋዕት”(በቅዱስ ይስሐቅ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/05/2004

ልጄ ሆይ የአእምሮህን ምንጭ ንጹሕ አድርገው

ከቁጣና ከነቀፋ ቃልም አጽዳው

እንደ አዘቅት ጭቃ የሆነውን ቅናትን ከውስጥህ አስወግድ

አስተሳሰብህ ሁሉ ንጹሕ ይሁን፡፡

እግዚአብሔርን ለማየት በጸሎት ወደ እርሱ በቀረብክ ጊዜ

አንተን በሚጠባበቁህ በእግዚአብሔር የምሕረት እጆች ፊት ጸሎትህ ንጹሕና ቅዱስ ካልሆነ

ሥላሴ በአንተ አይታመንምና እንዲህ ሆነህ ከፊ አትቅረብ፡፡

ከበከተው ለእርሱ መሥዋዕት አታቅርብ

ለኃያሉ አምላክ ከአንተ ዘንድ የሚቀርበው መሥዋዕት

በቅናት የተቃኘ ጸሎት ከሆነ

የበከተ መሥዋዕት ማለት ይህ  ነው፡፡

ስለዚህ በአንተ ላይ በተቃጣው የቁጣ ቀስት ላይ ተጨማሪ ክብደትን አትጨምርበት

የተመረጥከው ወዳጄ ሆይ ! በሚያቃጥል ፍቅር የተቀመመ መሥዋዕትን አቅርብ

ለእርሱ እንደ መሥዋዕት አድርገህ የምታቀርበው ጸሎትህ ነው

እንዲህ ዓይነት መሥዋዕትን የሚያቀርቡት መንፈሳውያን ናቸው

ከአምላክ ዘንድ የሚቀርብ ይቅርታን የሚያሰጥ የጣፈጠ መሥዋዕት ይህ ነው፡፡

ስለዚህም በጥናህ ውስጥ ጠብ ካለ እርሱ ባዕድ ፍም ነው

እርሱንና እርሱን የመሰሉትን ፍሞች ከጥናህ ውስጥ አስወግዳቸው

 ልጄ ሆይ ባዕድ ፍምን በጥናህ ውስጥ በመጨመርህ ምን እንደሚመጣብህ አስበህ ፍራ

የአሮን ልጆች በድፍረት ያልታዘዙትን ፍም ከጥናቸው ውስጥ ጨምረው ነበርና በእግዚአብሔር ቁጣ ጠፉ (ሌዋ.፲፥፩-)

የመሥዋዕቱ ፍም ፍቅር ነው፤ በዚህም ፍም ላይ መሥዋዕት አድርገህ የምታቀርበውን ጸሎት አዘጋጅ

እንዲህ በማድረግህ ጸሎትህ የተወደደ መልካም መዓዛ ያለው ዕጣን ሆኖ ከእግዚአብሐር ዘንድ ይደርስልሃል

የፍቅር ፍም አመድ የለውም በመቀጣጠሉም ምንም ጭስ አይገኝበትም

በውስጡ ዘለዓለማዊና ጣፋጭ መዓዛ ያለው መሥዋዕትን ይዞአል

ደስ ከሚያሰኙ መሥዋዕቶችም በላይ እጅግ የላቀና የከበረ መሥዋዕት ይህ ነው፤

ክርስቲያን ሆይ ይህን ልብ በል!!(ከአብርሃም ሶርያዊ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
13/05/2004
ወገኔ ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ፣ የእግዚአብሔር ወዳጆች ለተባሉት ወንድም/እኅት/ ፣ ከሐዋርያትና ከሰማዓታት ጋር ከበዛው ጸጋቸው ተካፋይ ፣ ከእርሱም ምስክሮች ጋር አንድ ማዕድን የምትካፈል ፣ የቅዱሳን ርስት ወራሽና ቅን በሆነው ፍርዱ ደስ ይልህ ዘንድ ከነቢያት የፍርድ ወንበር ላይ የተቀመጥክ ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር በምስጋና የምትሳተፍ ፣ ከሱራፌልም ጋር የምትነጋገር ፣ ከኪሩበል ጋር በሰማያዊ ዙፋን ላይ የተቀመጥክ ፣ ከክርስቶስ የጸጋ ስጦታ ተካፋይ የሆንክ ፣ የብቸኛ ልጁ ሰርግ ታዳሚ ትሆን ዘንድ የተጠራህ ፣ የሰማያውያን ሠራዊተ መላእክት ወዳጅ ፣ የሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ዜግነት ያለህ ነህ ፡፡ አእምሮህ ውስጥ እነዚህ በክርስቶስ ለአንተ የተሰጡት የእግዚአብሔር ቸርነቶች ከተቀመጡ የጨለማው ዓለም ገዢ አገልጋዮች የሆኑ አንተን ሊያሰነካክሉህ አይችሉም ፡፡ በንስሐ ጽና ፡፡ ሕሊናን ከሚያቆሽሹ ከንቱ አስተሳሰቦች ራስህን ንጹሕ አድርግ ፡፡ ከእነዚህ ፈጽመህ ራቅ ከንቱ በሆኑ አስተሳሰቦችም አትሸበር፡፡”

Saturday, January 21, 2012

ስለሦስተኛው ልደት(ጥምቀት) ምን ያህል ያውቃሉ?



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/05/2004
እነኋት ክርስትና ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ
እንደ ሶርያ ቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ ሦስት ዓይነት ልደታት አሉ፡፡ እነርሱም ከሥጋ እናታችን የምንወለደው ልደት፣ ከውኃና ከመንፈስ የምንወለደው ልደት(ይህ በእግዚአብሔር በሆነው ሁሉ ላይ መብትን የሚሰጠን ነው) ሦስተኛውና መሠረታዊው ልደት የፈቃድ ልደት ነው፡፡ ይህ ልደት ሦስተኛው ልደት በመባል ይታወቃል ወይም ሦስተኛው ጥምቀት ይባላል፡፡ ለዚህ ልደት የሚበቃው ሰውነቱን በጥምቀት የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ያደረገ ክርስቲያን ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሲታዘዝ ክርስቶስን ወደ መምሰል ይመጣል፡፡ አንድ ክርስቲያን ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስን ወደ መምሰል ማዕረግ ሲያድግ ሦስተኛውን ልደት ተወለደ ይባላል፡፡ እኛ ክርስቲያኖችም ለዚህ ተጠርተናል፡፡ ለመሆኑ በዚህ በፈቃድ ልደት ውስጥ ያለ ክርስቲያን ላይ የሚንጸባረቁ ጠባያት ምን ምን እንደሆኑ ሶርያዊው ባለራእይው ዮሴፍ የዘረዘራቸውን እንመልከት፡፡

Friday, January 20, 2012

ክርስቶስ ለእኛ ኦርቶዶክሳዊያን ማን ነው?



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/05/2004 
እርሱ የእግዚአብሔር በግ ነው፤ እርሱም መሥዋዕት ነው፤
እርሱ ስለብዙዎች ኃጢአት የተሠዋው ፍሪዳ ነው፤ እርሱ መሥዋዕቱን የሚያቀርብ ሊቀ ካህናት ነው፤መሥዋት ተቀባዩም እርሱ ነው፤
ስለእኛ መከራን የተቀበለው እርሱ ነው፤ ስለእኛም የራራልን እርሱ ነው፤
እርሱ ሙሽራ ነው ፤እርሱ ራሱ ሙሽሪትም ነው፡፡(ከእናታችን የነሣው ሥጋ ለጌታችን እንደሙሽሪት ነው፡፡ ይህ ሥጋ ግን አምላክ በመሆኑ ሙሽራ ሆነ፤ በሐዋርያትም እኛ ለእርሱ ታጨን፡፡ ስለዚህም እርሱ ሙሽራ ነው፤ እርሱ ራሱ ሙሽሪት ነው አልን)
እርሱ  የሰርጉ ቤት ነው፤ እርሱ ራሱ  የሰርግ ቤቱ አሳላፊ ነው፤
እርሱ ገነት ነው፤ እርሱ ራሱ የሕይወት ዛፍ ነው፤
እርሱ  ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ነው፤ እርሱ ራሱ መቅደሳችንና ቅድስተ ቅዱሳናችን ነው
በውኆች የተመሰለው እርሱ ነው፤ እርሱ ራሱ እኛ የምንኖርበት ዓለማችን ነው፤
እርሱ  ምግባችን ነው፤ እርሱ ራሱ ስለድኅነታችን የሚመግበን መጋቢያችን ነው፤
እርሱ ሕያው የሆነው ሕብስት ነው፤ እርሱ የሕይወት ውኃችን ነው፤
እርሱ እውነተኛው የወይን ግንድ ነው፤ እርሱ ራሱ የደስታ ወይናችን ነው፤
እርሱ ዕንቁዋችን ነው፤ እርሱ ራሱ መዛግብታችን ነው፤
እርሱ መረባችን ነው፤ እርሱ ራሱ ተዋጊያችን ነው፤
እርሱ የጦር መሣሪያችን ነው፤ እርሱ ሁሉን ድል የሚነሣ ነው፤
እርሱ ግዝረታችን ነው፤ እርሱ ራሱ ሰንበታችንና ሕጋችን ነው፤
እርሱ የቅዱሳን ኅብረት ለሆነችው ቤተክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ መልካሙ የስንዴ ቅንጣት ነው፤
እርሱ የወይን እርሻችን ነው፤ የእርሻውም ባለቤት እርሱ ነው፤
እርሱ ግርማችን ነው፤ እርሱ እምነታችን ነው፤
እርሱ ሰርጋችን ነው፤ እርሱ የሰርግ ልብሳችን ነው፤
እርሱ የሕይወት መንገዳችን ነው፤ እርሱ በራችን ነው፤
እርሱ የጽድቅ ፀሐያችን ነው፤ እርሱ የነፍሳችን ብርሃን ነው፤
እርሱ ሕይወት ነው፤ እርሱ መንግሥተ ሰማያት ነው፤
እርሱ መጀመሪያ የሌለው መጀመሪያ፣ መጨረሻ የሌለው መጨረሻ፣ አልፋና ኦሜጋ ነው፤
ስለዚህም እኛ ኦርቶዶክሳዊያን በክርስቶስ ከክርስቶስ ለክርስቶስ የሆንን የክርስቶስ ነን!!!

የጽሙና ሕይወት ወዳዱ ዮሐንስ ሶርያዊ ስለ ጥምቀት ያስተማረው ትምህርት


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/05/2004


ሥጋዊው ማኅፀን የሚታይ ሥጋን ለብሰን እንድንወለድ በማድረግ ከዚህ ዓለም ፍጥረታት ቁጥር እንዲደምረንና የዚህን ዓለም ውበት ለማድነቅ እንደሚያበቃን እንዲሁ ጥምቀትም መንፈሳዊ ልደትን እንድንወለድበት የተዘጋጀ ማኅፀን ነውና ከሰማያውያን ፍጥረታት ጋር እንድንደመርና መንፈሳዊውን ዓለም ለማየትና ለማድነቅ እንድንበቃ ያደርገናል ፡፡ በሥጋ ካልተወለድን በቀር ግሩም የሆነውን የዚህን ዓለም ውበት ማየት እንደማንችል ሁሉ በጥምቀት ካልሆነ በቀር እውነተኛውን ዓለም ለማየት አንበቃም ፡፡ ጌታችን ለኒቆዲሞስ እንደተናገረው አንድ ሰው አስቀድሞ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልምና ፡፡…(ዮሐ.፫፥፫)
ያልተጠመቀ ሰው በኃጢአት ምክንያት ልክ እንደሞተ ሰው የአካል መገጣጠሚያዎቹ የተለያዩ የሚከረፋና የሚሸት ሬሳ ነው ፡፡ ሥጋ በነፍስ ምክንያት ሕያው እንደምትሆን ነገር ግን ነፍስ ብትለያት ፈርሳና በስብሳ ወደ አፈርነቱዋ እንድትመለስ በክርስቶስ አምኖ ያለተጠመቀም ሰው እጣ ፈንታው ይህ ነው፡፡ በክርስቶስ የማዳን ሥራ በጥምቀት ይህ ሰው ክርስቶስን ቢለብሰው የእግዘአብሔር አርዓያንና አምሳልን ገንዘቡ ከማድረጉ በተጨማሪ  በነፍስ ምትክ መንፈስ ቅዱስ ነፍሱ ይሆንለታል፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ዘንድ ሕያ እንጂ ሙ አይባልም፡፡
 ቅዱስ ጳውሎስ “… እኛም በአዲስ ሕይወት እንመላለስ ዘንድ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ፡፡”(ሮሜ.፮፥፬) እንዲሁም “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል”(ገላ.፫፥፳፯) እንዲል ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ጠላትነት ጠፍቶ ከእርሱ ጋር ማኅበርተኞች ሆነናል፡፡  በክርስቶስም ሰውነት በኩል የመለኮቱ ተካፋዮች ሆነናል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ ይህ እንደሆን ለማስረዳት “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ፤ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ፤ወንድም ሴትም የለም ፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”አለን ፡፡ ( ገላ.፫፥፳፰) ጥምቀትን ለእኛ በሞትህ በመመሥረት  ሕያዋን ያደረገኸን አምላካችን ሆይ ላንተ ክብር ይሁን!!!

Thursday, January 19, 2012

“በዓለ ጥምቀት የሙሽሪት ምዕመናን የደስታ ቀን”




ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/05/2004
አምላክ ሆይ በነቢዩ ኢሳይያስ “ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል ጻድቅ ባርያዬ በዕውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል ኃጢአታቸውንም ይሸከማል፡፡”(ኢሳ.53፡11) ተብሎ አስቀድሞ የተናገረው እውን ሆኖ ዛሬ በዐይናችን ተመለከትነው፡፡ ጌታ ሆይ! በሕማምህ ወለድከን፤ በጥምቀትም ከሞትህ ጋር በመተባበር በመንፈስና በእሳት በመጠመቅ እሳታውያንና መንፈሳውያን የሆኑ መላእክትን መሰልናቸው፡፡ ስለዚህም በእደ ዮሐንስ በባሕረ ዮርዳኖስ በመጠመቅ ለእኛ ጥምቀትን የመሠረትክባት ይህቺን ዕለት በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ፍቅር እንዲሁም በታላቅ ተመስጦ ሆነን እናከብራታለን፡፡
ጌታ ሆይ ልጆችህ ልዩ ልዩ ሕብረ ቀላማት ባላቸው አልባሳት አጊጠውና ደምቀው ቅዱስ ሥጋህንና ክቡር ደምህን ከተቀበሉበት ማዕድህ፣ አምሳለ መስቀል ከሆነው ከምሕረት ቃል ኪዳን ታቦትህ ፊት ሆነው፣ በሐዋርያት ለአንተ ለሰማያዊው ሙሽራ የታጩበትን  ቀን ነፍስን በሐሴት በሚሞላ መንፈሳዊ ዝማሬና በታላቅ ደስታ ሆነው ሲያከብሩ ከላይ ከአርዓም ተመልከት፡፡

በእውን ሕፃናት አምላካቸውን አያውቁትምን?(ክፍል ሁለት)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/05/2004
ቅዱስ ኤፍሬም ጥምቀትን ነቢዩ ኤርምያስን በተሸከመች ማኅፀን መስሎ ሲያስተምር “ነቢዩ ኤርምያስ ገና ከእናቱ ማኅፀን ሳለ ተቀደሰ ተማረ፡፡ ደካማ የሆነችው ማኅፀን የፀነሰችውን ቀድሳ የወለደች ከሆነ እንዴት ጥምቀት ከእርሷ ማኅፀን የተፀነሱትን ይበልጥ ቀድሳና አስተምራ አትወል! ጥምቀት ተጠማቅያንን ንጹሐንና መንፈሳውያን አድርጋ ትወልዳቸዋለች” ይለናል፡፡ ከቅዱሱ አስተምህሮ  እንደምንረዳው ገና ከእናታቸው ማኅፀን ሕፃናት ፈጣሪያቸውን እንደሚያቁና እንደሚለዩ ነው፡፡  ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ዳዊት "ኃጥአን ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፤ ሐሰትንም ተናገሩ"ይለናል(መዘዝ.56፡3) ቅዱስ ጳውሎስ ስለኤሳውና ስለያዕቆብ ሲናገር “ርብቃ ደግሞ ከአንዱ አባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ ከእርሱዋ ፡- ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለላት፡፡ ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው”(ሮሜ.9፡10) ብሎ ጻፈልን፡፡

በእውን ሕፃናት እግዚአብሔርን አያውቁትምን ?



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/05/2004 
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ከእናቱ ማኅፀን ሳለ የጌታውን እናት ድምፅ በሰማ ጊዜ ፈጣሪው እርሱን በአካል ሊገኛኘው ሽቶ ወደ እርሱ መምጣቱን አስተዋለ ፡፡ ከደስታው ብዛት የተነሣ ዓለሙ በሆነው ማኅፀን ቦረቀ ዘለለ ፡፡ አስቀድሞ በእናቱና በአባቱ የቅድስና ሕይወት ምክንያት እርሱን በመንፈስ ሲጎበኘው የነበረው እግዚአብሔር ቃል ፣ የፈጠረውን ሥጋ ለብሶ ከእናቱ ጋር ወደ እርሱ እንደመጣ ሲረዳ ሊተረጎም በማይሞከር ደስታ ተሞላ ፡፡

Wednesday, January 18, 2012

ሞቴን አስቤ ልደቴን

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/06/2000 ዓ.ም የተጻፈ
ቀኑ እንዴት ነጎደ! ውስጤን ፍርሃት ፍርሃት አለው መቼም ሰው ሳያውቀው ወደ እግዚአብሔር መጣራቱ አይቀሬ ነው፡፡ አምላኩ ፊት ለፍርድ ሊቆም ነፍሱ ከሥጋው በተለየች ጊዜ ከትሞ ይኖርባት የነበረችውን ይህችን ግዙፍ ዓለም እንደ ሕልም እንደቅዠት ሆና ትረሳዋለች፡፡ በተቃራኒውም ይህችኛዋም ዓለም እርሱን ፈጥና ለዘለዓለም ትረሳዋለች፤ ስም አጠራርህም ከእነአካቴው ከሰው ሕሊና ይጠፋል፡፡ ወደ አምላካችን በሄድን ጊዜ ለዘለዓለም ከምንለያት ከዚህች ዓለም ሳለን ማወቅና መጠንቀቅ ያለንባቸውን እውቀቶችንና መንፈሳዊ ተግባራት ከፊት ይልቅ ግልጥ ሆነው በሰዋዊ አእምሮአችን ከምናቀው በላይ የመላእክትን እውቀት ገንዘባችን በማድረግ እናውቃቸዋለን፡፡ በፊቱ በቆምን ጊዜ እኛ በእርሱ ዘንድ የታወቅን፣ የጠጉራችንም ቅንጣት የተቆጠረች፣ በእርሱ ዘንድ የተራቆትን እንደሆንን ይበልጥ ግልጥ ይሆንልናል፡፡ በዚህ ምድር ሳለን በእምነት የምንረዳቸውን እውነታዎች በዚያን ጊዜ በግልጥ እናያቸዋለን፡፡

ጥምቀት በቅዱስ ኤፍሬም



ስብከት ወተግሣጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም በሚለው መጽሐፌ ቅዱሱ ስለጥምቀት ያስተማረውን ትምህርት አስፍሬዋለሁ፡፡  ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዱን እንድታነቡት እነሆ ብያለሁ፡፡

¨ ቅዱስ ኤፍሬም በጥምቀት የገሃነም እሳት ይጠፋል ይለናል፡፡
“የሰውነት ትኩሳት ከሰውነታችን በሚመነጨው ላቦት እንዲቀዘቅዝ እንዲሁ በጥምቀት የገሃነም እሳት ይጠፋል ፡፡”
ከዚህ ተነሥተን እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ምልከታ የገሃነም ቦታዋ ከሰውነታችን ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡ እሳቱ የማይጠፋ መባሉም ከእኛ ዘለዓለማዊነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን መረዳት እንችላልን ፡፡ እኛ ዘለዓለማውያን ሆነን ስለተፈጠርን እሳቱም በሰውነታችን ውስጥ ዳግም አይቀጣጠልም፡፡ ይህ የሚያስረዳን ከጥምቀት በኋላ በራሳችን ፈቃድና ምርጫ  በድርጊትም ይሁን በቃል ጌታችንን እስካልካድነው ድረስ የገሃነም እሳት በሰውነታችን ውስጥ እንደማይኖር ነው፡፡
ስለዚህ መዳን አለመዳን በእጃችን እንደተያዘች መረዳት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ይህን መብታችንን የማንጠቀምበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እርሱም በምጽአትና በሞት ወደ እግዚአብሔር ለፍርድ በተወሰድንበት ወቅት ነው፡፡ እስከዛው ድረስ ግን የገሃነምን እሳት በሰውነታችን ላይ ማቀጣጠልም ይሁን ማጥፋት ወይም ሰውነታችንን የጌታ ቤተመቅደስ ማድረግ ወይም አለማድረግ የእኛ ፈንታ ይሆናል፡፡ 
 ¨ ቅዱስ ኤፍሬም ጥምቀትን ወደሰማያት የምንወጣጣበት መሰላል ብሎም ይጠራዋል፡፡ 
“እርሱ ወደ ጥምቀት በመውረድ ጥምቀትን መሠረተልን እርሱም በሠራልን ጥምቀት ወደ ሰማየ ሰማያት ተነጠቅን ፡፡”
 ¨ ቅዱስ ኤፍሬም መጠመቂያ ገንዳውን በክርስቶስ መስቀል ይመስለዋል ፡፡ በውስጡም ክርስቶስን ለብሰን እንወለዳለን ሲለን እንዲህ ይላል ፡፡ 

Tuesday, January 17, 2012

አንብቦተ መጽሐፍ በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
08/05/2004
አዲስ አበባ

           ቅዱስ ኤፍሬም ስለአንብቦተ መጽሐፍ  ፖፕሊየስ ለሚባል ወዳጁ በጻፈው ደብዳቤው ላይ እንዲህ ብሎ እናገኘዋልን፡-
“ንጹሕ መስታወት የሆነውን የጌታችንን ቅዱስ ወንጌል በእጅህ መያዝን ስላልተውክ መልካምን አደረግህ ፡፡ በእርሱ መስታወትነት ማንም ምን መምሰል እንዳለበት ይረዳበታል ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ወገኖች በዚያ ውስጥ ምስላቸውን ከማግኘታቸው በተጨማሪ የራሳቸውን ተፈጥሮ በማስተዋል ከነውር እንዲጠበቁትና በቅድስና ጸንተው ያለመለወጥ እንዲመላለሱ ይረዳቸዋል ፡፡ በሰውነታቸውም ላይ ነውር አይገኝም ፤ ከእድፍም የጸዱ ይሆናሉ ፡፡
በመስታወት ፊት ባለቀለም ቁስ ቢቆም እንደቀለሙ ዓይነት እንዲሁ መስታወቱ ይሆናል ፡፡ ነገር ግን የመስታወቱ  ባሕርይው አይቀየርም ፡፡ ነጭ የሆነ ቁስ በፊቱ ቢያቆሙ ያንኑ ነጭ ቁስ መልሶ ያሳየናል ፡፡ ጥቁር ቀለም ያለው ቁስ በፊቱ ቢቆም የጥቁረቱን መጠን ያሳየዋል ፡፡ ቀይ ከሆነም ቅላቱን ያሳየዋል ፡፡ ውብ ገጽታ ካለው ደግሞ ውብቱን ያሳየዋል ፡፡ መልከጥፉም ከሆኑ እንዲሁም ለዐይን ምን ያህል እንደሚያስቀይሙ ያሳያቸዋል ፡፡ እያንዳንዱን የሰውነታችንን ገጽታ በዚህ መስታወት ውስጥ እናየዋለን ፡፡

Monday, January 16, 2012

በእውን ሰው በመበደሉ መንፈስ ቅዱስ ይለየዋልን?




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
 07/04/2004 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መግቢያ
 ፊሊክስዩስ በሰሜናዊ ሶርያ ለምትገኝ ማቡግ ለምትባል ቤተክርስቲያን ጳጳስ የነበረ አባት ሲሆን ፤ በዘመኑ በጣም ታዋቂ የሆነ የነገረ-መለኮት ሊቅ ነበር፡፡ የኬልቄዶንን ጉባኤ በመቃወም በሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተጠቃሽ የሆነ አባት ሲሆን እርሱ የኬልቄዶንን ጉባኤን የመቃወሙ ምክንያት የኬልቄዶናውያን አስተምሀሮ መለኮትን ከትስብእት ለመነጣጠልና ለመለያየት የሚሞክር ትምህርት ነው በማለት ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የእርሱ ጽሑፎች በነገረ መለኮት ላይ ያተኮሩ ቢሆኑም የሥነ ምግባር ትምህርቶችንም አብዝቶ ጽፎልናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ይህን ይመስላል፡፡
“ከእግዚአብሐር የተቀበልነው መንፈስ ቅዱስ የነፍሳችን ነፍስ ነው፡፡ ስለዚህም  ጌታችን በሐዋርያት ላይ እፍ በማለት መንፈስ ቅዱስን አሳደረባቸው፡፡ በእነርሱም መንፈስ ቅዱስ የነፍሳችን ነፍስ ይሆን ዘንድ ለእኛ ተሰጠ፡፡ በተፈጥሮአዊዋ ነፍስ ነፍስ ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን፡፡ ልክ ነፍሳችን የሥጋችን ሕይወት እንደሆነች፤ መንፈስ ቅዱስም የነፍሳችን ሕይወት ማድረግ እንደሚገባን ለማስገንዘብ ለነፍሳችን ነፍስ ይሆን ዘንድ በጥምቀት መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን፡፡ ከአዳም የተሰጠችው ሕይወት ከእግዚአብሔር እስትንፋስ የተገኘች ነበረች፡፡ “የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ ነበር፡፡ ነገር ግን በመተላለፈ ከእርሱ ተወሰደ፡፡(ዘፍ.፪፥፯)

Sunday, January 15, 2012

ክርስቶስና ክርስትና

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
05/04/2004 ዓ.ም
ክርስትና ማለት ክርስቶስ ማለት ነው፤ ክርስቶስም ክርስትና ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰው ተፀንሶ በመወለድ፣ በየጥቂቱ አደገ መጽሐፍ እንዲል ኃጢአትን እስከ ሞት ድረስ ተቃወመ፡፡ ክርስትናም እንዲሁ ናት ተፀንሳ ልትወለድ በየጥቂቱም ልታድግ ኃጢአትን በመቃወም እስከሞት ልትጸና ይገባታል፡፡
ክርስትና ማለት ክርስቶስ፣ ክርስቶስ ማለት ክርስትና ማለት ነው፤ ቤተሰብም ቤተክርስቲያን ማለት ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም በቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፤ ስለዚህ ቤተሰብ ቅድስት ድንግል ማርያምን ሊመስል ይገባዋል፡፡ እርሱዋ እግዚአብሔር ከወላጆች ሊገኝ የሚገባው መንፈሳዊ ብስለት ውስጥ ስለነበረች ክርስቶስን ለ...መውለድ ተመረጠች፡፡ የእርሱዋ ቤተሰብን በመንፈሳዊ እውቀት የመምራት ብቃቱዋን ለማስረዳት ለእኛ “በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት በጥበብና በሞገስ እንዲሁም በቁመት አደገ” ተብሎ ጻፈልን፡፡ እርሱዋ የእውነተኞች ወላጆች ምሳሌ ናት፡፡ ቤተሰብና ቤተክርስቲያን እንዲሁ ልጆቻቸውን ክርስቶስን መስለው እንዲያድጉ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት በጥበብና በሞገስ በጤንነትም የማሳደግ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ሕይወት ክርስትና ይባላል፡፡
ወይም ክርስትና እንደ መስቀሉና ክርስቶስ ናት፡፡ መስቀልን ስናስብ ጌታችንን አምላካችንን ከልደቱ እስከሞቱ ለእኛ አብነት የሆነባቸውን ተግባራዊ የሕይወት ምልልሶችን እናስባለን፡፡ መስቀልን ከክርስቶስ ክርስቶስንም ከመስቀል ነጣጥለን እንዳናስብ ክርስትናንም ከክርስቶስ ክርስቶስንም ከክርስትና ነጣጥለን አናስብም፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም “ስቅለቱ የእርሱን ልደት ሲያውጅ ልደቱ ደግሞ የእርሱን ሞት ያውጃል” ብሎ ያስተምራል፡፡ ክርስቶስ በሥጋ ከእውነተኛይቱ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ካልተወለደ እንዴት ሊሞት ይችላል? እርሱ ሊሰቀል የሚገባው ከሆነ በሥጋ ሊወለድ ግድ ነው፡፡ምክንያቱም መለኮት በባሕርይው ሞት የለበትምና፡፡ ስለዚህ አንዱ ለአንዱ ማስረጃ ሆነ፡፡ ልደቱን ስናስብ ኃጢአትን በመቃወም ክርስቶስን ወደ ማወቅ ልናድግ እንጂ ልደቱን አሳበን የኃጢአት ፈቃዳችንን ልንፈጽም አይደለም፡፡ ቤተሰብ የክርስትና ሕይወታችን መሠረት ነውና እናንተ ወላጆች ሆይ ቅድስት ድንግል ማርያምን ምሰሉዋት፡፡ ልጆቻችሁን በመንፈሳዊ ጥበብና እውቀት አበልጽጋችሁ ክርስቶስን ለብሰው እንዲያድጉ ትጉ፡፡ ንጹሕና ቅዱስ የሆነውን አዲሱን ሰው ክርስቶስን እወቁት ምሰሉት! ክርስትና ይህቺ ናት፡፡ ክርስቶስ በእኛ ይገለጥ ዘንድ በልደቱ እርሱን በመምሰል እስከሞት ድረስ ኃጢአትን በመቃወም እንኑር፡፡ መልካም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ይሁንልን አሜን!!

ስለፍቅር



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን ሰኞ 30/05/2003
አዲስ አበባ 

እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፡፡ እርሱ እጅግ ጥልቅ ከሆነው ለእኛ ለሰዎች ከመረዳት ባለፈ ፤ በእርሱ ብቻ በሚታወቅ ፍቅር ውስጥ ይኖራል፡፡ ሰውን በእርሱ አርዓያና አምሳል ፈጠረው ስንልም በባሕርይው ፍቅር የሚስማማው አድርጎ ፈጠረው ስንል ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰዎችን እጅግ ይወዳል፡፡ ሰውን በማንኛውም ማለትም በትልቅም ይሁን በትንሽ ባለማወቅም ይሁን በድፍረት በስውርም ይሁን በግልጽ በተንኮልም ይሁን በተግዳሮት የምናሳዝነው ከሆነ የምናሳዝነው ሰውየውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ጭምር ነው፡፡ በእኛ ያዘነው ሰው ልቡ በሃዘን ሲሰበር፤ እግዚአብሔርም እጅግ ያዝናል፡፡ በሃዘን ውስጥ ያለውን ሰው ከልቡ ደስ እንዲሰኝ ስናደርገው እግዚአብሔርም ደስ ይለዋል፡፡ በቅንነት ወደ ሰዎች ሁሉ ስንቀርብ እርሱም ከእኛ ጋር በቅንነት ይቀርባል፡፡ ሰዎችን ሁሉ እኩል ስናይለት ልቡ በደስታ ትፈካለች፡፡ በተንኮል ስንቀርብ ግን ግርማው ብቻ እንደሚያርድ አንበሳ በቁጣው ያርበደብደናል፡፡ በክፋታችን ከጸናን ደግሞ ያደቀናል ከእርሱ እጅ የሚታደገን ማንም አይኖርም ፡፡ ክፋታችንን አውቀን ከልባችን መጸጸታችንን ሲመለከት ደግሞ ልጁዋን እንደምታፈቅር እንስፍስፍ እናት ኃጢአታችንን ሁሉ ረስቶ በጸጋዎቹ እየሳመን ያጽናናል፤ ከእቅፉ ውስጥም በማኖር በፍቅሩ ያሞቀናል፡፡ የእርሱ ሃዘን ሰዎች ፍቅር ያጡ ጊዜ ነው፡፡

ኤደን ገነት በቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ

“ኤደን ገነት የተባለችው የእግዚአብሔር ፍቅር ናት፡፡ በዚች ውስጥ የገነት በረከቶች ሁሉ ይገኛሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከምድር በመነጠቅ መለኮታዊ ምግብን ተመግቦ የጠገበባት ቦታ ይህቺ ናት፡፡(፪ቆሮ.፲፪፥፪-፬) ከዚያ የሕይወት ዛፍ ፍሬ በልቶ ከጠገበ በኋላ “ዐይን ያላየችው ጆሮም ያለሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” ብሎ መሰከረላት፡፡( ፩ቆሮ.፪፥፱ )… እንደእኔ እምነት በሲኦል ያሉ ነፍሳት የሚቀጡት በፍቅር ማጣት ነው እላለሁ ፡፡ ፍቅርን ከማጣት የበለጠ እጅግ የሚጎዳና የሚያም ሕመም ምን አለ ? በፍቅር ላይ በደልን የፈጸሙ ሰዎች በራሳቸው ላይ እጅግ የከበደና አስፈሪ ቅጣትን አመጡ ፡፡….” (ቅዱስ ይስሐቅ)

የአምላክ እናትነት




ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን 4/06/2003 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ጌታ ሆይ የእጅህ ሥራ ስለሆንኩ እጅግ ግሩምና ድንቅ ነኝ፡፡ ስለኃጢአቴ ራሴን ብወቅስም አንተ ግሩምና ድንቅ አድርገህ የፈጠርከውን ሰውነቴን በኃጢአቴ ምክንያት የተዋረደ ነው አልለውም፡፡ ይህ ሰውነት በአንተ ንጹሐን እጆች የተበጁ ናቸውና፡፡

እናቴ ሆይ ንገሪኝ አንቺ ትሆኝ ከሆድሽ ሳለሁ ሰው እንድሆን ዐይንና ጆሮ አፍንጫንና ግንባርን የሠራሽልኝ፣ ወይስ አንቺ ትሆኚ ሥጋዬን ከአጥንቴ ጋር አዛምደሽ ያበጃጀሻቸው? ወይስ በሥጋዬ ውስጥ ደምሥሮቼንና ጅማቶቼን አንዲሁም ልብና ኩላሊቴን ሌሎችንም ውስብስብ የሆኑ የሰውነት ሥርዐቶችን የሠራሻቸው? አንቺ ከሆንሽ በምን እውቀትሽ? እንዲህ ከሆነ ከእናቴስ በላይ አዋቂ ማን አለ? ከእናቴስ በላይ ሁሉን ቻይ ማን አለ? ነገር ግን እናቴ ዐይኖቹዋን በፍቅር ወደ አምላኩዋ አቅንታ “አንተን ከእኔ እኔንም ከእናቴ ማኅፀን ያበጀኝ እርሱ እግዚአብሔር ነው” ብላ አመላከተችኝ፡፡ ከልቡዋም ሆና እርሱዋን ሠርቶ በእርሷ ልጆቹዋን የፈጠራቸውን አምላኩዋን ዐይኖቹዋ የፍቅርን እንባ አንዳጋቱ ሲጋ እየተናነቃት ወደ እርሱ አንጋጠጠች፤ ተንበርክካም ስለቸር ስጦታው አመሰገነችው፡፡ በግንባሩዋም ተደፍታ ሁሉን እንዲህ ላከናወነው ለእርሱ ሰገደችለት፡፡ ከሰጊዱዋም ቀና ስትል ጉንጮቹዋ በእንባ ረጥበው ነበር፡፡ ዐይኖቿንም አቅንታ ክርስቶስ ከሥጋዋ ከፍሎ ወደ ፈጠራቸው ልጆቹዋ ተመለከተች፡፡ ነገር ግን እንባዋ ከጉንጮቹዋ መጉረፉን አላቋረጠም ፡፡ ምክንያቱም ጌታ ሆይ የአንተ እጅ ሥራ ናቸውና፡፡

በእውን ክርስቶስ ኢየሱስን እናውቀዋለንን?


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/04/2004
አዲስ አበ

እጅግ ጠንቅቄ የማውቀው አንድ ሰው ነበር ፡፡ በእጁ ምንም ስባሪ ሳንቲም የለም ፤ ጸጉሩም አድጓል ፡፡ በእጁ ምንም ባለመኖሩ ምክንያት ጸጉሩ ቢያድግም መከርከም አልቻለም ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሌላም የገንዘብ እዳ አለበትና ጭንቅ ይዞታል ፡፡ ወዲያው አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ ለራሴ“በእውኑ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጉሩን ያሳደገው ከድህነት የተነሣ ይሆንን? አልኩኝ ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው “ለወንድ ጠጉርን ማስረዘም ነውር ነውና”(፩ቆሮ.፲፩፥፲፬፣፲፭) ድህነት ደግሞ ለዚህም ያጋልጣል ፡፡
ጌታችንም ያደገው በምድራዊው ሀብት ደሃ ከምትባለው በሰማያዊው ብልጥግና ግን እጅግ ባለጠጋ ከሆነችው ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥር ሆኖ ነው ፡፡ ሐዋርያት “እኛ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን”(፪ቆሮ.፱፥፲፪) ካሉ ቅድስት ድንግል ማርያም እንዴት ከእግዚአብሔር ዘንድ ባላት ሞገስ የተነሣ ከጸጋ ተራቁተው ያሉትን ባለጠጎች አታደርግ ? እርሱዋ የክርስቲያኖች ሁሉ ተማሳሌት የሆነች ፣ ራሱዋን በቅድስና ሕይወት በማመላለስ እግዚአብሔር ለሌላ የማይፈጽመውን ወደ እርሱዋ በመምጣት በሥጋ ከእርሱዋ በመወለድ እናቱ ትሆን ዘንድ የመረጣት ፣ እውነተኛ እናቱ ናት ፡፡ ቢሆንም በምድራዊ ብልጥግና በእርግጥም ደሃ ነበረች ፡፡ “እፎ ቤተ ነዳይ ኀደረ ከመ ምስኪን እምሰማያት ወረደ ላዕሌሃ ፈቲሖ ሥነዚአሃ ወተወልደ እምኔሃ” እንዲል፡፡

ኦ ክርሰቶስ!!!


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ
05/04/2004 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኦ ክርስቶስ ስላንተ ሴቶች ወንዶችን ተከትለው ሄዱ፡፡(ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል የሚለውን ቃል ሽረው) ዘፍ.2፡24 ፡፡መበለት የነበረችው ትዕማር እርሱን(የባሎቿን አባት የአባታችን የያዕቆብ ልጅ ይሁዳን) ተመኘችው ፡፡ሩት ስለአንተ በእድሜ ያረጀውን ሰው ወደደችው፡፡ አዎን ሰዎችን በዝሙቷ የምትማርከው ረዓብ ባንተ ተማረከች፡፡ ትዕማር ጨለማን ለብሳ በጨለማ ወጣች ብርሃንንም ሰረቀች፡፡ ንጹሕ ባልሆነ መንገድ ንጹሕ የሆነውን ሰረቀች፡፡ ሰውነቷን በማራቆት አንተን ለመስረቅ ተጓዘች፡፡ንጹሕ ካልሆነው ንጹሕ የሆነውን የምታስገኝ አምላካችን ሆይ! ሰይጣን እርሷን አይቶ ተንቀጠቀጠ፤እናም እርሷን ለማሸበር ተፋጠነ፤ በእርሷ አእምሮ ውስጥ ፍርድን አስገባ፤ ነገር ግን እርሷ አልተሸበረችም፡፡ ስለአንተ በድንጋይ መወገርና በሰይፍ መቀላት አላስደነገጣትም፡፡ ይሁዳን ለማጥመድ ዘማውያንን መሰለች ከእዛ በኋላ ግን ልትዘሙት አልወጣችም፤ ምክንያቱም ዝሙትን የማይፈቅደውን ጌታ ሽታ ነውና የወጣችው፡፡ (ቅ/ ኤፍሬም ዘሶሪያ)

የተባረከው ሩካቤ (ለሙሽሮች)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/02/2003 ዓ.ም
አዲስ አበባ


ባልና ሚስትን ሰማያዊ ወደ ሆነው የደስታ ሥፍራ እንዲነጠቁ የሚያደርጋቸው፤ ፍቅር ከሞላበት ኩልል ካለው ከብርሃናዊ ምንጭ ጠጥተው የሚረኩበት፤ የደስታን እንባ በማንባት በፍቅር ግለት ልክ ከእናቱ ማኅፀን ግሩም በሆነ ጥበብ በእግዚአብሔር እጅ እንደሚፈጠር እቦቀቅላ ሕፃን አንድ አካል ለመሆን በእግዚአብሔር የሚሠሩበት ማኅፀን፡፡
የጌታን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በየእለቱ አንድንቀበል በዚህም ወደሰማያዊ ምንድግናና ከክርስቶስ ጋር ፍጹም ወደሆነ ተዋሕዶ አንደምናድግ፤ እንዲሁ በዚህ የተባረከ ሩካቤ እግዚአብሔር ፍጹም ወደሆነ የአካል፣ የመንፈስ፣የስሜት ፣የፈቃድ አንድነት እንድንመጣ ለመላእክት ያይደለ ለእኛ ...ለሰው ልጆች ብቻ በእጁ ከምድር አፈር እንዳበጀው አዳም ሆነን ዳግም እንድንፈጠር የተሰጠ ግሩም ስጦታ፡፡

“እናንተ የመንግሥቱ ካህናት ናችሁ”(1ጴጥ.2፡5-9)



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
5/04/2004
አዲስ አበ
መቼም ካህን የሚለውን ቃል ትርጉም የሚያጣው ክርስቲያን አይኖርም፡፡ ለማስታወስ ያህል ግን ካህን ማለት አገልጋይ ማለት ነው ፡፡ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ሆኖ እግዚአብሔርንም ምዕመናኑንም የሚያገለግል መካከለኛ ፡፡ ይህ ይጠፋዋል ተብሎ የሚታሰብ አንድም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የለም ፡፡ ባይሆን ወዳጄ ሆይ ይልቁኑ አንተ ራስህ ስለእነርሱ መዳን ለሞተላቸው ነገር ግን ወደ ክርስትና እምነት ላልተመለሱ ዘመዶችህ በምግባር አብነት ሆነኻቸው፣ በቃልም አስተምረሃቸው ወደ ጥምቀት በማቅረብ ከእግዚአብሔር ጉባኤ እንዲቀላቀሉ ቤተክርስቲያን ካህን አድርጋህ እንደሾመችህ ታውቃለህን ? መቼም እንዲህ ስትባል “እንዴ ! ምነው! ቤተክርስቲያንን ይመሩና ያስተዳድሩ ዘንድ ጳጳሳት የሾሟቸው ካህናት የት ሄደው ነው እኔን ካህን ማለትህ ? ብለህ ልትጠይቀኝ ትችላለህ ፡፡

Saturday, January 14, 2012

“ከተኩሎች ተጠበቁ”


ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
ቀን16/09/2000 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መግቢያ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰዎች ፍቅርን ከማጥፋቸው የተነሣ እግዚአብሔር መንግሥትን እንደሰጣቸው ያስተምራል፡፡ በእርግጥም ላስተዋለው ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ገዢና ተገዢ ወይም ባርያና ጌታ የሚሉት ቃላት የመጡት የኖህ ልጅ ካም የአባቱን እርቃን ተመልክቶ በእርሱ ላይ በመሳለቁ ነበር ፡፡ ኖህ ከስካሩ ሲነቃ ካም በእርሱ ላይ እንደተሳለቀበት አወቀ ስለዚህም ልጁን ረገመው፡፡ “ከንዓን የባሮች ባሪያ ይሁን” አለው፡፡ ከዚያ ወዲያ በኃጢአት ምክንያት የገባው የገዢና የተገዢ ሥርዐት በአህዛብ መልክና ቅርጽ እየያዘ  መንግሥት ወደ መሆን መጣ፡፡ በእስራኤልም ሕዝቡ እግዚአብሔር ገዢአቸው እንዳይሆን በመሻታቸው እንደ አሕዛብ ንጉሥ ይኑረን ብለው ነቢዩ ሳሙኤልን በጠየቁት ጥያቄ መሠረት የመጀመሪያውን የመንግሥት ሥርዐት በጨካኙ ሳኦል ተዋወቀ፡፡ እንደ ቤተሰብ ይተያዩ በነበሩት ሕዝቦችም ዘንድ ገዢና ተገዢ ተፈጠረ፡፡ የእግዚአብሔር አሳብ የነበረው ግን ሰው ቤተሰባዊ በሆነ ሕግ እንዲመራ ነበር፡፡ አሁን ይህ ቤተሰባዊ ሥርዐት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በደሙ በመመሥረት ሰጥቶናል፡፡